>
5:13 pm - Saturday April 18, 2607

ተቦርነ በየነ “አንተ አልክ?” - ቴዲ አፍሮን [ክንፉ አሰፋ]

Teddy Afro – ETHIOPIA – ኢትዮጵያ – [New! Official single 2017]እንዲህም ሆነ። የይሁዳ ገዥ የነበረው ጲላጦስ ክርስቶስን አስጠርቶ “አንተ የአይሁድ ንጉስ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ክርስቶስም መልሶ “አንተ አልክ?”  አለው። ሰማይን ያለ ምሰሶ ያቆመው ክርስቶስ “ጥፋ” የምትል ቃል ብቻ ከአንደበቱ ቢያወጣ ኖሮ ፒላጦስ አይደለም መላው ቂሳር ክምድረ-ገጽ በጠፉ ነበር።

ታዋቂዎች በአዋቂዎች ላይ የሚቀልዱበት ይህ የገሃዱ አለም እውነታ ግብረ-ገብ ወደ ግብግብ በተቀየረበት በዚህ ዘመን ባሰበት እንጂ አልጠፋም። ጥንት አንቺ-ትብሽ ፣አንተ-ትብስ ይባል የነበረው ብሂል አሁን በ”አንቺ ብስብስ አንተ ብስብስ” ተቀይሯል ሲል አንዱ አጫወተኝ። ከቶውንም ስድብን እንደ ስንቅ በከረጢት ቋጥረው በሚጓዙበት የፌስ ቡክ ዘመን መስመር የመልቀቁ ነገር አዲስ ሊሆን አይችልም።  “አንተ አልክ?” ብሎ ማለፍ ምን ይጎዳል?

ብላቴናው ላይ አንዳች እንከን ሲያጡ፣ የጠወለገን የጥላቻ ህያሴ ለማንጠባጠብ የሚሞክሩትን እንዲህ ማለቱ ይበጅ ይመስላል፤ “አንተ አልክ?”። እንግሊዞች “Cover before you discover”  ይላሉ። “አወቅኩ ከማለትህ በፊት፣ እወቅ” እንደማለት ነው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አንደራደረም ከሚሉ ወገኖች ያልሆኑትን- እነሱ ልንላቸው ነው።   ከእኛ ሳይሆን ይልቁንም ከነሱ ወገን፣  አንገት አርዝመው፤ ምላስ አሹለው የቴዲን ስራ ለማጣጣል ብቅ ያሉ  ሃያሲ ተብየዎች ግራ ቢገባቸው፣ “ቴዲ ስለ አባይ ስላልዘፈነ ግብጻዊ ነው” ሲሉ አስደምመውናል።  “ህዝቤ እውቀት ከማጣት የተነሳ ጠፍቷል” ይላል ቃሉ።  “ስለ አባይ ስላልተቃኘ ግብጻዊ ነው!” የሚለውን የድንቁርና ዝባዝንኬ ሲቀባጣጥሩ፣  የ”ፈለገ ግዮን” ምስጢራዊ ቅኝት ሊገባቸው አይችልምና እንደነዚህ አይነቱን ለማስረዳት መጣር ግዜ ማባከን ይሆናል።  አባይ  የወንዞች ሁሉ ታላቅና ንጉስ ስለሆነ፣ በታላቁ መጽሃፍ ፈለገ-ግዮን በሚል ስም ይጠራል።

እርግጥ ነው። ቴዲ አባይን ያየበት መንገድ ከባህላዊው ቅኝት ትንሽ ለየት ይላል። ስለ አባይ ያነሳው ቅኝት ለጸጸት፣ ለቁጭት እና ለፕሮፓጋንዳ ከተነሱት ዘፋኞች ሁሉ የላቀ ነው። ስለ አባይ ብዙ ተዘፍኗል። አንዳንዶች ግጥምን ከጉልት እንደሚሸመት ሸቀጥ እየገዙ አዚመውታል።  ይኽኛው ከነዚያ ስራዎች ጋር የሚነጻጸር አይደለም። በረቀቀ መልኩ “…ፈለገ ግዮን ያንቺ ስም ሲጠራ” ሲል በእናትነት፤ ከፍ ሲል ደግሞ ከሃገር ጋር አቆራኝቶ ተቃኝቶለታል።

ስለ ወዳጃችን ተወልደ/ተቦርነ በየነ የከተፋ ወግ ከመግባቴ በፊት በቴዲ አምስተኛው የአልበም ስራ የተሰማኝን ልግለጽ። አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ ይህንን ስራ በአንድ መስመር ሲያስቀምጠው፣ “እኔ ማለት ምችለው ቴድሮስ ካሳሁን / ቴዲ አፍሮ / ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን የጠፋውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የመለሰ ልብ አስታራቂ ልጅ ነው።” በማለት ነበር።

