>
5:13 pm - Wednesday April 19, 2609

ነፃ ነፃነት?....

ደምስ ሰይፉ
“ነፃ ሆነን ብንፈጠርም በየሄድንበት እንደታሰርን ነው” ይላል ሩሶ… “Man is born free, and everywhere he is in chains. One man thinks himself the master of others, but remains more of a slave than they are.” ~ Jean Jacques Rousseau … ይህን ጥቅስ ለረጅም ጊዜ አብሰልስዬዋለሁ… በርከት ላሉ ጊዜያትም በነፃነት የትርጉም ፈለጌ ላይ ተጋድሞ ማለፊያ ነስቶኝ ያውቃል… ‘ነፃ ነኝ’ ብዬ ባሰብኩ ቁጥር ድንገት ከች ይልና የተተበተብኩበትን ድር ያሳየኛል… ምንም ጥያቄ የለውም – አባባሉ እውነት ነው… እንዲያውም በነፃነት ትርጓሜያችን፣ በአማናዊው ነፃነትና በኑሮአችን መሃል ያለውን ተምታቶሽ ሰከን ብለን እንድናይ የሚረዳን ታዛም ይመስለኛል…
~~~
ስለ ነፃ ንግግር፣ ስለ ነፃ ጽሑፍ፣ ስለ ነፃ አስተሳሰብ… ወዘተ ከሚሰብከው ዘመነኛ ብያኔ በፊትም ሆነ አሁን ነፃነት አለ… ልዩነቱ የትርጓሜና ግንዛቤ ብቻ ይመሰለኛል… ትርጉምና አረዳዳችን ከግለሰባዊ ተሞክሮአችን ደጃፍ ሳይሆን ከውጪያዊው ቅኝት አፍ ስለሚቀዳ እውነቱና ትርክቱ ሳይገናኝ ይኖራል… እርግጥ ነፃነትም እንደበርካታዎቹ እሳቤዎች የግለሰቦች መረዳት ጥላ ስለሚያጠላበት ወጥ ትርጓሜ እንዲኖረው አይጠበቅም… የትርጉም ማጠንጠኛው ውጪያዊ ጫና ላይ ሲንጠለጠል ግን ነፃነት ‘ነፃ’ መሆኑ ይቀራል…
~~~
የምንም ነገር ትርጉም ‘ይህ ብቻ ነው’ በሚል ዶግማ ውስጥ ሲታጠር ነፃነት ያሳጣል… ዶግማዊነት አጥር አበጅቶ ከመስክ እውነት መፋታትን ያነግሳል… ልክ ‘ጉድጓድ ውስጥ ተቀምጦ የጉድጓዱ አፍ ከሚፈቅደው ስፋት በላይ ሰማዩን እንዳለማዋቅ’… ራስህን ወደ አንድ አጥር ከወረወርክ በኋላ ከአጥሩ ማዶ ላለው ኑረት እውቅና ያለመስጠት ንፍገት እንጂ ‘እዚያስ ቤት ምን አለ’ የሚል በጎነት አይስተዋልብህም… እዚህም ነፃነት አለ…
~~~
የነፃ መሆን አለመሆን ነገር አወዛጋቢ ነው… ለአንተ ነፃነት የሆነ ነገር ለሌላው ‘መታሰር’ ሊሆን ይችላል… ያንቺ የባርነት ጥግ ለሌላዋ የነፃነት ጠገግ ሊሆን ይችላል… አንዳንዴ ነፃ ወጣን ባልንበት ነገር ተመስጠን የነገርየው ሎሌ የመሆን ዕጣ ሊወድቅብን ይችላል…
የሆነው ሁሉ ሆኖ ግን፡-
[ከማሰብ ነፃ አይደለንም]… ማሰብን ትልቅ ቁምነገር የሚያደርገው ማሕበረሰባዊ ግንዛቤያችን ሰውን ከማሽን ለይቶ አያይም… በቀን ውስጥ ከሰባ ሺህ በላይ የሃሳብ ሰበዝ አዕምሮአችንን ሲያባትል እንደሚውል ስናስብና ስንቱን ሃሳብ ፈቅደን እንደምናስብ ስንጠይቅ የነፃነት ነገር ይገባናል… የሃሳብ ፈለጋችን ሲሶው እንኳ በገዛ ፈቃዳችን አይተለምም… እግረ አዕምሮአችን በደረሰበት የምንደርስ እንጂ የፈቀድነውን የምናስስ አይደለንም… ሰው በትክክል የሃሳብ ማሽኑ ባሪያ ነው… በአዕምሮችን ላይ እንሰለጥን ዘንድ ገና ነፃ አልወጣንም!!… ነፃ ከሆንክ አዕምሮህን ፀጥ አድርገው…
~~~
