>
5:13 pm - Wednesday April 19, 2215

ነገረ-ቴዲ አፍሮ [ኢ.ሚ.ፎ]

Tedy Afro Afrcan prideኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ሲባረሩ የልጅነት ጓደኞቻችንን አቅፈን እቃቸውን አብረን አሻሽጠን አልቅሰናል:: ያኔ ላቅመ ፖለቲካ ላልደርሰነው ለብዙወቻችን “ኤርትራ ትገንጠል” ብለው ድምጽ ከሰጡ ወላጆቻቸው ይልቅ ሜካፕ ያልደረሰበት የነነቢያት ውበት ፤ የነርሻን የልጅነት ቁንጅና ፤ የነስምኦን አብዶ ፤ የነመዋእል ተንኮል ፤ የነሚካኤል ጅልነት ዘላለም ከልባችን የማይወጣ የልጅነት ትዝታችን ነው:: ኋላ ላይ ለሻእቢያ ብር ታዋጣ እንደነበር የተወራው ለተተንሳይ እንኳን አሮን ልጇ የፍጥር ጀግናችን ነበር:: በባዶ እግሯ ስትሮጥ ጀርባዋ ላይ የሚጨፍረውን ጸጉሯን እያዩ ከነቢያት ጋር ሌባና ፖሊስ መጫወትን የመሰለ ደስታስ የት ነበረ??!! “መሬቱን እንጂ ሰውን አትወዱትም” ሲሉን ፤ የኖርነው ሃቅ ፤ የነ አወት የነ ልዋም ፊት አይናችን ስር እየቆመ በከሳሾቻችን ላይ ይስቃል:: ይህንን ሁሉ የልጅነታችንን አንድ ጉማጅ ከቴዲ አፍሮ በላይ የዘከረልን ማን አለ?! ቴዲ አፍሮ “ፊዮሪና”  እያለ ሲጣራ ‘ግራ የገባው ሰው ዘፈን ፣ የድሮዋን ኢትዮጵያ ናፋቂ’ ይሉታል:: እሱ ግን የብዙወቻችንን እውነት

“እስኪያበቃው አይኔን ላይንሽ የሱ ስራ

ጓል አስመራ ጓል አስመራ”  

እያለ መጫወቱ ከድንበር ባሻገር ስላለው ሰውኛ ወግ ማውራቱ ባይሆን ኖሮ አስቀድሞ ዳህላክን ባነሳበት ዜማ “ዝሆኖች ተጣልተው ሰበሩት ድንበሩን” ይል ነበርን?  እኛ የከሳሾቹን ሸር ሳይሆን የቴዲ አፍሮን ፍቅር እናውቃለን::

ከምድላየ!!! 

ቴዲ አፍሮ ግዙፍ ነው! ቴዲ አፍሮ ብዙ ነው! ቴዲ አፍሮ አባቶቻችን የሰጡን፣ ዘመዶቻችን የሞቱላት ፣ ባወረሰችን መከራ ሁሉ የማንጠየፋት የኢትዮጵያችን ድምጽ ነው::ኢትዮጵያ ውስጥ የአርቲስትነት ከፍታው አላሙዲን ቤት መንከባለል እና ዳንጎቴ ደረጃ ላይ ማሽቃበጥ በሆነበት በዚህ ዘመን የካሳሁን ገርማሞ ልጅ  በኩራት እና በታላቅነት የህሊናው ሰው ሆኖ ይኖራል:: ጫታቸውን እንኳን በሼኩ ምጽዋት የሚቅሙ እነ ነዋይ ደበበ ባሉበት አገር ቴዲ አፍሮ ‘ካንትሪ ክለብ እርጥባንህን አልቀበልም :: እኔ መኖሪያ ቤቴን ሰርቼ እንጂ ተመጽውቼ አልወስድም’  በማለት የከተማውን ምርጥ ማንሽን ቅንጡ ቤት እጅ መንሻ ወደጎን የሚገፋ ኩሩ አበሻ ነው:: ዛሬ ዛሬ  “ኩሩ አበሻነት” እንደ ቅርስ በየአዛውንቱ ባዮግራፊ ውስጥ እንጂ መሬት ላይ በማይገኝበት በዚህ ዘመን የካሳሁን ገርማሞ ልጅ ከገንዘብ ከፍ ብሎ ፣ ለገዥው ስልጣን ከማሽቋለጥም ራሱን ሰውሮ ለህሊናው ታምኖ ይኖራል:: አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር እንዲል !!