የሃይሌ ገብረስላሴን ገጽ ያነበበ ሁሉ በእርግጥ “የኢትዮጵያዊነት መንፈስ” ጠፍቶ ኖሯል የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይደንቅም። የኢትዮጵያን ባንድራ እያውለበለቡ ስምዋን በአለም መድረክ የሚያስጠሩም ሳይቀሩ ኢዮጵያዊነታቸው በሰላቢዎች ተሸልቶ የበጠፋበት ግዜ መሆኑ ግን ያስደነግጣል። በእናት እየመሰለ የተቀኘላት ይህች ሃገር የሚያቆስሏት እንጂ የሚቆስሉላት በጠፉ ግዜ፣ የሚጮሁባት ሳይሆን የሚጮሁላት በመነመኑበት ግዜ፣ በድብቅ ሳይሆን በገሃድ የ”እናፍርሳት” አፈርሳታ የሚዶልቱ በበዙበት በዚህ ዘመን፣ እናቱን ከነ ችግርዋ የሚወድዳት፣ በሲቃና በደስታ መሃል የተቀኘላት የጠላት፣ የሚጠላትን ደግሞ በድፍረት የሚረግም ጀግና ብቻ ነው።

ከ”ሰምበሬ” …እስከ “ናት ባሮ”  እናትን እናይበታለን፤ ከቴዎድሮስ እስከ አደይ ኢትዮጵያን እንቃኝበታለን።

“አደይ”ን እያሰማን ከመረብ ወንዝ በላይና ታች አድርጎ ታቹን በጀግናው አጼ ቴዎድሮስ ወደ ጎንደር ያስገባናል፤ ከዚያም “ማሬ” እያለ በጎጃም አውርዶ ወሎ እና ሸዋ ላይ ያወጣናል።  “ኦላን ይዞ” እያለን ወደ ደቡብ ይወስደንና “በአና ኛቱ” ምስራቅንና ምእራብን ያስጎበኘናል።  በሙዚቃው ቅኝት ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከጫፍ የማስጎብኘት ጥበብን መሰለኝ ሃይሌ ለማንሳት የፈለገው።  ይህ የድምጻዊነት ደረጃውን ጣራ ያደረሰው ብቻ ሳይሆን፣ የተነጠቀን ኢትዮጵያዊነት የማስመለስ ምትሃት ይመስላል። ይህ ስራ በውቀት ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ልቆ የሚገኝ ስለመሆኑ ሚሊዮኖች መስክረዋል። ሚሊዮኖች  “ኢትዮጵያ” እያሉ አብደዋል።

የቴዲ ስኬት ያሳበዳቸውም አልጠፉም።

አንድን ስራ ስነ ምግባር መተሞላ መልኩ መተትች አንድ ነገር ነው። በሙያው የተካኑ ይህንን ቅንብር ቢተቹ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም። ከግል ጥላቻ ብቻ ተነስቶ ይህንን ድንቅ ስራ ጥላሸት ለመቀባት መሞከር ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ስኬቱ ያበገናቸው ሁሉ ዘልለው የማይይዙትን ተራራ ለመንካት ከቁመታቸው በላይ መንጠራራትን ይዘዋል።

ተቦርነ በየነ የኢሳት ራዲዮ ላይ ስለ “መተቸት መብት” ይናገራል። መብትም እኮ “መብት” ስለሆነ ብቻ ፋይዳ አለው ማለት አይደለም። አጋጣሚ እየፈለጉ እንደ Crusades የማያቋርጥ ማጥላላትን በአንድ ብላቴና ላይ ማናፈስ ግን መብት አይደለም፣ ፍጹም ጭፍን የሆነ ጥላቻ እንጂ። ጥላቻና ማን-አለብኝነት ደግሞ የደካማነት እንጂ የጥንካሬ ምልክት አይደለም። ለሃገር ቆምኩ የሚል ሰው በሃገር ጉዳይ ላይ አይደራደርም።  ለነገሩ እንጂ “ሺ ዝንብ መሶብ አይከፍትም” እንዲሉ፣  እነዚህን በእውቀት እና በጥበብ ከፍታ ላይ የተሰሩ ስራዎች የማውረድ አቅም ያለው ሊኖር አይችልም።

ይህች ሀገር አሽቃባጭ እና ጥሩምባ ነፊ አላጣችም።  ሊያጠፉዋት የሚዶልቱትን እንኳ ሳይቀር በአንዲት ዜማ ማስመለስ የሚችሉ፣ ከችሎታው በላይ ደግሞ ዝምታን ደፍረው የሚሰብሩ ናቸው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጉዋት።  ይህንን ቴዲ ሲያደርግ አልጋ ባልጋ ሆኖ አይደለም። ከሚነደው እሳት ጥግ ሆኖ ወላፈኑ እየገረፈው ይህንን አደረገ። ከውጭ ሆናችሁ ሌላ እሳት መለኮስ የምትሹ ሁሉ፤ እባካችሁ ተወት። ወላፈኑ ይበቃዋል።