[ከስሜት ነፃ አልወጣንም]… በሚግለበለብ የስሜት እሳትና ከስሎ ሲያበቃ በሚያምድ ፀፀት መሃል ስንታኘክ የምንውለው ለዚህ ነው… ለበርካታዎቹ የስሜት ጥያቄዎቻችንን የእምቢታ ድፍረት የለንም… ስሜት ግዘፍ ነስቶ ከክፉ ግብረ መልሱ ጋር ሲያጋትረን ነው ልክ ያለመሆን እምነት ሆድ ሆዳችንን የሚበላው… ስሜቱን በሚያስተናግደውና በስሜቱ ምላሽ በሚቆጨው እኔነት መሃል ልዩነት ኖሮ አይደለም ሰበብና ድርጊት የተለያየ አቀባበል የቆያቸው – እኛ በስሜት ላይ ስላልሰለጠንን እንጂ… ከስሜቱ አንድ ስንዝር የቀደመ ሰው ከስሜቱ ምስ ከሚለጥቁ እልፍ ኪሎሜትሮች ድካም ይድናል…
~~~
[ከመፈለግ ነፃ አይደለንም]… ከእጅህ ያለው አልማዝ ቀሎ የሌለህ የመሰለህ ሸክላ ከረቀቀ በፍላጎት ባርነት ውስጥ ነህ… እስኪኖርህ ልብህን አቁሞት የኖረህለት ያነሰብህ ነገር ካለ ችግር አለ… እርካታ ስትፈልገው የምትኖረው እንጂ የሚኖርህ አይሆንም… ባለህ ደስታን ሳትፈጥር በሌለህ መኖር ደስታህ ሊከሰት አይችልም… ደስታህ በፈላጊነትህ ላይ ባለህ ስልጣን እንጂ በአገኘሁ ባይነትህ ማግስት ውስጥ ሊኖር አይችልም… ስግብግብነት ጉድለት በሚመስለው ነገር ላይ የሚያተኩር ሰው ሕመም ሲሆን እርካታ ምልዓቱን ማየት የሚችል ሰው ትርፍ ነው…
~~~
[ከፍርድ ነፃ አይደለንም]… በየዕለቱ ለሚገጥሙን ሁነቶች ሁሉ ሚዛን እናኖራለን… ልክ እንሰይማለን… ስም እናወጣለን… ለምናየው፣ ለምንሰማው፣ ለምንዳስሰው… የስሜት ሕዋሳቶቻችን ለሚያቀብሉን ነገር ሁሉ ደረጃ እንመድባለን፣ ጎራ እንፈጥራለን፣ ፈርጅ እናበጃለን… የሚዛን ማበጂያችን ምንጩ ደግሞ የተቃኘንበት አውድ ነው… ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ ሚዲያ፣ ጓደኛ፣ ስርዓት… ወዘተ… ልክህ ሲያንስብህ ልክ ታዛባለህ… ልኬት ሲገባህ ግን ልክ መስጠት ታቆማለህ…
~~~
[ከነኝታ ነፃ አይደለንም]… ‘እንዲህ ነኝ’ – ‘እንዲያ ነኝ’ ስትል የምትውለው ከነኝታህ ተጽዕኖ መላቀቅ ባለመቻልህ ነው… ነኝታህ ከመሆንታህ ይበልጥብሃል… የሆንከው ግን ነኝ ከምትለው የማይናጸር ጥልቅ ነው… ነኝታህ የመሆንታህን ብርሃን ያደበዝዛል… ነኝታህ ከጎሳህ፣ ከስራህ፣ ከችሎታህ፣ ከሃብትህ፣ ሐይማኖትህ… ወዘተ ይመነጫል… መሆንታህ ግና የአማናዊው ተፈጥሮህ መሰረት ነው… The essence of who you are in the deepest level. አግዮስ፣ ንዑድ፣ ክቡር፣ ጽሩይ… ነኝ የምትለውን ሁሉ አውልቀህ ብትጥል ምን የሚቀር ይመስልሃል?… ምንም!… መሆንታው ላይ የቆመ ግና ያልሆነው ስለሌለ ነኝ የሚለው አይኖረውም… የሚያጣው ስለሌለው ባዶነት አይሰማውም…
~~~
[ከትርጉም ነፃ አይደለንም]… በኑረት ሃዲድ ላይ እርምጃዎቻችንን የሚወስኑ ትርጉማ-ትርጉሞችን የያዘ ኮሮጆ አለን… ለነገሮች የሚኖረን ምላሽ ትርጉማችን ላይ ይንጠለጠላል… በትክክል ከትርጉም እስራት ነፃ አይደለንም… ለሕይወት ያለህ ትርጉም ነው – የእልፍ በረከቷን ጓዳ አልያም የንፉግነቷን ጎድጓዳ የሚያሳይህ… ለፍቅር ያለህ ትርጉም ነው – የዓይናማነቱን ድምቀት አልያም የእውርነቱን ጽልመት የሚያቆይህ… ለስራ ያለህ ትርጉም ነው – የወዝህን ሲሳይ አልያም የሌሎችን ፍሬ ብካይ የሚያስመኝህ… ሌላውም ሁሉ እንዲሁ ነው… ትርጉም ከሰጠህ በኋላ ሌላ ተዓምር መጠበቅ የለብህም… መዝገቡን ከዘጋህ በኋላ ሌላ ምዕራፍ ሊኖር አይችልም… ትርጉም ያበጀህለት ታስረሃል – ነገርህንም ቋጥረሃል… ከልብ ደስተኛ የሆነ አንድ ሰው ታውቅ እንደሁ ለነገሮች ያለውን አተያይ ጠይቀው… ወይ የትርጉም ሜኑ የለውም – ሁሉን እንዳመጣጡ ተቀብሎ ይኖራል… አልያም በጎ በጎዎቹ ትርጉሞች የኑረቱ አካል ናቸው…
~~~
[ከቂም ነፃ አይደለንም]… ስለት የቆረጠው ጣትህ ደም እስከመች ነው ይፈስ ዘንድ የምትተወው?… ነገር የጓጎጠው ልብህስ ገላ እስከመች ነው ይቆስል ዘንድ ችላ የምትለው?… የጣትህ ደም ፍሰት አንተ ችላ ብትለውም በደምህ ውስጥ ያሉት ፕላትሌትስ ከየቦታው ተጠራርተው በሚሰሩት ግድብ /Blood clotting/ ይቋረጣል… የልብህ ቁስል ግን ፈቅደህ በምትሰጠው ይቅርታ እንጂ በሌላ መንገድ አይጠግም… ይቅርታ ከሚደረግለት በላይ ለአድራጊው የሚሰጠው ሰላም ትልቅ ነው… ቂመኛ ስትሆን በዳዬ ያልከውን ባየህ አልያም ባሰብክ ቁጥር በደሉ ከደረሰብህ የአንድ ጊዜ ሁነት በላይ ደጋግመህ ትታመማለህ… ይቅር ስትል ግና ከመጀመሪያው ቁስልም ትፈወሳለህ… ያልኖርክበትን ዘመን ጠቅሰህ የለውጥን እርሾ ነው የክፋትን ቁርሾ የምታሻትተው?… የትናንትን በደል ቆጥረህ በግመል ሽንት ነው በቀስት አቅጣጫ ጉዞህን የምትቃኘው?… ቅድመ አያትህ ለአያትህ ያሻገረውን ክፋት ትተህ ጥበቡን ቀምር፣ አያትህ ለአባትህ የተወውን ጠብመንጃ ጥለህ ሞፈሩን አንሳ፣ ከአባትህ የፍቅር ታሪክ ለልጅህ ጦማር አዘጋጅ… ‘ስታልፍ’ የሚነበበው ታሪክህ እርሱ ብቻ ነውና…
~~~
ከጥበቃ ነፃ አይደለንም… በአገኘዋለሁ ተስፋ ውስጥ እንደታሰርን አለን… በይመጣል ጥበቃ ውስጥ እንደታበትን አለን… ለኑረት አንዳች አበርክቶ የሌለው ሁሉ ቁጭ ብሎ ይጠብቃል… ከሰማይ ይጠብቃል… ከምድር ይጠብቃል… ከወዳጁ ይጠብቃል… ከመንግስት ይጠብቃል… ከጥበቃ ነፃ ስላይደለ ግምቱ ፍርሽ ሲሆንበት ይበሳጫል… ከሌሎች የሚጠበቀውን ልክ አበጅቶ “ከአንተ አይጠበቅም” ይላል… ደግሞ ወዲህ የሚጠብቀውን የማያውቅም አለ… ሳሙኤል ቤኬት አንድ ጊዜ “Waiting for Godot” የሚል አብሰርድ ድራማ ጽፎ ነበር… በድራማው ውስጥ የሚታዩት ሁለት ገጸባሕሪያት ካሉበት ጭንቅ ያወጣቸው ዘንድ In the middle of nowhere ቆመው የማያውቁትን አንድ ነገር ሲጠብቁ ይታያል… ተጠባቂው ሲመጣ ባይታይም እነርሱ ግን ጥበቃቸውን አያቋርጡም… አንደኛው ገጸባሕሪ በመሰላቸት “Nothing happens, nobody comes, nobody goes, it’s awful!” ይላል… ያም ሆኖ ቀረ ብለው አይንቀሳቀሱም… ምክንያቱም ጎዶትን እየጠበቁ ነው…
ESTRAGON – Let’s go.
VLADIMIR – We can’t.
ESTRAGON – Why not?
VLADIMIR – We’re waiting for Godot. … የድራማው ፀሐፊ አንድ ጊዜ በጋዜጠኛ ተጠየቀ፡ “ጎዶት ማን ነው?”… ቤኬት መለሰ፡ “እኔም አላውቀውም”

