>
5:26 pm - Sunday September 15, 0707

የማለዳ ወግ...ለአዲሱን የፈረንጆች 2017 ዓመት ያደረሰኝ መንገድ [ነቢዩ ሲራክ]

ማስታወሻ ላንባቢዎቻችን :-  ሃገሩን ለቆ ከወጣ ጀመሮ  ባለበት ኣካባቢ ያለመታከት የወገኖቹን ኑሮ፣ስቃይ፣ ሁኔታ ወዘተ ያለመታከትና ያለመሰልቸት መረጃ በማቀበል ለወገኖቹ ድምጽ የሆነውን ጋዜጠኛ Nebiyu Sira ነብዩ ሲራክን ኢትዮ ሪፈረንስ የዓመቱ ምርጥ ብላዋለች።

* የተበደሉት በደሉ ሲከፋቸው …
* የበዳይ ወገኖች …
* መረጃ ቅበላው በ2017 ሲቀጥል….
* የእኔው መልዕክት …

nebiyu-sirak-2017የእኛ ያልሆነውን የፈረንጆች አዲስ 2017 ዓመተ ምህረት የራሳችን አድርጌ በመቁጠር በጥሩ መንፈስ ከዋዜማው እስከ መባቻው ተነቃቃቅቸ ተቀብዬዋለሁ … 🙂 ተነቃቅቸ የተቀበልኩትን 2017 አዲስ አመት ከመምጣቱ አስቀድሞ በተሸኘው 2016 ዓመተ ምህረት በበርካታ አሉታዊ ክስተቶች የተሞላ ነበር ፣ ከአመት አመት ቢለያይም በቅርብ ስላሳለፍነውና ትዝታው ስላልራቀ እንደሁ አንጃ ያለፈው አመት የከበደ ነበር ። ሀገራዊና አለም አቀፋዊ መልኩን ለጊዜው ገለል አድርገን ወደ ሚያገባን የስደት ህይዎት ሰደናተኩር ያለፈው ከቀደመው ባይከፋም ለእኔ ያሳለፍነው 2016 በልብ ሰባሪ የስደት ገጠኞች የተሞላ አመት ነበር 🙁 ከገጠመኞቹ መካከል ከታመሙና ከሞቱት በላይ ወደፊት የማቀርበው የቤተሰብ የአፋልጉኝ መልዕክት ሰላም የነሳኝ ፣ ውስጤን የሚያውከው ሆኖ ቀጥሏል 🙁

በዚሁ የእኔው የመረጃ ቅበላ መካከል ከምሰማ፣ ላስተናገድኳቸው ውስጥ የ2016 የማይረሱኝ ትዝታዎቸን ክፍል አንድልጠቃቅስ …

የተበደሉት በደሉ ሲከፋቸው …

የሚሰማ ባለመኖሩ ስደተኛው ከመንግስ ተወካዮችን ስራ ለምን አልሰረሰህም ብሎ ቢሞግተኝ አልፈርድበትም ። ባሳለፍነው አመት ከደረሱኝ መልዕክቶች መካከል ድጋፍ ማበረታቻውን እንዲህ ነው ብዬ አላደክማችሁም ፣ ስድብ ፣ ውረፋውን ግን ለማሳያነት ማስቃኘት እወዳለሁ …

ባንድ ወቅት ያለባትን ችግር አማክራኝ መፍትሔ ያልሰተጠኋት እህት የላከችልኝ መልዕክት ፍጹም አይረሳኝም ፣ እንዲህ ይላል ” አንተም ትሰማለህ ፣ ታያለህ ፣ ትናገራለህ መፍትሔ የለህም ፣ ልትረዳን አትችልም ፣ ዝም ብለህ ፎቶ እየለጠፍክ ለመታወቅ ታወራለህ ፣ ኢንባሲና ቆንስሎች ደግሞ ስልካቸውን አያነሱም ፣ ብንሄድ አይሰተናግዱንም ፣ እድል ገጥሞህ ቸግርክን ብትናገር አያማክሩህም ፣ አይረዱህም ፣ መፍትሔያቸው ” ከአሰሪሽ ጋር ተስማሚ ነው !” አንተም እነሱም ሁላችሁም አትረቡም ! እኛ በአረብ ቤት ጭንቅ ውስጥ ሆነን ከማናችሁም መፍትሔ ስለማናገኝ የራሳችን ምርጫ እንወስዳለን ፣ ወይ በችግሩ ራሳችን እናጠፋለን ወይ ወንጀል ሰርተን መያዝን እማራጭ እናደርጋለን ! ይህን ጊዜ ፎቶና ቪዲዮ እየለጠፋችሁ የአዞ እንባ ታለቅሳላችሁ ! መረጃውን ሸር እያላችሁ ትለጥፋላችሁ ፣ ምድረ ጉረኛ አስመሳይ ” ይላል … ይህ ከአንዲት የደረሰባት እንግልትና ችግሩ ካማረራት እህት ከደረሰኝ ስድብ ውስጥ ያወጣሁት የስድብ አንኳር ነው !

