>
5:13 pm - Saturday April 18, 7699

ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር፡- የሆለታ ገነቱ ገጣሚ እና የጦር ሰው (ታሪኩ አበበ)

Writer shaleqa Kifle Abocher and Artist Teddy Afroእኚህ በምስሉ ላይ ከቴዲ አፍሮ ጋር ቆመው የምታዩአቸው ሰው ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ይባላሉ ብዙዎች በስም እንጂ በመልክ አያቋቸውም ወይም ከእርሳቸው ስም በላይ በእርሳቸው የተጻፉ ገናና የሙዚቃ ስራዎች ይበልጡኑ ይታወቃሉ በተለይም ለጥላሁን ገሰሰ ከሰጡት ግጥሞች መካከል፦
“በአካል ሳይፈተን በአካል ሳይነካ
የማን ምንነቱ ግብሩ ሳይለካ
እርግጥ በተፈጥሮ በወል ስም ይጠራል
በቁም ነገር መድረክ ሰው ከሰው ይለያል”
የሚለው ሙዚቃ የሻለቃውን ጥልቅ የስነጽሁፍ ችሎታ በልግልጽ ከሚያሳዩ ሰራዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው።
ከዋናው ስማቸው ፊት የተቀመጠው ሻለቃ የሚለው የመኮነን ማዕረግ ዝምብሎ የመጣ አይደለም የቀድሞው የሆለታ ጦር አካዳሚ ምሩቅ እና በሱማሌ ጦርነት ጊዜ በታጠቅ ጦር ሰፈር ስልጠና ይወስድ የነበረውን የሚሊሻ ጦር በፓለቲካ ከማንቃት ጀምሮ እስከ ጦርነቱ ድረስ የተሳታፉ የቀድሞ የኢትዮጺያ ጦር ሰራዊት አባል የነበሩ እንዲሁም በጦርነቱም ጊዜ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው እንደሌሎች ውድ ኢትዮጲያዊያን ጓዶቻቸው ሁሉ ለሀገራቸው መስዋትነትን የከፈሉ ምርጥ ኢትዮጲያዊ ናቸው።

እኔ ግን ከውትድርናው ህይወታቸው ይልቅ የስነጽሁፍ ህይወታቸው ይበልጥ ይመስጠኛል የሶማሊያ ተስፋፊ ጦር የሀገራችንን አንድ አምስተኛ የሚሆነውን መሬት እስከመጨረሻው ድረስ የራሱ ለማድረግ ሀገራችንን በጉልበት በወረረበት እና ሀገራችን አደጋ ውስጥ በገባችበት ጊዜ ከውትድርናው ተጋድሎአቸው እና ከወደሩት የክላሺንኮቭ ጠመንጃ በላይ የተባው ብዕራቸው ጦርነቱን በድል እንድንወጣ ትልቅ አስተዋጾን አበርክቷል ለማለት ይቻላል።

የነበራቸውን አስደናቂ የስነጽሁፍ ችሎታን በመጠቀም የኢትዮጲያ አንድነትን የሚሰብኩ የኢትዮጲያ ሰራዊትን የሚቀሰቅሱ፣ ጀግናን የሚያሞግሱ ከጥቃቅን የግል ፍላጎቶቻችን ይልቅ ሀገርን ማስቀደም እንዳለብን የሚያሳስቡ እና ሰራዊቱን ለመስዋትነት የሚያዘጋጁ በርካታ ለቅስቀሳ የሚሆኑ ሙዚቃዎች (አብዮታዊ) ግጥሞቻቸውን በመጻፍ ሀገራቸውን አገልግዋል።
በ1969 ዓ/ም ለኢትዮጲያ ፈታኘ ጊዜ ነበር በሰሜን የኤርትራ ተገንጣይ ሀይሎች እና ወያኔ በሰሜን ምዕራብ ኢዲዩ በመሀል ሀገር ደግሞ ኢህአፓ ከመአከላዊ መንግስት ጋር ጦርነት የገጠሙበት ጊዜ ነበር ይህንን እንደአመቺ አጋጣሚ በመቁጠር ሶማሊያ የረጂም ጊዜ እቅዷን ለማሳካት ሀገራችንን በጉልበት የወረረችበት ጊዜ ነበር ወረራውን ለመመከት ደግሞ ኢትዮጲያዊው ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ በታጠቅ ጦር ሰፈር ከተተ በታጠቅ ጦር ሰፈር ለሶስት ወራት ብቻ ስልጠና የወሰደው ሶስት መቶ ሺህ የሚሆነው የሚሊሻ ጦር ስልጠናውን ጨርሶ ሰኔ 19 ቀን በአብዮት አደባባይ ወታደራዊ ትርኢት ሲያሳይ እና የጀግና አሸኛኘት በተደረገለት እለት ባደባባይ ለተሰበሰበው ህዝብ የወታደራዊ ሰልፍ ትሪኢት በሚያሳይበት ጊዜ ለሚዘምራቸው መዝሙሮች ግጥም ያዘጋጁት ሻለቃ ክፍሌ ነበሩ በተለይም በእርሱ ተጽፈው በተሾመ ሲሳይ ዜማ ተደሶላቸው በምድር ጦር ኦርኬስትራ ቅንብር እና ህብረዝማሬ የተዘጋጁት ቀስቃሽ መዝሙሮች በወቅቱ አጠራር አቢዮታዊ መዝሙሮች ተጠቃሾች ናቸው።

