>
5:30 am - Tuesday September 28, 2021

ተቋማዊ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትን ለማስቆም ምን ይደረግ? [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

BefeQadu Z. Hailuአንዳንዴ፣ መንግሥትን በሰብኣዊ መብቶች ጥሰቱ የምንወቅሰው ሰዎች እኛ እራሳችን እንዴት እንደምናስከብረው የምናውቅ አይመስለኝም። ታሪካችን እንደሚያረዳን እንደ ማዕከላዊ ያሉ ተቋማት ስርዓቱ ሲቀያየር ተቋማቱ ግን ሥራቸውን እና አሠራራቸውን ይቀጥላሉ። አንዳንዴ ደግሞ ከላይኛው የሥልጣን እርከን ላይ ያሉት ሰዎች የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቱን ባይፈልጉት እንኳ ከታች ያሉትን ሰዎች መቆጣጠሪያ ተቋማዊ አሠራር ስለሌለ፣ ማስቆም የማይችሉ ይመስለኛል። (ባሕላችን በአካላዊ ጥቃት እንደሚያምን መዘ:ንጋትም የለበትም። እናቶች የገዛ ልጆቻቸውን ከጥፋት ለማረም በበርበሬ የሚያጥኑበት አገር ውስጥ ነው ያለነው።)

ስለተቋማት ስ:ናገር እንደ ኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያሉትን ማለቴ አይደለም። የነርሱን አስፈላጊነት አሳንሼ አልመለከተውም። እነዚህ ተቋማት (በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚጠመዘዙ መሆናቸውን ለዚህ ጽሑፍ እንዘንጋውና) የመብቶች ጥሰትን ለመመርመር ፍላጎቱ ቢኖራቸው እንኳ ጥሰቶቹ ለሚፈፀምባቸው ቦታዎች ቀጥተኛ ተዳራሽነት የላቸውም። የዚህች አነስተኛ ምክር ሐሳብ ዓላማም፣ ‘መሬት የወረደ ቁጥጥር እንዴት ይደረግ?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሞከር ነው።

የአደባባይ ሰልፎችን (ስብሰባዎችን) ለመበተን ከሚደረጉ የፖሊስ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪ የሚከተሉት ሦስት የሰብኣዊ መብቶችን ጥሰት ተቋማዊ የሚያደርጉ አካላት አሉ።

፩ኛ. የፖሊስ ማቆያ ጣቢያዎች

የፖሊስ ጣቢያዎች አብዛኛዎቹ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች የሚደርሱባቸው ቦታዎች ናቸው። ጥሰቱ የሚጀምረው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉባት ደቂቃ ጀምሮ ቢሆንም በምርመራ ጊዜም ይቀጥላል። ‘የሚራንዳ’ ሕግ የሚባለው በሕገ መንግሥታችን (አንቀፅ 19/2) የተቀመጠው እስረኞችን ባለማወቅ በሕግ ፊት ስህተት ከመሥራት እንዲቆጠቡ የሚረዳቸው መብታቸው በፖሊስ ተከብሮ አያውቅም። በዚያ ላይ፣ ምርመራዎች በብዛት ኃይል የቀላቀሉ ናቸው።

ማዕከላዊን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ክስ ያልተመሠረተባቸው የማቆያ ጣቢያዎች ለሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ክፍት አይደሉም። ማቆያ ጣቢያዎቹ እስረኞች ተነጥለው የሚቆዩባቸው ቀዝቃዛ፣ ጨለማ ቤቶች አሏቸው። አንዳንዶቹ ሰቅጣጭ ቅጣት (ቶርቸር) መፈፀሚያ ቁሳቁስ አላቸው። ሌሎቹ ደግሞ በመንግሥት በጀት ይህንኑ መፈፀሚያ ይገዛሉ።

የፖሊስ ምርመራዎች ‘ጠበቃዬን ሳላማክር አልናገርም’ የማለት መብትን በፍፁም አያከብሩም። እንደ ማዕከላዊ ያሉት ጣቢያዊች ደግሞ ጭራሹኑ ለተወሰነ ግዜ (መሠረታዊ ምርመራ እስኪጨርሱ) ጠበቆች ደንበኞቻቸውን እንዲጎበኙ ወይም ቤተሰቦች እስረኞችን እንዲጠይቁ አይፈቅዱም። ይህ በሕግ አግባብ ክልክል ነው። እስረኞቹ ብዙ ግዜ ይሄንን ቅሬታ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ያሰማሉ። አንዳንዴ ፖሊስ አቤቱታውን ያስተባብላል። ሌላ ጊዜ ፖሊስ ከድርጊቱ እንዲታረም ፍርድ ቤት ያ:ዛል። ነገር ግን ፍርድ ቤቶቹ በቅሬታው ላይ ምርመራ እንዲካሔድ አ:ዘው የመብት ጥሰቱን ባደረሱት አካላት ላይ የእርምት እርምጃ ግን የወሰዱባቸው ጊዜያት የሉም።

