>
5:16 pm - Thursday May 23, 2052

ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪና ኤሊያስ ገብሩን የእስር ቤት ጉብኝት [በጋዜጠኛ ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን]

ananiya-sory-and-elias-gebiruዛሬ ስል፣ ነገ ስል ፣ እንደገና ነገ ስል ….. ቀናት ተቆጠሩ፡፡ ሳምንታት ተደመሩ፡፡ ዛሬ እኩለ ቀን ግን ከራሴ ጋር ተዋቅሼ ስልኬን አንስቼ ወደ ሙያ አጋሬ ፍፁም ማሞ ደወልኩ፡፡ “ሌላ ጉዳይ ከሌለህ እነ ኤልያስ ገብሩ እና አናንያ ሶሪን ብንጠይቅስ? ከ 8 ሰዓት ጀምሮ መጠየቅ ይቻላል አሉ” አልኩት፡፡

“ጥሩ ሃሳብ፤ መጣሁ፡፡ ስድስት ኪሎ እንገናኝ” አለኝ፡፡ እና ከቀኑ ሰዓት ሲል ወደ ቀበሌ 24 መረሽን፡፡….. ወደ 20 የሚሆኑ ሰዎች የእስር ቤቱ በራፍ ላይ ሰልፍ ይዘው እየጠበቁ ነው፡፡ እኛም ተሰልፍን፡፡ ግቢው ውስጥ የሚታዩ መስኮቶች ፊት ለፊት በርካታ ሰዎች ተገጠግጠው ሲጯጯሁ ከሩቅ ይታየናል፡፡ ከግቢው በር ላይ ከቆሙት ሴትና ወንድ ፖሊሶች አጠገብ የታሸገ ውሃ ፣ ለስላሳ፣ ሶፍትና ብስኩቶች የሆነ ጠረጴካ ነገር ላይ ተደርድሮ ይታየኛል፡፡
“የሚሸጥ ነው?”
“አዎ ….” አለኝ ፖሊሱ፡፡
የገቡት ከፊል ጠያቂዎች እንደወጡ “ሴት እስረኞች የሚጠይቅ አለ?” ሌላ ፖሊስ ከውስጥ እየጮኸ፡፡
“ወይንሸት ሞላን ለምን አንጠይቅም?” አልኩት ከኋላዬ ወደቆመው ጓደኛዬ ዞሬ፡፡
በር ላይ የቆመችው ፖሊስ “ወይንሸት እዚህ የለችም” አለችኝ ከመቅፅበት፡፡
“ግን እኮ ….እዚህ መሆኗን ነበር የማውቀው” አልኳት፡፡
“እዎ፤ እዚህ ነበረች፤ ወስደዋታል ….”
“ወስደዋታ ….ል? ማነው የወሰዳት?”
መልስ አልሰጠችኝም፡፡ “የማነው ነፈዝ” የሚል አስተያየት እያየችኝ ዝም አለች፡፡ ወይንሸት እዚያ አለመኖሯን እዚሁ ፌስቡክ ላይ አንብቤአለሁ፡፡ ምናልባት የተወሰደችበትን ቦታ ታውቅ ይሆናል ወይም ፍንጭ ትሰጠኝ ይሆናል በሚል መንፈስ ነው ሆን ብዬ ጥያቄ የምሰነዝርላት፡፡
“ማለቴ …. ከዚህ እስረኞች ሲወሰዱ ወዴት እንደሚሄዱ እናንተ ሳታውቁ አትቀሩም መቼም?”
“አናውቅም” አለችና ፊቷን አዞረች፡፡ አትጨቅጭቀኝ ዓይነት፡፡
ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ከዋናው በር በስተጀርባ የተደረደረውን እሽግ ውሃ እየጠቆምኩት “ይሄ ነገር የሚሸጥ ነው?” ስል ጠየቅኩት በረኛውን ፖሊስ፡፡ አዎ አለኝ፡፡ ገዛሁ፡፡ የገዛሁትን ውሃ ይዤ ወደ ውስጥ ልዘልቅ ስል “ይዘህ መግባት አትችልም” ፖሊሱ፡፡
“ማለት?” ግር ብሎኝ አየሁት፡፡ “ከምትጠይቀው እስረኛ ዕቃ ተቀብለህ ገልብጠህ ትሰጠዋለህ”
(እዛው ግቢ ውስጥ የታሸገ ውሃ እየሸጡ ማሸጊያውን እቃ ይዘህ አትገባም ማለት ምን ማለት ነው?)
ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ውሃውን እዛው ትቼ ገባን፡፡ መጠየቂያው መስኮት ፊት ለፊት 10 ያህል ሰዎች ቆመዋል፡፡ ከሚጠይቁት ሰው ጋር ያወራሉ፤ ይጯጯሃሉ ማለት ይቀላል፡፡ እንደምንም ተንጠራርቼ እነ አናንያን እንዲጠሩልን ነገርኳቸው፡፡ መጡ፡፡ ከመጠየቂያው መስኮት ባሻገር ሁሉት ወይም ሶስት ሜትር ርቀት ላይ ሌላ ፍርግርግ ብረት አለ፡፡ በፍርግርጉና በመስኮቱ መሃል ሁለት ፖሊሶች ቆመዋል፡፡