ተቦርነ የሚባል ባህላዊ በያጅ ቴዲአፍሮ ላይ በአደባባይ የዘመተ የመጀመሪያው ሰው ነው:: የተቦርነ ባህላዊ ትችት ያንድ ሰሞን መንጫጪያ ከመሆን አልዘለለም:: ወዲያው ግን የቴዲ አፍሮ ስራዎች ትችት አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ጉብ አለ:: አሁን ትችቱ ከመደዴ ነቆራ ወደ ‘ኢንተሌክቿል’ ሂስ አደገ:: ስራዎቹም ‘ቴክኒካሊ’ ተብጠለጠሉ:: ትችቶቱቹ ከአዳማጭ ‘ኦፒንየን’ነት የዘለሉ እንዲሆኑ ሰርጸ ፍሬስብሃትም የበኩሉን እንዳዋጣ እንገምታለን:: ያኔ ይህ መሆኑ ችግር አልነበረውም:: ቴዲ እንደ ማንኛውም የጥበብ ሰው ከትችት አያመልጥም:: ዛሬ ላይ ግን ኬኔዲ መንገሻ ከታፈነ ሰርኑ ስር በሚለቃት ዘፈን ሲቀውጥ የኖረ አገር እና ሚካኤል በላይነህ የሚባል እጅግ መደበኛ የሆነ ድምጻዊን አግንኖ ማሳየት የሚፈልግ ልሂቅ ቴዲ አፍሮን በድምጹ እና በድምጹ ብቻ መበየን እና ማሳነስ ሲፈልግ ታዝበን እንስቃለን:: ስቀንም እንናገራለን:: ያን ሰሞን ሰርጸ አንዱ ጋዜጣ ላይ “ቴዲ በተለያየ ሬንጅ መዝፈን የሚችልና በርካታ የድምፅ ቴክኒኮች አፈራርቆ መጠቀም የሚችል አይደለም” ማለቱን እየጠሩ ዛሬም ጽሁፋቸውን ለማድመቅ  የሚሞክሩ ወዳጆቻችን ስለምን እዚህ አሳብ ላይ ተሰፉ የሚለው ነገር ግርም ይለናል:: የሙዚቃችን ከዋክብት ጥላሁን ገሰሰ እና ሙሉቀን መለሰ የ6ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች በነበሩበት አገር ቴዲ አፍሮ ““ትምህርት ቤት የመግባት ድፍረቱ ሊኖረው ይገባል፤ ታሪክ ፍልስፍናና ቋንቋ ኮርሶችን ቢወስድ አቅሙን ይበልጥ ማጎልበት ይችላል ብዬ አስባለሁ” የሚለውን የሰርጸ ፍሬስብሃት የሰከረ ትችት ዛሬም አለአውዱ ስቦ ማምጣት እጅግ አስቂኝ ተግባር ነው [ላውረን ሂል እየተንከባለለች የምትስቅ ይመስለኛል] :: መሃሙድ የትኛው ኮሌጅ ተመርቋል? አለማየሁ እሸቴ የትኛው ካምፓስ ነበረ? አሊ ቢራ ካገር ከመውጣቱ በፊት እና ተወዳጅ የሆነባቸውን ዘፈኖች በዘፈነበት ዘመን ስንተኛ ክፍል ነበረ? ብዙ መጠየቅ ይቻላል:: ቴዲ እጅግ ዝነኛ እና ገዢ ከሆኑ ጥቂት ዘፋኞቻችን አንዱ በመሆኑ አይን ማረፊያ መሆኑ አይገርምም ነገር ግን ቴዲ ላይ በኢንተሌክቿል ስም የሚቀርቡበት ክሶች እሱ ላይ ብቻ ያተኮሩ እና ፌይር ያልሆኑ ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል:: 

ቴዲን የሚጠሉት ለምን ይጠሉታል?? የትግሬ ብሄርተኞች ቴዲ ላይ በጥላቻ ከዘመቱት የመጀመሪያዎቹ ናቸው:: ልክ በማሲሞ ዱቲ ሱፍ ቂቅ ብለው አዲስአበባ እንደገቡ ነገር ቁምጣችን ለምን ተጠራ በሚል እንዲሁም “ያስተሰርያል” የምርጫ 97 አስማት ሰልፍ ዋና ግብአት መሆኑን ተከትሎ ጠምደው ይዘውታል:: የሚገርመው ነገር ቴዲን በግለሰብ ደረጃ ያጠቁት ሰዎች ሆነው ሳለ ፤ ቴዲ ግን መሪያቸው ቢሞት ለቅሶ ለመድረስ ልቡን ያልከበደው ፣ የሚያወራውን የሚኖር ከፍ ያለ የሞራል ማማ ላይ የተሰቀለ ልኡል መሆኑን ማሳየቱ ነው:: እንደ ኃይሌ ገብረስላሴ እንባና ንፍጥ ሳይቀላቅል ፣ እንደ ትግስት ወይሶ የማስመሰል ዳንኪራ ሳይደነክር ፣ እንደ አትርሱኝ ባይ አርቲስቶች ተሰብስቦ ጭራውን ሳይቆላ እንደ ተራ ግለሰብ ከባለቤቱ ጋር ለቅሷቸውን የደረሰውን ሰው “ትግሬ ይንቃል” እያሉ ጠማሞች ስለ ቴዲ ጠማማ ጠማማውን ያወራሉ:: የጃዋር ሰልፈኞች ደግሞ  በሌላው ወገን የተሰለፉ ቴዲን የሚያጥላሉ አስቂኝ ፍጥረቶች ናቸው:: እነዚህ ስለሁላችን የሚዘፍነውን ቴዲን ነቅለው ዘረኝነትን የሚሰብከውን ሃጫሉን መትከል የሚፈልጉ ናቸው:: ድልድይ ሰሪ ነን በሚል ይህንን የጃዋር ሰልፈኛ የተደገፈ ሌላ ቡድን ደግሞ አለ ቴዲን በመጥላት የተጠመደ:: ለጥላቻው ምሁራዊ ምርኩዝ ሲፈልግ  የሰርጸን ትችት ይስባል:: ዞር ብሎ ደግሞ የመጨረሻውን አቨሬጅ ዘፋኝ ሚካኤል በላይነህን ሲያወድስ ታየዋለህ :: ‘ቴዲ የኦርቶዶክስ ዘፋኝ ነው’ ይልሃል ሃሳዊው ድልድይ ሰሪ::  “ሼ መንደፈርን” ስትጠራበት አፉ ዲዳ ይሆናል:: አያርፍም:: ‘ቴዲ የአማራ ዘፋኝ ነው ይልሃል’ መንገድ ቀይሮ ሲመጣብህ:: “ጥቁር ሰው” የተዋቀረበትን ችክችካ እና ሸጎዬ ስትጠቁመው ደግሞ ተመልሶ ያንኑ የጅል እንጉርጉሮውን “ቴዲ ድምጹ አያምርም” ያንጎራጉርልሃል:: ድልድይ ሰሪ ነኝ ብሎ እራሱን ለሾመው እንዲህ ያለ መንቻካ ሰው በረከት በላይነህ በቀደም የገጠማትን ስንኝ ወርውረህለት ታልፋለህ:: 