እንደመፍትሔ፣ የታሳሪዎች የመብቶች ጥሰት ቅሬታዎች የጥሰት ፈፃሚዎቹን ተጠያቂ ማድረግ የሚቻልበት አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል። የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፤

ሀ) ብዙዎቹ የፖለቲከኛ እስረኞች በፍርድ ቤት “ጥፋተኛ” የሚባሉት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ተገደው በሚናዘዙት ቃላቸው መሠረት ነው። ተጠርጣሪዎች መደበኛ ክስ ተመሥርቶባቸው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የሰጡት ቃል በኃይል መሆን አለመሆኑን የማረጋገጥ ሸክሙን ተጠርጣሪዎቹ ላይ ይጥላል። ይህንን ማረጋገጥ ለተጠርጣሪዎቹ በጣም ከባድ የሚሆነው ፖሊሶች የመብቶች ጥሰቱን የሚፈፅሙት በምስክር ፊት ባለመሆኑ ነው። ቢሆንም ግን፣ የተጠርጣሪዎቹ ቃል ብዙ ጊዜ የሐሰት ኑዛዜ ነው። እንዲህ ዓይነት ቅሬታዎች በተጠርጣሪዎች በቀረቡ ጊዜ (ሕጉ በሚያዘው መሠረት) ቃሉን ውድቅ ማድረግ ሞራላዊም፣ ሕጋዊም ፍትሕ ነው።

ለ) በአሁኑ አሠራር፣ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለፖሊስ የሰጠው ቃል በኃይል ተገዶ መሆኑን ማረጋገጥ ከቻለ፣ ዳኞች የሚወስዱት ብቸኛ እርምጃ ቃሉን ከማስረጃነት ውድቅ ማድረግ ነው። ነገር ግን፣ ይህንን የመብት ጥሰት ባደረጉት አካላት ላይ የእርምት እርምጃ ሲወስዱ አይቼ አላውቅም። የመብቶች ጥሰትን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከተፈለገ ግን ዳኞች ተጠርጣሪውን በኃይል የሐሰት ቃል እንዲሰጥ ያደረገው ግለሰብ ወይም ተቋም ተጠርቶ ተጠያቂ እንዲሆን ማዘዝ መቻል አለባቸው። ለዚህም የመብት ጥሰት ቅሬታዎች በገለልተኛ ወገን ተጣርተው፣ መብት ጣሺዎቹ ለፍርድ የሚቀርቡበትን አሠራር አስገዳጅ የሚያደርግ አዋጅ መውጣት አለበት።

፪ኛ. የምሥጢር ምርመራ ማዕከላት

እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው የፖለቲካ እስረኞች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የሚወሰዱባቸው የምሥጢር እስር ቤቶች አሉ። እነዚህ እስር ቤቶች በይፋ አይታወቁም። እስረኞቹ ወደ ምሥጢራዊ ማዕከላቱ ሲወሰዱ ዓይናቸው ተሸፍኖ ነው። ከአንድ ወይም ሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ እነዚህ እስረኞች እንዳመጣጣቸው ወደ ማዕከላዊ ይዛወራሉ። የማዕከላዊ ፖሊሶች በ48 ሰዐት ውስጥ ፍርድ ቤት ያቀርቧቸዋል። እስረኞቹ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ቅሬታ ካቀረቡ ፖሊሶቹ ‘ትላንት ገና ነው የታሰረ[ች]ው’ በማለት ያሳ:ጧቸዋል።

የምሥጢር ምርመራ ማዕከላቱ ከሁሉም የከፋ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የሚፈፀምባቸው ቦታዎች ናቸው። ፖሊስ የምሥጢራዊ እስር ቤቶቹን መኖር ቢክድም መኖራቸውን ማረጋገጥ ከባድ አይደለም። ተጠርጣሪዎቹ የተሰወሩበትን ቀን የሚመሰክሩ ወዳጅ ዘመዶች አሏቸው። እራሳቸውም በምሥጢራዊ ማቆያዎች ያሳለፉትን ጊዜ መናገር ይችላሉ። ከምሥጢራዊ ማቆያዎቹ ወደ ማዕከላዊ የተዛወሩበትን ጊዜ በሰነድ በማስደገፍ ማስተያየት ይቻላል።