አናንያ እና ኤልያስ መጡ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ዳንኤል ሺበሺም ከኋላቸው ብቅ አለ፡፡ ኤልያስ ገና እንዳየኝ “አንተ አለህ እንዴ?” አለኝ እየሳቀ፡፡
“አለሁ”
“የሚገርምህ ነገር ሰሞኑን እየቦጨቅንህ ነበር” አለኝ፡፡
“ምን ብላችሁ?”
“ይሄ ልጅ የእስር ቤት በር ላይ እንዳይደርስ ገርፈው ነው እንዴ ያሰናበቱት እያልን”
“እኛ ነን የታሰርነው ወይስ እሱ እያልን ነበር” አለ አናንያ ቀበል አድርጎ፡፡
ሳቅን፡፡ ተሳሳቅን፡፡
“…እንዴት ነው ነገሩ ወፍራችሁ የለ እንዴ?”
“እንዴት አንወፍር ቁጭ አድርገው ይቀልቡናል” አለ ኤልያስ አሁንም እየሳቀ፡፡
“ይመሻል፤ ይነጋል፣ አንድ ክፍል ውስጥ ታጉረን አለን፤ ቀና ስትል ሰማይ ዝቅ ስትል ግድግዳ ታያለህ፡፡ …ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ መፅሃፍ የለ፤ መፅሔት የለ፤ ጋዜጣ የለ፡፡ ቁጭ አርገው ያደነዝኑናል፡፡ …” አለ አናንያ፡፡
“እዚህ ከገባችሁ ስንት ቀን ሆናችሁ?”
“41 ቀን! ….. 41 ቀን ሙሉ መረጃ የለ፤ ምን የለ፡፡ አንዲት በሶላር የምትሰራ ሬደዮ ነበረት፡፡ እሷንም ወሰዷት፡፡ 41 ቀን ሙሉ ሳይኮሎጂካል ቶርቸር በለው ….” ጮክ ብሎ፡፡ ከሚነግረኝ ነገር ከፊሉ አይሰማኝም፣ የመጠየቂያው ርቀት፤ …. መነጋገር ሳይሆን መደናቆር ዓይነት ነው የምናወራው፡፡
“…. ሰዎቹ ምን አላችሁ? ምርመራ ምናምን አለ?”
“የለም ….. ምንም ነገር የለም… ወይ አልከሰሱን፤ ወይ አልለቀቁን፤ ወይ ስልጠና ወደሚሉት አልወሰዱን ዝም ብለን ቀን እንቆጥራለን” አለኝ አናንያ፡፡
“በል የውሃ መያዣ ዕቃ አምጣ፤ የታሸገ ውሃ አናስገባም አሉን”
አናንያ ወደ ውስጥ ተመልሶ ባለ አምስት ደቂቃ ጀሪካን አመጣ፡፡ እኔ ውሃውን ለመገልበጥ ወደ ዋናው በር ስመለስ ፍፁም እና ኤልያስ ማውራት ቀጠሉ፡፡ ኤልያስ በዕንቁ መፅሔት ላይ ባቀረበው ዘገባ የተነሳ ስለተመሰረተበት ክስና ፍርድ ቤት ስለሚቀርብበት ቀጠሮ ነው የሚያወሩት፡፡ ለጠበቃው እንዲደውልለት ነው ኤልያስ የሚነግረው፡፡ ፍፁም የጠበቃውን ስልክ ጠየቀው፡፡
…. ከአፍታ በኋላ የጀሪካኑን ውሃ ለአናንያ አቀበልኩና በጥቂቱ ተተራርበን እየተሳሳቅን ተሰነባበትን፡፡….. ወደ ውጭ እየወጣን ሳለ “መንፈሳቸው ጠንካራ” ነው አልኩ ፍፁም ከኋላዬ ያለ መስሎኝ፡፡ መልስ ሳይሰጠኝ ሲቀር ወደኋላ ዞር አልኩ፡፡
ፍፁም ሁሉት ፖሊሶች መሃል ቆሟል፡፡ አንደኛው ፖሊስ እጅ ውስጥ የፍፁም ሞባይል ታየኝ፡፡
“ ቆይ …. ስልኩን ልክፈትልህ …” ይላል ፍፁም፡፡
“ምንድነው?”
“ነገርኩህ እኮ …. የጓደኛዬን ጠበቃ ስልክ ነው የያዝኩት”
“ፎቶውን ክፈተው?” አለ ፖሊሱ ሞባይሉን ለፍፁም እየዘረጋለት፡፡
የፎቶ ማህደሩን ገልጦ አሳየው፡፡
“እስቲ ይሄ ፎቶ …. ይሄ….. አይ የለም፡፡ ጨዋ ነህ ፎቶ አላነሳህም” አለ፡፡ “ባለፈው ጊዜ በስልክ ፎቶ አንስተው ፌስ ቡክ ላይ ለጥፈው ነበር፤ ስለዚህ በጥብቅ መቆጣጠር እንዳለብን ታዘናል” አለና ሞባይሉን መለሰለት፡፡ እናም የእስር ቤቱን ግቢ ለቀን ወጣን፡፡
በመጨረሻ፡-
አናንያ፣ ከኤልያስና ከዳንኤል ሺበሺ ጋር ስንሰነባበት አንድ ጥያቄ ሰንዝሬላቸው ነበር፡፡ “ለወዳጆቻችን (ለፌስቡክ) መልዕክት ካላችሁ?” የሚል፡፡
እንዲህ በልልን አሉኝ፡-
“እኛ እንዳለን አለን- እናንተ እንዴት ናችሁ”
ባሉኝ መሰረት እነሆ ሰላምታቸው ይድረሳችሁ፡፡

Filed in: Amharic