>
8:32 am - Tuesday August 9, 2022

ጠመንጃ ያንቀጠቀጠ ሐሳብ! [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

BefeQadu Z. Hailu“ተራሮችን በጠመንጃ አንቀጥቅጫለሁ” የሚለው ‘ገዢው’ ፓርቲ፣ ለብዕር ግን ይንቀጠቀጣል። የአቶ መለስ (solo) አመራር እና የአቶ ኃይለማርያም የቡድን አመራር ሁለቱም ብዕር ይፈራሉ፣ የጨበጠውንም ይቀጣሉ።የመለስ ዜናዊ የ21 ዓመታት አመራር “በጻፈው ነገር የታሰረ ሰው የለም” እያለ ይጎርር ነበር። እኛም እንዴት አድርገን መስማት እንዳለብን እናውቅ ነበር፤ ‘ሌላ ወንጀል ፈጥረን ነው በሰበብ የምናስራቸው’ ማለታቸው የሚመስለን ጥቂት አልነበርንም። በአቶ መለስ ጊዜ የተከሰሱ ጋዜጠኞች “አዳፍኔ” ስለሚባሉ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጽፈዋል። ተከሳሽ ላይ ወንጀል ሲደፈድፉ ዓይን የላቸውም።

አሁን ለሰበብ የሚጨነቅ አመራር የለም። ዝም ብሎ የማሰር ጊዜ ሆኗል – ዓመቱ።

የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 257 በንዑስ አንቀፆቹ ‘በጽሑፍ [እና መሰል ድርጊቶች] አመፅ ማነሳሳትን’ ይከለክላል። በዚሁ መሠረት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል፤ ሑሴን አራጌ ሁለት ዓመት እንዳይጽፍ ታግዶበታል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ አንድ ዓመት ተፈርዶበታል። ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፍርድ ቤት እየተሟገተበት ነው። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ታስሮ እየተከላከለበት ነው። እኔ ተከራክሬ ጨርሼ ብይን እየጠየቅኩበት ነው። ዘሪሁን ገሠሠ ተከሶበታል። ወዘተ… እነዚህ ሁሉ (የዘረዘርኳቸው ክሶች እና ተከሳሾች) በጻፉት ጽሑፍ “ተነሳ ባሉኝ መሠረት ተነሳስቼ ይሄን አድርጌያለሁ” የሚል ግለሰብ ወይም ያንን ተከትሎ የደረሰ ጉዳት የለም። እንደማስረጃ የቀረበው የመንግሥት (ዐቃቤ ሕግ) ‘አመፅ ሊነሳ ይችል ነበር’ የሚለው ስጋት ነው። (የኤልያስ ገብሩ ክስ፣ እሱ ዋና አዘጋጅ የነበረበት መጽሔት ላይ አምሳሉ ገብረኪዳን የጻፈውን ጽሑፍ ተቃውመው ያመፁ የጅማ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ያደረሱትን ጉዳት ለማካካስ ያለመ ይመስላል፤ ብቸኛው የሚመስል ሰበብ የቀረበበት ክስም ይሄው ነው። የነጻነት አገር ቢሆን ኖሮ ግን ጋዜጠኛ ኤሊያስ ራሱ መጽሔቱ ላይ ባተመው ጽሑፍ ከሚመጣበት ሐሳብን በአመፅ ከሚሞግቱ ሰዎች አደጋ በመንግሥት መጠበቅ ይገባው ነበር።)

ቀደም ሲል በጠቀስኩት፣ በሰበብ ዘመን “በሽብርተኝነት” ሰበብ 18 ዓመት የተፈረደበት እስክንድር ነጋ እና 14 ዓመት የተፈረደበት ውብሸት ታዬ የሚታወቁት በሐሳቦቻቸው/ጽሑፎቻቸው ነው። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በ1997 ምርጫ ማግስት ስለፍፁማዊ አመፅ–አልባ “ሕዝባዊ እምቢተኝነት” መጽሐፍ አሳትሟል። ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ከታሰረ በኋላ በጻፋቸው ሁለት መጽሐፎች ደጋግሞ ያሳየው ለሠላማዊ ትግል ያለውን ታማኝነት ነው። ሁለቱም ተፈርዶባቸው ከታሰሩ በኋላ፣ ከእስረኛ ሁሉ በከፋ አያያዝ ነው ተይዘው እየከረሙ ያሉት። የነርሱ ወንጀል ኢፍትሐዊ ነው ያሉትን መንግሥት በሠላማዊ ትግል መውረድ እንዳለበት መሟገታቸው ነው። ይህንን ደግሞ በአመፅ እስካልሞከሩት ወይም በአመፅ እንዲከናወን እስካልተናገሩት ድረስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው። በኔ እምነት ዛሬ ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ የሚጀምረው ያኔ ነው። መንግሥት መካሪዎቹን ሲያስር። የአንጋፋዎቹ ሐሳብ ሰሚ ሲያጣ! ዛሬ ሁሉም አመፀኛ ሆኗል ማለት ይቻላል፣… በዚህም የተነሳ መንግሥት እጅ ላይ የተረፈው ለስለሳ ትችት ያቀረበውን ሁሉ መጠርጠር ነው።