ስለዚህ መፍትሔው እንዲህ ዓይነቶቹን ምሥጢራዊ ምርመራ ማዕከላትን በአዋጅ በመከልከል፣ ቅሬታዎች በታሳሪዎች በቀረቡ ቁጥር ተጣርቶ ማዕከላቱ እንዲዘጉ እና መጠየቅ የሚገባቸው አካላት ሕግ ፊት እንዲቀርቡ የሚያስገድድ እና ለዳኞች ሥልጣን የሚሰጥ አዋጅ ማውጣት። (በነገራችን ላይ፣ ብዙዎቹ ዳኞች ፍርድ ቤት ውስጥ በሚደመጡ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ቅሬታዎች ተሰላችተዋል። ለብዙዎቹ የመሰላቸት ምንጭ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ማወቃቸው ነው። ጉዳዩን ተከታትሎ፣ ጣሺዎቹን ለተጠያቂነት ማብቃት የሚችሉበት አሠራር /ተቋማዊ ባሕል/ የለም። ሌሎቹ ደግሞ ብዙ ጉዳዮችን መመልከት ስለሚያባትላቸው የግለሰቦች የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች የማያሳስባቸው ዓይነት ሆነዋል። ቀሪዎቹ፣ ስርዓቱን ወይ ይፈሩታል፣ ወይም ደግሞ በሹመት ጉጉት ባለሥልጣናቱን ለማስደሰት ይፈልጋሉ።)

፫ኛ. ማረሚያ ቤቶች

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ወኅኒ ቤቶች ለአስተዳደር ምቾት በዞኖች የተከፋፈሉ ናቸው። በየዞኑ ያሉ እስረኞች ከዞን ተጠሪዎች (አስተዳደሮች) ጋር በቀጥታ መገናኘት ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ የዞን ተጠሪ አባላት ራሳቸው ናቸው ‘በማይታዘዙ ወይም የስርዓት መተላላፍ ባደረጉ’ እስረኞች ላይ እንደ ድብደባ ያሉ የመብቶች ጥሰት የሚያደርሱት። በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እና የሚንስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ መሠረት በማረሚያ ቤት ውስጥ ጥፋት የሠራ እስረኛ ሰብኣዊ መብቱ ሳይጣስ እዚያው በሚቋቋም ኮሚቴ የሚዳኝበት አግባብ አለ።

ለዚህ መፍትሔ በያንዳንዱ ዞን እስረኞች የዞን ተጠሪዎችን ፈቃድ ሳይጠይቁ በቀጥታ የሚጎበኙት የሰብኣዊ መብቶች ጉዳይ ቢሮ ማቋቋም ነው። የቢሮዎቹ ተጠሪነት ደግሞ በቀጥታ ለኢሰመኮ ይሆናል።

በአሁኑ ጊዜ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ‘ዘመናዊ’ ወኅኒ ቤቶችን በተለያዩ ቦታዎች እያስገነባ ነው። አዳዲሶቹ ወኅኒ ቤቶች አጥፊዎችን ማጎሪያ ብቻ መሆን የለባቸውም። አጥፊዎችን የማረሚያ ተቋሞች እንዲሆኑ ተደርገው መቀረፅ እና መገንባት ያስፈልጋል።

ለመደምደም ያክል፣ ተቋማዊ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትን ይቀንሳሉ በሚል የጠቆምኳቸው ምክር ሐሳቦች ሲጠቃለሉ፦

፩) ተጠርጣሪዎች በፖሊስ እጅ ላይ እያሉ የሰጡትን ቃል እውነተኝነት የማረጋገጥ ሸክሙ በዐቃቢ ሕጉ ላይ እንዲሆን ማድረግ፤

፪) ዳኞች ተጠርጣሪዎች በሚያቀርቡት ቅሬታ ላይ ተመሥርተው በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ፣ አጥፊዎች ተጠይቀው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችል ትዕዛዝ የማሳለፍ ሥልጣን በአዋጅ እንዲሰጣቸው ማድረግ፤

፫) ምሥጢራዊ የእስር/ምርመራ ማዕከላት እንዳይኖሩ በሕግ ማገድ፤

፬) እስረኞች በቀጥታ መጎብኘት የሚችሏቸው እና ተጠሪነታቸው ለኢሰመኮ የሆኑ የሰብኣዊ መብቶች ጉዳይ ቢሮዎች በየማረሚያ ቤቶቹ ዞኖች ውስጥ እንዲቋቋሙ ማድረግ።

(ፎቶ፤ በመገንባት ላይ ያለው የዝዋይ ፌዴራል ማረሚያ ቤት)

(Link for English: http://befeqe.blogspot.com/…/how-to-decrease-institutionali…)

Filed in: Amharic