ሌላው ያስተናገድኩት ስድብ የደረሰኝ በደላላ ቪዛ ገዝታ ከመጣች በኋላ ለከፋ ወጭና እንግልት የተዳረገች እህት ናት ፣ መረጃዎችን እንደ ክብደታቸውና ይዞታቸው ፣ በዋናነት ለመፍትሔ ካላቸው ቅርበት አንጻር የሚደርሱኝን መረጃዎችን ሳስተናግድ እኔኑ ከመረጃ አቀባይ አውጥተው የመንግስት ተወካይ መብት አስከባሪ የሚያደርጉኝ ብዙ ናቸው ፣ በግል ፍላጎት ከስራ ጋር ደርቤ መረጃ ቅበላውን እንደምሰራ አይገባቸውም ፣ ለጉዳያቸው መፍትሔ ከሌለኝ ደግሞ ጭራሽ ይናደዱብኛል ። ጉዳያቸውን ባለመከታተል ፣ ባለ ማስፈጸም ፣ ባለ መርዳቴ የሰላ ወቀሳና ስድብ ያዘንቡብኛል ፣ ከቀናት በፊት የቪዛ እድዳት ወጭ ያንገላታት እህት እንዲህ ብላ ወርፋኛለች ” …ነቡዩ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው ፣ እዛ ላይ የተደረደራችሁት ሁሉ አስመሳዮች ናችሁ ፣ እኔ እንኳን በግሌ 10000 ጊዜ ጻፍኩልህ ፣ እርዳኝ ብየ የጻፍኩልህን ጀሮ ዳባ ልበስ ነው ያልከው ፣ ስላለፈው ታወራለህ ፣ እዚህ አጠገብህ ሁኘ መቸ ሰማክ ፣ መስሚያየ ጥጥ ነው ያልከው ፣ ጉረኛና ወሬ ብቻ መጀመሪያ ካጠገብህ ያለውን እርዳ ” ይላል … አሁንም መልስ የለኝም !

የበዳይ ወገኖች …

” … ስደተኞች እንዲህ ሆኑ ፣ ደመወዝ ተቀሙ ፣ ተደበደቡ ፣ ተደፈሩ ፣ እዚህ ወደቁ ፣ እዚህ ሞቱ ” ብለን ስጮህ … ሰው መረጃውን አንዱ ካንዱ እየተቀባበለ ማሰራጨት ፣ ከንፈር መምጠጥ ፣ ማልቀስ ፣ በእልህ በብስጭት መናገርን ከማንም ሰው የሚጠበቅ ነው … ይህ የእኛ የግፉአኑ ስደተኞች ውሎ አዳር ሆኖ ቀጥሏል 🙁 የመንግሰት ደጋፊ ነኝ ከሚለው የበዳይ ወገን የሚሰማው ቁጭት “ወገን ለምን ተበደለ? ” አለመሆኑ መታዘብ ሁሌም ያማል !

እኔና መሰሎቸ ” በስደት የወገን መከራ በዛ ፣ የመበት ጥበቃው ጎደለ !” ብለን ለምንጮኸውን ጩኸት ምላሻቸው ስድብና ማስፈራሪያው ያደረጉት የገዥው መንግስት ሎሌዎች መከረኛዋን ሃገር የብቻቸው አድርገው ” ወደ ሀገር አትገባትም ” ሲሉ በበሉበት ይጮሃሉ ። የተራው ጀሌ ሰራዊት ጉዳይ ሳይደንቀን ደሞዛቸውን በዶላር እያፈሱ በአራት አመት የዲፕሎማቲክ ስራ ጥሪት እየሰበሰቡ የወገናቸውን መከራ እየደፋፈኑ ፣ ለጩኸት አቤቱታው ” የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ ” ያሉት ተወካዮች ይታወሳሉ ፣ ዜጋው እየተቸገረ ፣ የመብት ጥበቃው ተዝረክርኮ ፣ ሰው በደሉ እየከፋ ከህዝብ ቀረጥ በሚሰበሰብና ደመወዝ ለቀሪ መቋቋሚያ እድሜያቸው ሀብት ንብረት በመሰብሰብ የተጠደመዱ ባለስልጣቻችን ዝምታም ያማል ። መብታችን አስከብሩ ስንላቸው ምላሻቸው በመታበይ ግልምጫ፣ ንቀት ውረፋ ነውና ልብን ጠልቆ በሀዘን ይጎዳል 🙁