ማድረግ የምትችለውን ሁሉ ማድረግ ነፃነት አይደለም… ከአድራጊነትህ ጋር ኃላፊነት አለ… ተግባርህ የሌሎችን ጉዳት ካስከተለ ከፀፀት አትነፃም… እንዳሻህ መናገር ወይም መፃፍ ነፃነት አይደለም… ቃልህ የአብሮ መኖር ሚዛን ካዛባ አልያም ጎራ ለይቶ ደም ካቃባ ከተጠያቂነት አትድንም… ነፃነት ብቻነትም አይደለም… ኑረት ለሌሎች ባለን አበርክቶት እንጂ በራስ ደሴት ጡዘት ከቴም አትሞላም… ነፃነት እንደልቡ መኖር አይደለም… እንደ ደንቡ መመላለስ እንጂ…

እህስ…
ኦርጅናሌው ነፃነት የልጅነት ንጽሕና ይመስለኛል!! እንደልጅ ልጅነት – እንደ ሕፃን ‘ጅልነት’ የመኖር ድፍረት… የልጅነት ዓለም ከራሱ ከ’ነፃነትም’ ነፃ ያወጣል… ነፃ ነኝ ከሚለው ባዶ እምነትም ጭምር… ልጅነት ነፃነትን ይኖራታል እንጂ አያነፃጽራትም… ነፃ ነኝ አይደለሁም ውዝግብ የሌለበት ኑረት ነው ‘ነፃ ነፃነት’… የሚኖሩት ግን የማያስቡት… ከራስ ውስጥ የሚወልዱት… ፈቅዶ የሚቸርህ አልያም ከፍቶ የሚነሳህ የሌለበት እውነት ነው ነፃነት… ይህ ነፃነት ከሰንሰለት ስርም ሆነ ከግዞት መሃል ሆነህ ልታጣጥመው ትችላለህ… ከደቋሽ ክንድና አደፍራሽ ሁከት ሳትርቅም ልትኖረው ትችላለህ… ምክንያቱም ‘ነፃ’ ነፃነት ነውና…

ብዙ ፍቅር!!

ሰላም!!

Filed in: Amharic