“ባ’ሻጋሪ ገጹ መራራቅ የሚስል

መአት ግድግዳ አለ ድልድይ የሚመስል” 

ቴዲን የምንወደውስ ስለምን እንወደዋለን ? በተማሪ ብራችን “እንደ ቢራቢሮ” ብለን ስላበድን? ከንፈሯን በሳምን ማግስት “አሁን አየ አይኔ” ብለን ስለጨፈርን? ወይስ ከነኢክራም ጋር “እኔም ልማል ባላህ አንቺም በቁልቢ” ስለተባባልን? ይህ ሁሉ ሊሆን ይችላል:: ግን ቴዲ አፍሮ ከዚህ ሁሉ ይልቃል:: ነውረኛ ምሁራን ለጎሳ ፖለቲካ በኢንቴግሪቲ ስም ሲያሸረግዱ በከረሙበት አገር ፣ የመንፈስ ደሃ የሆኑ አርቲስቶቻችን ንዋይ ፈለጋ በየባለጸጋው ደጃፍ በተኮለኮሉበት አገር ፣ ስለ አንድነታችን የሚዘምር ፣ ስለፍቅር የሚሰብክ ፣ የሚናገረውን የሚኖር ፣ የገዥዎቻችን እርግጫ የሚነቁር የካሳሁን ገርማሞ ልጅ ቴዲ አፍሮ ብቻውን አዲሳባ ላይ ተቸንክሮ ጠበቃችን በመሆኑ ባንወደው ነው የሚገርመው:: ቴዲ የቆመለት መንፈስ እንዲሰበር የሚፈልጉ ሁሉ ቴዲን ያጠቁታል:: ቴዲ የቆመለት መንፈስ እንዲያብብ የሚፈልጉ አንዳንዶች በተጓዳኝ ቴዲን ሲጠሉት ደግሞ ያስገርሙናል::  እኛ ግን ሃቁን አንስተውም!!! “ጃ ያስተሰርያል” ብቻውን ዛሬም አዲስአበባን ያስረግዳል:: ማንም ምሁር ፣ ማንም ፖለቲከኛ ፣ ማንም ተናጋሪ ነኝ ባይ የማይቀሰቅሰውን የፍቅር እና የአንድነት ማእበል ቴዲ አፍሮ ብቻውን ያናውጠዋል:: “የጠላሽ ይጠላ” ያለው ጥልዬ ፣ “ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ” ያለው ጥልሽ ዊልቸሩ ላይ ቁጭ ብሎ “አይኔን ባይኔ አይቼዋለሁ ፣ ብሞትም አይቆጨኝ” ብሎ ስለአልጋ ወራሹ ስለቴዲ አፍሮ ሲናገር ፣ ስለቴዲ ድምጽ እያወራ አልነበረም  https://goo.gl/zZEs7s  :: እሱ በጉብዝናው ወራት ስለዘፈነላት ኢትዮጵያ እና ቴዲን ስላሸከመው የአገር ፍቅር እያወራ እንጂ:: በሚገባ! ቴዲ በሞራልም ፣ በህልሙም ፣ በመንገዱም ከፍ ያለ የጥላሁን ገሰሰ ልጅ ነው:: ስለዚህ እንወደዋለን:: ስትዘምቱበት ዝም አንልም:: አላግባብ ስትጎነትሉም እንዳላየ አንሆንም:: የሚበዛው በቴዲ ሚዛን ሲመዘን የቀለለ ገለባ ነው:: ቴዲ የመጠበቂያው ማማ ላይ የቆመ ድምጽህ ነው:: ልትደግፈው ግድ ይልሃል::

Filed in: Amharic