ተወካዮቻችን መብት ማስከበሩ ጎድሏል ስንላቸው ” ብጥለው ገለበጠኝ ” እንዲሉ እኛኑ የችግሩ ምንጭ አድርገው ሲወነጅሉን ፈጣሪን አይፈሩም ” … ተጋነነ ፣ ዋሸ ፣ ለፖለቲካ ጥቅም መንግስትን ከማሳጣት ለማጥላላት መረጃ ያቀርበል ፣ የዜጎችን መከራ እየፈለፈለ የሚያጋልጥ ለግል ጥቅምና ዝና ነው የሚሰራ ፣ የግንቦት 7 ፣ የኦነግ …ተቃዋሚ አባል ነው !” … የሚለው ዥጉርጉር ውንጄላ ለእኛ የዜግነት ግልጋሎት ከተወካዮቻችን የሚሰጥ ሽልማት ነው ።

ሁሌም የምለውን ልድገመው መቸም የጨካኞችን ተንኮልና ጠለፋ ፈርቸ የወገኖቸን ድምጽ አላፍንም ፣ የምወዳቸው ቤተሰቦችና ልጆች አሉኝ ቢያጡኝና ባጣቸው እንጎዳለን ፣ ሰው ነኝና በወጥመዳቸው ላለመግባት እሞክራለሁ ፣ ከምንም በላይ ግን ሁሉንም በሚያይና ፍርድ በሚሰጥ አንድ ፈጣሪ አምናለሁና ጠባቂዬ እሱ ቸሩ መድሐኒአለም ነው !

መረጃ ቅበላው በ2017 ሲቀጥል…

በዚህ ሁሉ የህይዎት ጉዞ መካከል ጋሬጣውን አልፈን ዛሬን ደርሰናልና ተመስገን ነው ። ከዚህ ቀደም እንደነበረው ዛሬም ጉዞዬ ይቀጥላል ፣ በቀጣይ መረጃ ቅበላችን አቅም በፈቀደ መጠን ያየሁትን ፣ የታዘብኩትንና ” እህ ” የሰማሁትን ከድምጽ መረጃ ጋር ይዥ ለመቅረብ ተልሜያለሁ … ይህ በእለት ተእለቱ ኑሮ የሚከዎን ይሆናል !

ሩቅ ሲታሰብ ደግሞ ፣ ከኩባንያ ስራው ፣ ከመረጃ ቅበላውና ከቤተሰብ በተረፈችው ሰዓቴ የሞነጫጨርኩት ደጎስ ያለ መጽሐፍ ለፍጻሜ የሚበቃው በያዝነው አዲስ የፈረንጆች 2017 ነው ብዬ አስቤያለሁ ፣ የፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ በዚሁ ደጎስ ባለ መጽሐፊ ላለፉት 20 ዓመታት የባጀሁበትን የስደት ህይዎቴ በአካል ካየሁትን ተነስቸ ከእማኞች ከሰማሁትና አጣርቸ ማረጋገጥ ስለቻልኳቸው የስደት ህይዎት ትዝታዬ ደጎስ ባለው መጽሐፊ ታጭቋል ! ሀሳቤ በወራት ውስጥ ተሳክቶ በወራት ጊዜ ውስጥ በእጃችሁ እንዲገባ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለቴን በአዲሱ አመትም እገፋበታለሁ 🙂

የእኔው መልዕክት…

ከሁሉም አስቀድሞ የማስተላልፈው መልዕክት በአዲሱ ዓመት እንደቀደመው እንባ አባሽ ያጣ የመንግስት ተወካይ ያጣ ስደተኛ ወገኔን ሁለንተናዊ ህይዎት የምዳስስበት እንደሆነ ይቀጥላል ። ዛሬም የአዲሱ አመጥ ምኞቴ ከሁሉም በላይ ለሰብዕና ቅድሚያ እንስጥ ነው ። ስላለፈው ሳይሆን አሁን እየሆንነ ስላለው እናብር ። ሃገር ማለት ፣ ዜጋው ሰው ነው ። “ሃገራችን ህዝባችን እንወዳለን !” ካልን ፣ ሃገር ዜጋን ስለመውደድ ከመስበክ ማለፍ አለብን ! ዘር ፣ ቀለም ፣ የፖለቲ ካ ርዕዮት ፣ ሃይማኖት ሳይለያየን ፣ ችግር መከራውን ለመታደግ አንድ እንሁን ። ብሩህ መጻኤ ህይወት ለማየት አንድ በሚያደርገን እንስማማ ፣ መለያየትና መጠላላቱ አልበጀንምና ይብቃን ። ለሃገር ወገን ፍቅር ፣ ለሰብዕና በአንድነት እናብር !

በመጨረሻም እብራችሁኝ እዚህ ለደረሳችሁ ፣ ለጠላት ወደጆቸ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ ! ስላደረጋችሁልኝ ድጋፍ ፣ ስላበረታታችሁኝ ፣ ወቅሳሁ ስላጠነከራችሁኝ ለሁላችሁም ምስጋናዬ ወደር የለውም !
ቸር ይግጠመን !

ነቢዩ ሲራክ
ታህሣሥ 22 ቀን 2009
1/1/2017

Filed in: Amharic