>

"ኢትዮጵያዊ ማነው?" (ሙሉነህ ኢዩኤል)

Ethiopia - MAPየዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ አንድ ሀሳብ አልባ ኦሮሞ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝቶ “ኢትዮጵያዊነት የሞተው ግንቦት7 ኤርትራን እንደ አገር ተቀብሎ ኤርትራ የገባ ጊዜ ነው” ሲል ተናገረ። በእርግጥ የዚህን ሃሳብ አልባ ሰው አመክንዮ ከተከተልን አስቀድሞም ኢትዮጵያዊነት በተሳሳተ መሰረት ላይ የቆመና በጥቂቶች ልብ የነበረ ያስመስለዋል። በእርግጥ ኢትዮጵያዊነት በተሳሳተ መሰረት ላይ ከነበረና መሰረቱ ሲስተካከል የሚጠፋ ነገር ከነበረ በፊትም የነበረ መስሎን እንጂ ያልነበረ ነገር በመሆኑ ለመጥፋቱ የግንቦት7 መሪዎች ተጠያቂ አይሆኑም።

ዛሬ ደግሞ አንዳንድ የአማራ ብሄርተኛ ልሂቃን “ኢትዮጵያዊነት ያለ አማራነት አይጸናም” ሲሉ እያደመጥን ነው። በዚህም “ኢትዮጵያዊነት” አማራነት አማራነትም “ኢትዮጵያዊነት” ያስመስሉታል። ይህን አባባል ከትናንት በስትያ እነዋለልኝ፥ ትላንትና የኦሮሞ ብሄርተኞች ሲሉት ያደመጥነው ነገር በመሆኑ አዲስ ነገር አይደለም። አዲሱ ነገር የትላንት እና የከትላንት በስትያ ሰዎች ይህን በማለታቸው ያወገዟቸው ሰዎች የበፊተኞቹን እግር መተካታቸው ብቻ ነው። በእርግጥ “ኢትዮጵያዊነት” የአማራ ብሄርተኞች በአማራነት ከተደራጁ የሚጠፋ ነገር ከሆነ በፊትም ስላልነበረ ለመጥፋቱ የአማራ ብሄርተኞች ተጠያቂ አይሆኑም።

በእርግጥ አሳዛኙ ነገር “ኢትዮጵያዊ ማነው?” የሚለው ጥያቄ ዛሬም እየተጠየቀ መሆኑ ፖለቲካችን አንድም ይህ ጥያቄ ከተጠየቀበት የዛሬ አርባ አመት ከነበረበት ቦታ ፈቅ አለማለቱን አልያም እኛ የኋሊት እየተጓዝን ኦቦ ኢብሳ ጉተማ ጋር መድረሳችን ነው።

ኢትዮጵያዊነት ኤርትራም እንደሀገር እያለች፥ የአማራ ብሄርተኞችም በአማራነታቸው እየተደራጁ ዛሬም ያለ ወደፊትም ኢትዮጵያውያኑና ኢትዮጵያዊነት የማይሰማቸው የሀገራችን ህዝቦች ልዩነቶቻችንን በሰላም አቻችለን ፖለቲካችንን አርቀን ጉዞአችንን ወደፊት ስልቀጥል ኢትዮጵያዊነታችንም በጋራ በሚኖረን መስተጋብር እየዳበረ፥ እየተሻሻለ፥ እየሰፋ የሚሄድ ማንነት ሆኖ ይቀጥላል። ስለሆነም ኦሮሞ ሆነን ኢትዮጵያዊ፥ ትግሬ ሆነን ኢትዮጵያዊ፥ አማራ ሆነን ኢትዮጵያዊ፥ ሱማሌ ሆነን ኢትዮጵያዊ ፥ ከምባታ ሆነንም ኢትዮጵያዊ እንሆናለን።

Filed in: Amharic