>

"አሳረፍናቸው"

(ከ1887 ~ 1939ዓ.ም.)

yoftahe-niguse በ52 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታላቁ ባለቅኔ፣ ጸሐፌ-ተውኔት፣ አርበኛ፣ የመዝሙርና የታሪክ ጸሐፊው ዮፍታሔ ንጉሴ፣ ከ70 ዓመታት በኋላ አጽማቸው በትውልድ ቀያቸው ጎጃም፤ በደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስትያን ዛሬ፣ ሐምሌ 1ቀን 2009ዓ.ም. በክብር አርፏል።

*  የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ፍልስተ አፅምን ይዘን ከአዲስ አበባ ~ ከመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ተነስቶ በደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል።

* የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን “አፋጀሽኝ” ትያትርን በአዲስ አበባና በደብረ ማርቆስ ከተሞቾ አቅርበዋል።

* በዚህ ታላቅ ጉዞ ደጀን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወንቃ፣ ሰንተራ ሜዳ፣ ፈንደቃ፣ ወይንማ፣ የውላ እንዲሁም በደብረ ገነት ኤልያስ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የክብር አቀባበልና ሽኝት አድርጎላቸዋል።

* ደብረ ገነት ኤልያስ ከተማ ከመድረሳችን ልዩ ወታደራዊ የክብር ዘብ አስክሬኑ ተቀብሎ እንዲሁም በወታደራዊ አጀብ በክብር እንዲያርፍ አድርገዋል።

* የልጅ ልጆቻቸው (ቅዱስ እና ትዕግስት የምሩ ዮፍታሔ ንጉሴ) እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል ።

*  የመታሰቢያ ሐውልት እና  ሙዚየም ግንባታ የመሠረት ድንጋዮች ተቀምጠዋል

***

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዲህ አለ …

አራት ኪሎ ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አጠገብ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ‹ልማት ላለማ ነው› ብሎ በዚያ ያረፉ ክርስቲያኖችን ዐጽም አንሡልኝ እያለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስን፣ ቀጥሎ የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን አሁን ደግሞ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም አንሡ ብሏል፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድ የማን ነው?

ለፕሮፌሰር ዐሥራት የማይሆን በዓለ ወልድ የማን ነው?

ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ያደጉ፣ ቤተ መቅደሱን ያገለገሉ፣ በሕክምና ሞያቸው ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እስከ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያከሙ፣ አያሌ ጳጳሳትንና መነኮሳትን በየጊዜው እቤታቸው ድረስ እየመጡ ሲረዱ የነበሩትን የሕክምና ሰው እንደ ባዕድ ቆጥሮ ‹አንሥቼ ወደዚያ አደርጋቸዋለሁ› አለ፡፡

ገና ለገና ከዘመኑ ጋር አይስማሙም፣ በእርሳቸው ጉዳይ መንግሥት አይቆጣንም ብለው ካልሆነ በቀር የፕሮፌሰሩ ውለታ ጠፍቷቸው አልነበረም፡፡ ቀድሞውንም አቡነ ጳውሎስ ፖለቲካው ተጭኗቸው እንጂ ለጥላሁን ገሠሠ የሰጡትን የሥላሴ ቦታ ለፕሮፌሰር ዐሥራት መንፈግ አልነበረባቸውም፡፡ በርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዋሉባት እንጂ ለዋሉላት መሆን ካቆመች ቆየች፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተማሩት በዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ የደከሙት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ ያገለገሉት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን – እንዴት ባለ ሂሳብ ነው አዲስ አበባ ለቴአትሩ ንጉሥ ቦታ የላትም ተብሎ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዐጽሙ ይሂድ የሚባለው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ መቀበርም የሚቻለው በክልላችሁ ነው ልትሉን ነው?

ዮፍታሔ ንጉሤ የደብረ ኤልያስ ብቻ ናቸው? ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከትሺውን ሰው ጥቀሽ ስትባል ከምትጠቅሳቸው ተርታ አይደሉምን? ይህ ለትውልዱ እየሰጠነው ያለው ትምህርት የት የሚያደርስ ነው?

መሐል ሠፋሪ ጦር ጃንሜዳ እየተሰበሰበ አንዴ እቴጌ ጣይቱ ከቤተ መንግሥት ይውጡ፣ አንዴ ሚኒስትሮቹ ይነሡ ሲል፣ መኳንንቱም እየተቀበሉ ሲያስፈጽሙ፣ እቴጌ ጣይቱ ‹ለዚህ ጦር ክፉ ትምህርት አታስተምሩት፣ ካልሆነ ሁላችሁንም ያወርዳችኋል› ብለው ነበር፡፤ ሰሚ አልተገኘም፡፡ ያው ጦር ግን በ66 ዓም ንጉሡንም መኳንንቱንም አወረደ፡፡ ያውም እንደ እቴጌ ጣይቱ ወደ እንጦጦ አልላካቸውም ፣ ወደ እንጦሮጦስ እንጂ፡፡

ዛሬም ለዚህ ትውልድ ክፉ ትምህርት ባታስተምሩት መልካም ነው፡፡ ዐጽም እያሽቀነጠሩ ሱቅና አዳራሽ መሥራት ነገ በዐጽመ ቅዱሳን መወጋትን ያመጣል፡፡ ሲሠራና ሲታደስ ገንዘብ ካላመጣችሁ የምትሉን ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲህ ደስ ሲላችሁ ዐጽማችንን የምትወረውሩበት ከሆነ በዓለ ወልድ የማነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡

በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጽር ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሕንጻ እየሠራ ነው፡፡ ከሕንጻው አጠገብ አንድ አምስት መቃብሮች አሉ፡፡ አንዱ የጣልያን ወታደር፣ ሌሎቹ የኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት እነዚህን ዐጽሞች እግር ከሚጠቀጥቃቸው በክብርና በሥርዓት አንሥተን በተገቢው ቦታ እናድርጋቸው፣ ብለው ጠየቁ፡፡ ቤተ ክህነቱ የሰጠው መልስ ግን አስገራሚ ነበር፡፡

‹ከመቃብሮቹ መካከል የኢትዮጵያውያንን እንደፈለጋችሁ ማንሣት ትችላላችሁ፤ የጣልያኑን መቃብር ግን እኔ መፍቀድ አልችልም› አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለጣልያን ወታደር የምትሰጠውን ቦታ ያህል ለአድማሱ ጀንበሬና ለዮፍታሔ ንጉሤ የላትም?

ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ …

ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ … ይሉ ነበር፡፡

***
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  መምህር #ይኩኖአምላክ መዝገቡ የስንብት ስንኝ እንዲህ ይላል …

የዐጽሞችኽ ማረፊያ ደብረ ኤልያስ ትኩራ፣
በቃልኽም ጸዳል ጥበባችን ታብራ

Filed in: Amharic