“ይህ ነው ምኞቴ እኔ በህይዎቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጲያ እናቴ”
*****
“ለአንድነቱ ድሉ እንዲሰምር ለነጻነቱ
ወጣ ወረደ ሄደ ነጎደ ሰራዊቱ
ምሎ ተነሳ ህዝባዊ ሰራዊት
ጉዞ ጀመረ እየዘመረ”
እነዚህ ድንቅ መዝሙሮች በወቅቱ ሰራዊቱን በማነቃቃት እና ጓዳዊ መንፈስን በማጠንከሩ ረገድ ትልቅ ሚና
የተጫወቱ ነበሩ።
*********
ጊዜው 1970 ዓ/ም ነው የኢትዮጲያ ሰራዊት በሶማሊያ ሰራዊት ከፍተኛ
ማጥቃት ተሰነዘሮበት አፈግፍጎ ሀረር አካባቢ በሚገኘ ጃርሶ በሚባል ከፍተኛ
ቦታ ላይ ሰፍሮ ከኃላ ተጨማሪ ኃይል እንዲመጣለት ድረሱልኘ ይላል ወዲያው
አየር ኃይል በሰማይ እነጥላሁን በምድር ከተፍ አሉ “ወረድ በለው” አለ
ጥላሁን ወዲያው የጦርነቱ ሁኔታ ተለወጠ የኢትዮጲያ ሰራዊት ከመከላከል
ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ።

“ወረድ በለው ግፋ በለው ግደል ተጋደል
በረታ ወገኔ ባለው ታሪክህ ባባትህ ወኔ”

ይህንን የጥላሁን ድንቅ ሙዚቃ ግጥም የጻፈው ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ነበር። ይሄን ብቻ አይደለም ሌሎችም ተወዳጅ እና ቀስቃሽ ግጥሞችን ለጥላሁን ሰተውታል እነሱም በትንሹ ይህን ይመስላሉ…

ሻለቃ ክፍሌ በአንድ ጦርነት ላይ ቆስሎ ለማገገም ድሬዳዋ ሆስፒታል ይገባል በሆስፒታል አልጋውም ላይ እያለ ግሩም ግጥም ጽፎ ወደ አ.አ ይልካል ግጥሙም ወደ ሙዚቃ በጥላሁን ተዜሞ እዛው ሆስፒታል አልጋው ላይ እያለ በራዲዮ ይሰማዋል

“እንኳንስ በህይወት እያለሁ በቁሜ
ለሀገሬ ነጻነት ይሟገታል አጽሜ”

የሚል ሙዚቃ ነበረ በዚህ ሙዚቃ ለሀገር በክብር በክብር መሰዋትን ሰብኮበታል
****
“ለሀገሬ ስታገል ለድንበሯ ወድቄያለሁ እኔ ላፈሯ
ስለድል ታሪኬ ስታወሱ ቤተሰቦቼን ግን እንዳትረሱ”
በማለት የዘማች ቤተሰቦች በቂውን ክብር እንዲያገኙ እና በጦርነቱ ጊዜ የቤተሰብ አስተዳዳሪ አባ
ወራቸው የተሰዋባቸው ቤተሰቦች የመሬት ይዞታቸው እንዲከበርላቸዉ ልጆቻቸው በመንግስት የህጻናት ማሳደጊያዎች እንዲያድጉ የበኩሉን አስተዋጾ ማድረግ ችሏል።
*****

“ከመራራው ትግል ከጀግኖች ደም ጀርባ
አዲስ አለም ታየኘ ከአቢዮት ድል አምባ”
*****
ብዙዎቻችን በልጅነታችን በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን እያየነው ያደግነው ጥላሁን እያለቀሰ ስለሀገር ያዜመውን በእናት ሀገር ፍቅር በሚያውቀኘ በማውቀው የሚለው ሙዚቃ የሻለቃ ክፍሌ የጥበብ ውጤት ።
እነዚህ ስራዎች ከሻለቃ ክፍሌ አቦቸር በርካታ ስራዎች ጥቂቶቹ ቢሆንም በስራዎቹ የኪነጥበብን ኃይል ኪነጥበብ መዋጋት እንደምትችል ማስተማር እንደምትችል ለተፈለገው አላማ ህዝብን ማሰለፍ እንደምትችል ያሳየ ድንቅ
የጥበብ ሰው ነበር።
በአሁን ሰአት በሜሪካን ሀገር ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በመኖር ላይ ይገኛል ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ስለ ሰጠኸን ነገር ከልብ እናመሰግናለን።

Filed in: Amharic