አሁንም “የፖለቲካ ወንጀል” የሚባል የለም ብሎ የሚከራከረውን መንግሥት በመቃወማቸው ብዙ ሰዎች መታሰራቸው ምሥጢር አይደለም። ምሥጢሩ ‘የሚከሰሱት በምን ወንጀል ነው?’ የሚለው ነው። ጋዜጠኛ እዮኤል ፍስሐ ከታሰረ ከ100 ቀን በላይ ቢሆነውም፣ ክሱን አላወቀም። ጋዜጠቹ ኤልያስ ገብሩ እና አናንያ ሶሪም ከፖለቲከኛው ዳንኤል ሺበሺ ጋር ከ90 ቀናት በላይ የታሰሩት ምን ወንጀል ሠርተው እንደሆነ አልታወቀም። ብዙ ሰዎች “ወንጀል” ብለው የጠረጠሩት ሦስቱም እጃቸውን አጣምረው ተነስተው በለጠፉት የፌስቡክ ፎቶ እንደታሰሩ ነው። ጥያቄው ግን ‘በርግጥ ያንን ምልክት ማሳየት በሕግ ተከልክሏል ወይ?’ መሆን አለበት።

በሰበብ ዘመን፣ አቶ መለስ በድኅረ ምርጫ 1997 “ጣቱን የቀሰረ ይቆረጥለታል” ብለው ሲዝቱ “የመሪ ንግግር ያው ሕግ ነው” ብለን በጣቶቻችን የሁለት ሰው ምልክት ለበራሪ ታክሲ ለማሳየት እስከመፍራት ደርሰን ነበር። አሁንም ታሪክ በሽሙጥ መልክ ራሱን ደግሞ ሁለት እጅ አጣምሮ ማሳየት ሕገ ወጥ ነው በሚል ተፈርቷል። ሕግ ግን ጽሑፍ ይፈልጋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “አመፅ የሚቀሰቅስ ምልክት ማሳየት” ሲከለክል ምልክቱ ምን እንደሆነ አልጠቀሰም። ሌላው ቀርቶ ባለሥልጣናቱ የሰጡት ማብራሪያ ላይም በምልክት ወይም በገለጻ የተከለከለውን የምልክት ዓይነት ሲያብራሩ አላየሁም። ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች መታሰር ከጋዜጠኝነት፣ ፖለቲከኝነት ሥራቸው ጋር የተያያዘ ነው ብለን እንድንጠረጥር ያስገድደናል። ምክንያቱም ወንጀላቸው አልተነገረማ።

እነ ጋዜጠኛ ኤልያስ ያሳዩት ምልክት በርግጥም ተከልክሎ ከሆነ ተቃዋሚነት ተከልክሏል ማለት ነው። እንደሚታወቀው፣ ምልክቱ “ታስረናል” ወይም “ሐሳባችንን የመግለጽ ነጻነታችን ታስሯል” የሚል የተቃውሞ ሐሳባዊ መሟገቻ ነው እንጂ በምንም ዓይነት ከአመፅ ጋር አይያያዝም። ለዚህም ከተቻለ [ሚኒሶታ ሰልፍ የወጡት የኢሕአዴግ ደጋፊ የሶማሊ ተወላጆች በምላሹ እንዳሳዩት ዓይነት] የምልክት ግብረ ምላሽ ሰጥቶ ሐሳቡን በሐሳብ ለማሸነፍ መጣር ነው እንጂ በአዋጅ መገደብ “ተራራ ካንቀጠቀጠ”፣ ጠመንጃ ከጨበጠ ትውልድ ፈፅሞ የሚጠበቅ ነገር አይደለም።

ከላይ የተጠቀሰው ምልክት በአዋጅ የተከለከለው ምልክት ነው እንበል። ቢሆንስ ታዲያ ምልክቱ በተሐድሶ የማይታረም ወንጀል ሆኖ ነው ወይ እነ ጋዜጠኛ ኤልያስ ከተያዙ በኋላ የታሰሩ ሰዎች ለተሐድሶ ሲላኩ እነርሱ ያልተላኩት? ሌሎቹስ?

በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታሰሩ ሰዎች እጣ ፈንታ ሦስት ነው። ጉዳያቸው ተጣርቶ ነጻ መለቀቅ፣ በተሐድሶ ታርሞ መለቀቅ እና ፍርድ ቤት መቅረብ። ፍ/ቤት ይቀርባሉ የተባሉት እስካሁን አልቀረቡም። እነጋዜጠኛ እዮኤል ዳምጤ የርሐብ አድማ ለአምስት ቀን አድርገው ክስ እንደሚመሠረትባቸውና ለዚህም ልዩ፣ ተዘዋዋሪ ችሎት እንደሚቋቋም ተነግሯቸዋል። ይህ ከተባለም ቆየ። እነኤልያስ ገብሩ ምን እንደሚገጥማቸው ገና አላወቁም። በሰበብ አልባ ዘመን ክስም ይናፍቃል።

Filed in: Amharic