ተወልደ/ተቦርነ በየነ በቴዲ ስራዎች ላይ ያሻውን የማለት መብት አለው። በአመክንዮ ሳይሆን በጥላቻ ስራውን ለማጥላላት እንደሚሞክረው OMN ቲዩብ ማለት ነው።  ተቦርነ ቲዩብ ብሎ መልቀቅም ይችላል። ኢሳትን ምርኩዝ አድርጎ ሲሰራው ግን የ”ትችቱ” ትርጉም ይቀየራል። “ቀላል ይሆናል” ይላል ቴዲ – ነገሮች መስመር ሲስቱ። ይህ ዘመቻ-  የ”ሙዚቃ ሃያሲ”ው ትራስ እያደረገ የሚነሳበት ተቋም ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ግን “ቀላል አይሆንም”። የኢትዮጵያን ማልያ ለብሶ ለ OMN መጫወት ይመስላል። አንድ ግለሰብ ከሚሊዮኖች ጋር ለመላተም ከቶውንም አይደፍርም። አእምሮውን ቆልፎ ይህንን ድፍረት የሚሰጠው ትራስ ካልተማመነ በስተቀር።… አካሄዱ “ሹሩባ ልትሰራ ሄዳ ጠጉሩዋን ተላጭታ መጣች”  እንዳይሆን ነገሩ የገባው ሁሉ ይወቅበት።

አዎ ቴዲ ስለጎንደር የተቃኘውን ስራ “የይርጋ ዱባለ ሰራ ነው” ሲል ተቦርነ አሹፎበታል። “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” እንዲሉ ከዚህ ቀደም እንደሚለው “ለምን ይዋሻል”ን አልጨመረበትም እንጂ ሙዚቃው ከሌላ ድምጻዊ እንደተወሰደ በድፍረት ተናግሯል። በኢሳት ራዲዮ  የተናገረው ቃል በቃል እንዲህ ይላል።

“በቴዎድሮስ ካሳሁን አዲሱ ኢትዮጵያ የሚዚቃ አልበም ውስጥ የአንጋፋውን የባህል ድምጻዊ የይርጋ ዱባለን ጎንደር የተሰኘ ስራ ጨምሮ 14 ያህል የሙዚቃ ስራዎች ተካትተዋል።”

ከዚያም ይደግምና “ከአንጋፋው ይርጋ ዱባለ ጎንደር የተሰኘው ስራ ውጭ ሌሎች አስራ ሶስት የሙዚቃ ስራዎች ግጥም እና ዜማ ድርሰቶች የድምጻዊ  የቴዎድሮስ ካሳሁን ናቸው።” ይለናል።

አልበሙ ላይ የምናየው የዚህ ስራ ግጥም ጸሃፊ “በቴዎድሮስ ካሳሁን” ይላል። በዜማው ላይ ጎንደርኛ  ቅኝት የቀባበት መሆኑንም በግልጽ አስቀምጦታል።   ቴዲ በጠራራ ጸሃይ ሊዋሽ እንደማይችል ግልጽ ነው።  ለከተፋው ይህ ስራ የተመረጠበት ምክንያትም፣ ሙዚቃው በህዝብ ልብ ውስጥ እጅግ ዘልቆ መግባቱ ይመስላል።

የሚደንቀው ደግሞ የቴዲን አልበም ሽያጭ ለማኮሰስ ሲል የተጠቀመበት የንጽፅር መነጽሩ ነው። የአልበም ሽያጭ ሰልፉን ከሌሎች ድምጻውያን ሰልፎች ጋር ለማወዳደር የሞከረበት መንገድ ቴዲን ሳይሆን ይልቁንም አድማጩን ሕዝብ የመስደብ ያህል ነው። ከጅምሩ ይህ አልበም ከሌሎች ድምጻውያን አልበም ጋር  ለንፅፅር መቅረብም የለበትም።  በሚሊዮን አይደለም በመቶ ሺዎች ያሳተመ ድምጻዊ በኢትዮጵያ ታሪክ አልነበረም፣  የሚዚውቃ ሲዲ እንደ ቀበሌ ስኳር በሰልፍ እና በሽሚያ የተገዛበት አጋጣሚም የለም፤ አዟሪዎች ሲዲን በእጥፍ የሽጡበት ወቅት አላየንም። እስከዛሬ በማንም ድምፃውያን ያልተከሰተን ነገር ነው ለንፅፅር ሊያቀርብ የሞከረው።

ለወንድሜ ተቦርነ የምለው አንድ ነገር ብቻ ነው። ልቦና ይስጥህ። በጥላቻ እና በትችት መሃል ያለን ልዩነት መቀበል እና ማመን ይገባሃል። ጥላቻ ደግሞ እንዲሁ አይመጣም። ምክንያቶች አሉት። ግላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ምክንያቶች። ጥላቸው ከየትም ይምጣ ከየት – ግን አንድ የምመክረው ነገር አለ። አበው እንደሚመክሩት “ቆዳ ሲወደድ በሬህን እረድ።”  እጅህን ከቴዲ አንሳ!

(ንግግሩን ለማድመጥ https://ethsat.com/2017/05/esat-radio-hule-addis-sat-06-may-2017/ ከ10ኛው ደቂቃ ጀምሮ)

Filed in: Amharic