>
11:02 am - Monday November 29, 2021

20ኛው ኢትዮ አውስትራሊያ ቶርናመንት በድምቀት ተከናወነ!

20ኛው ኢትዮ አውስትራሊያ ቶርናመንት በድምቀት ተከናወነ!በአውስትራሊያ የተለያዩ ስቴቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በዓመት አንዴ የሚያገናኘው ኢትዮ-አውስትራሊያ ቶርናመንት ዘንድሮም ለ20ኛ ጊዜ በሜልበርን አዘጋጅነት በድምቀት ተከናውኗል።

https://youtu.be/XjgjUD_Z7hI

ከዲሴምበር 26 እስከ ዲሴምበር 31 ለስድስት ተከታታይ ቀናት ሲከናወን የቆየው አመታዊ ቶርናመንት አዘጋጇን ሜልበርንን ጨምሮ ሲድኒ፤ ብሪዝበንና ታስማኒያ ተሳትፈውበታል።

የእግር ኳስ ውድድርን ማእከል ያደረገው ይህ ቶርናመንት ከስፖርታዊ መዝናኛነቱ ባሻገር በመላው አውስትራሊያ ለሚገኘው ኢትዮጵያዊ ብቸኛው ዓመታዊ የመገናኛ መድረክ ሆኖ ቆይቷል።

ዘንድሮም ይኽው የኢትዮጵያዊያን መገናኛ መድረክ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት በዲሴምበር 26 በድምቀት ተጀምሮ ቅድሜ ዲሴምበር 31 በድምቀት ተጠናቋል።

የእግር ኳስ ውድድር

ሜልበርንን ጨምሮ ከአራቱም ስቴቶች የመጡ ቡድኖች ለስድስት ቀናት ባደረጉት ውድድር ታስማኒያ ፤ ብሪዝበን፤ እንዲሁም የሜልበርኖቹ አፍሪካን ታውንና ፤ሲቲቱ ሁመራ ለፍጻሜ ግማሽ አልፈው አርብ ዲሴምበር 30 ባደረጉት የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ሴቲቱ ሁመራ አፍሪካን ታውንን ብሪዝበን ታስማኒያን አሸንፈው ለፍጻሜ አልፈዋል።

በመዝጊያው ቀን በተደረገው የፍጻሜ ውድድር ብሪዝበንና ሴቲቱ ሁመራ ገጥመው በመደበኛው 90 ደቂቃ ሳይሸናነፉ 2 ለ 2 በመለያየታቸው፤ 30 ደቂቃ ተጨምሮ ተጫውተዋል።ይሁንና በተጨመረው ሰአትም ሊሸናነፉ ባለመቻላቸው ብርፍጹም ቅጣት ምት መለያየት ግድ ብሎ በተሰጠው አምስት አምስት ፍጹም ቅጣት ምት ሴቲቱ ሁመራ 4 ሲያስቆጥር ብሪዝበን 3 አስቆጥሮ በአጠቃላይ ውጤት ሴቲቱ ሁመራ 6 ለ 5 አሸንፎ የ20ኛው ቶርናመንት ሻምፒዎን ለመሆን በቅቷል። ሁለቱም ቡድኖች ዋንጫውን ለማንሳት በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት ያደረጉት ድንቅ እንቅስቃሴ ተመልካቹን ያረካ ነበር።

የኳስ ነገር ሆኖ አንዱ የግድ ማሸነፍ ስላለበት የሜልበርኑ ሴቲቱ ሁመራ ባደረገው ጠንካራ ፉክክር የዋንጫ ባለቤት ቢሆንም በወጣት የተገነባው የብሪዝበን ቡድንም ተስፋ በሚጣልባቸው ተጫዋቾቹ ባሳየው የጨዋታ ብቃት ከተመልካቹ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል።የብሪዝበን ቡድን መሪ አቶ ወርቅነህ ከውድድሩ ፍጻሜ በኋላ በሰጡን አጭር አስተያየት ቡድናቸው አመቱን ሙሉ ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ ዋንጫ ባለማንሳታቸው ቢቆጩም ወጣቶቹ ባሳዩት የጨዋታ ብቃት መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው ጠንካራ ቡድን ታስማኒያ ነበር። ታስማኒያ ለመጀመሪያ ግዜ እንደመሳተፉ ለፍጻሜ ግማሽ ማለፉ የቡድኑን ጥንካሬ አመላካች ነው።  የታስማኒያ ወጣቶችም እንደ ብሪዝበን ቡድን ሁሉ ድንቅ ችሎታቸውን አሳይተዋል።

በጥንካሬው የሚታወቀው የሲድኒ ቡድን አራት ያህል ተጫዋቾች ጎለውበት ያደረግው ፉክክር ቀላል የሚባል አልነበረም። ለቀጣዩ አመት እንደ ቀዳሚ አመታት ሁሉ ተሟልቶ በመምጣት ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ እምነታችን ነው።

የሜልበርኑ አፍሪካን ታውንም እንደ ጅምሩ መቀጠል ባይችልም ለተጋጣሚዎቹ ቀላል ሆኖ የቀረበ ቡድን አልነበረም።

የኢትዮጵያ ቀን ዝግጅት

የመዝጊያውን ቀን ቅዳሜ ለማድረግ ሲባል ከዚህ ቀደም ባሉ ዓመታት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይከናወን የነበረው ቶርናመንት ዘንድሮ አንድ ቀን ተጨምሮ ለስድስት ቀናት ተከናውኗል።

በዚሁ መሰረት የቶርናመንቱ ሶስተኛ ቀን ላይ የሚውለው “የኢትዮጵያዊያን ቀን” በዘንድሮው ዝግጅት አራተኛው ቀን ላይ ማለትም ዲሴምበር 29 ተከብሯል።

በኢትዮጵያዊያን ቀን ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን በሕጻናት ባህላዊ ጭፈራ የጀመረው የእለቱ መርሃ ግብር በመቀጠልም የግጥም ውድድር፤ የሰርከስ ትርዒት፤ የአዋቂዎች ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ፤ የስክስታ ውድድርና ታሪክ አስታዋሽ ድራማ ቀርቧል።
በተደረገው የግጥም ውድድር ከአምስት ያላነሱ ግጥሞች ቀርበው የወንድማገኘሁ አዲስ ግጥም አሸናፊ ሲሆን የሲሳይ ከበደ ግጥም ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል።

ወጣት ሲሳይ ታደሰም ያቀረበው መነባንብ የተመልካችን ቀልብ የገዛ ነበር።

ባጠቃላይ የዘንድሮውም የኢትዮጵያዊያን ቀን ባህል አስተዋዋቂ፤ አዝናኝና ከሁሉም በላይ ደግሞ አገርና ወገንን አስታዋሽ ሆኖ አልፏል።

የመዝጊያ ቀን ዝግጅት፦

ለፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ በሜልበርን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ሊያዝናና የመጣው አርቲስት ይሁኔ በላይና ልጁ የእለቱ የክብር እንግዳ ነበሩ።አርቲስት ይሁኔ በዝጊያው ዝግጅት ላይ ባደረገው አጠር ያለ ንግግር ስለ ተደረገለት ግብዣ አመስግኖ ይህን መሰሉ አመታዊ ቶርናመንት ኢትዮጵያዊያንን በማገናኘት ረገድ ያለውን ጠቀሜታ የራሱን አጋጣሚ ዋቢ በማድረግ ገልጿል። “በዚህ አመታዊ መገናኛ መድረክ ራሴም ተጠቃሚ ነበርኩና ጥቅሙን እመሰክራለሁ። ባለቤቴን የተዋወኳት በአሜሪካው አመታዊ ቶርናመት ላይ ነበር፡፤” በማለት ነበር ምስክርነቱት የሰጠው።

የዋንጫው ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ የቪክቶሪያ ኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲ ቲ ፕሬዝዳንት አቶ አዳሙ ተፈራ ለአሸናፊው ቡድን ዋንጫና ለተጫዋቾችችም ሜዳሊያ ሰጥተዋል።

አቶ አዳሙ ዋንጫውን ከሰጡ በኋላ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር፤ ከየስቴቱ የመጡ እንግዳ ተሳታፊዎችንና ለዚህ ቶርናመንት በስኬት መከናወን እገዛ ያደረጉትን የማህበረሰቡን አባላት አመስግነዋል።

በመጨረሻም ለ20ኛውን አመት ሻምፒዎን የእንኲን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ዝግጅቱ በስኬትና በሰላም በመቋጨቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ጠቅላላ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ማጠቃለያ

የዘንድሮው ቶርናመንት ከአምናው በእጅጉ የደመቀ ነበር።ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኮሚኒቲው ጽ/ቤት ተከስተው የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ግማሽ መንገድ አልፎ ያደረገው ጥረት ፍሬ አልባ መሆኑ ነው። ይህ መሆኑ የችግሩ መንስኤ በግለሰቦች መካከል የተከሰተ አለመግባባት ብቻ እንዳልሆነ ለኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ግልጽ አደረገው።  ትክክለኛው የችግሩ ምክንያት ከግለሰቦች አለመግባባትም የዘለለ ምናልባትም በአንድ ወይም ከዛ በላይ በሆኑ ምክንያቶች አንድነቱን ካለመፈለግ የሚመዘዝ ጫፍ የረገጠ አቋም እንደሆነ ይፋ ሆነ። ይህ ደግሞ ፦ ሰላም ወርዶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ አንድ ላይ ይሰባሰብ ዘንድ ጽኑ ፍላጎት የነበረውን አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አሳዘነ።እናም የኢትዮጵያዊያንን መሰባሰብ የሚፈልገው ማህበረሰብ በኮሚኒቲውና በባንዲራው ስር ተሰባሰበ።

ይኽው መሰባሰብ ለከርሞም ከዚህ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኮሚኒቲያችን አመራሮች ከወዲሁ ዝግጅትና ብሎም እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ እምነታች ነው።

አንድነት ጥንካሬ ነው!
አንድነትን የሚሻት ይዘልቃል የሚሸሻት ይወድቃል!

Filed in: Amharic