>

ይድረስ ለካድሬው ወዳጄ! (ዘውድአለም ታደሰ)

ይድረስ … በኢህአዴግ ወንጌል አምነህ ፣ ፌደራሊዝምን እንደግል አዳኝህ ተቀብለህ ፣ አንድ ለአምስት ተደራጅተህ ፣ በውሎ አበል አተር ክክ የምታህል ቦርጭ አውጥተህ ፣ የሆነች ቀበሌ ውስጥ የ አ/ገ/ጫ/ቱ/ሪ/ና/ፋ በሚል አሸን ምህፃረ ቃል ያበደ ወሳኝ የስራ ሂደት ሃላፊ የተባልህ ፣ ለጎንህ ማረፊያ ሚጢጢ ኮንዶሚኒየም ተሰጥቶህ ለምትኖር ካድሬው ወዳጄ።

ለጤናህ እንደምን አለህልኝ? ያው እኔና አንተ ምስኪኖቹ እንጠያየቅ እንጅ እላይ ቤት ያሉትማ የታይላንድና የማሌዢያ እውቅ ሃኪሞች ይኑሩላቸው እንጂ ምን ይሆናሉ ብለህ ነው?

እና እንዴት ነኝ አልከኝ? «ሁለት አሃዝ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሃገር ላይ እየኖርኩ ምን እሆናለሁ?» አልከኝ ልበል? ይሁንልህ ወንድሜ! ያርግልህ! እድገትህ ከቻይና ባቡር ይፍጠን! ኑሮህ እንደግርማ ወልደጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት ይመር!

ይሁንልህ ስልህ ምን ትዝ አለኝ መሰለህ ካድሬውዬ? አንድ ግዜ ሃይለስላሴ ራሳቸው የመረቁት ብሔራዊ ቲአትር በር ላይ ያለውን በኮብልስቶን የተሰራ አንበሳ ረስተውት ነው አሉ … በዚያ ሲያልፉ «ይሄ ተንበርክኮ ሃውልት የተሰራለት ሰውዬ ማነው?» ብለው ጠየቁ። ጋሻ ጃግሬዎቻቸውም በጥያቄያቸው በመገረም ፈጠን ብለው «ንጉስ ሆይ ይሄኮ ሞኣ አንበሳ ነው» አሏቸው። ጃንሆይ ታዲያ ግርርርም ብሏቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? …. «ይሁንላችሁ!»

ይኸው ከጃንሆይ ቀጥለው ደርጎች መጡ! በመጡ በማግስቱ ታዲያ «እኛ ለጭቁኑ የኢትዮጲያ ህዝብ ስንል ነው ስልጣን የጨበጥነው» አሉ። የኢትዮጲያ ህዝብ ታዲያ ምን አለ? «ይሁንላችሁ!»
ትንሽ ቆዩና ደሞ ሶሻሊስትነታቸውን አወጁ! አሁንም ይህ በኮሚኒዝምና በቡድሂዝም መሃከል ያለው ልዩነት በቅጡ ያልገባው ምስኪን ህዝብ ፈገግ ብሎ «ይሁንላችሁ!»
ቀጠሉ ደርጎች … «መሬት ላራሹ!»  አሉ ባላባቱ ተከፋ! ጭሰኛው ተደሰተ! ሚነጠቀው መሬትም ሆነ ሚያገኘው ርስት የሌለው የኢትዮጲያ ህዝብ ግን አሁንም እንደንጉሱ «ይሁንላችሁ!» አለ!

እያለ እያለ …. ደርግ ሆዬ ህዝቡ ላይ ቫንዳም ቫንዳም መጫወት አማረውና ቀይ ሽብር! ነጭ ሽብር! ሰማያዊ ሽብር! ወዘተ በማለት ሽብርተኛን በቀለም ከፋፍሎ ማተራመስ ሲጀምር አሁንም ይህ ህዝብ ግራ ግብት ብሎት ምን አለ? «ይሁንላችሁ!» አለ!

ያው ታሪኩን ታውቀዋለህ መቼም ብሶት የወለዳቸው አለቆችህ በመራራ ትግል ደርግን ጥለው ህዝቡን «አቢዮታዊ ዴሞክራሲ ነው ሚበጅህ!» አሉት …. ህዝቡስ ምን አለ? …. «ይሁንላችሁ!»

አቢዮትና ዴሞክራሲን ምን እንዳገናኛቸው እንጃ ብቻ ለሃያ ምናምን አመታት ይኸው በአቢዮታዊ ዴሞክራሲ እየተመሩ ፣ በቀን ሶስቴ ትበላለህ በሚል የተስፋ ቃል ይሄን ምስኪን ህዝብ እያስጎመዡ ፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችና ድንበር የለሽ እስር ቤቶች ገንብተው ሰነበቱ!
ህዝቡም  እግዜር ይመስገን በጀሶ የተለወሰ እንጀራና ከሸክላ ጋር የተፈጨ በርበሬን አቅሙ እንደቻለ እየበላ የአተትና የመተት መጫወቻ ሆኖ አቧራ እየተነፈሰና ጂብሰም እየተፀዳዳ እስታሁን አለ!

ኤዲያ እኔኮ አልረባም …. ከፀረ ሰላም ሃይሎችና ከሻእቢያ ተላላኪዎች ጋር እየዋልኩ ልፅፍልህ የተነሳሁትን ሃሳብ ትቼ ነዘነዝኩህ ይቅር በለኝ!

እና አንተ እንዴት ነህ ጃል? እድገቱ እንዴት ይዞሃል? ስራስ ጥሩ ነው? ያው አንተማ የለት አሸባሪህን ይጣልልህ እንጂ ምን ትሆናለህ? ቀልብህ ያልወደደው ላይ እጅህን እየጠቆምክ እንጀራህን ትበላለህ። ይብላኝ እንጂ ለኔ!

እኔማ ወዳጄ … ኑሮ አስረአንድ ለባዶ እየመራኝ ያ የምታውቀው ወዜ እንደጤዛ ተንኖ አመድማ ሆኜልሃለሁ! ወይ አንደኛዬን ተማርሬ ጫካ አልገባሁ ፣ ወይ እንደምንም ውጪ ሃገር ሂጄ «Shame on you» ለማለት አልበቃሁ! ወይ እንዳንተ ለመንግስቴ አድሬ ወሳኝ የስራ ሂደት ሃላፊ አልሆንኩ! በቃ ድህነቴን እንደካባ ደርቤ አድገሃል ሲሉኝ «ይሁን» እያልኩ። ተጨቁነሃል ሲሉኝ «እሺ» እያልኩ ካፔቴኗ እንደጠፋባት መርከብ ነፋሱ ወደመራኝ ስኳትን ይኸው ሁለት ፀጉር አበቀልኩ!

ንግግሬን አለልክ እንዳረዘምኩት ይገባኛል ይቅር በለኝ ካድሬውዬ! መቼም እንደኔ ያለው በተስፋ ያደገና በቀን ሶስት ግዜ ጤፍና ጀሶ የሚበላ ሰው አእምሮው ልክ አይሆንም ታውቃለህ! ሆድ ይብሰዋል! እህ ብለው ከሰሙት የሃያአምስት አመት ብሶቱን በመዘብዘብ ወሳኝ ግዜህን ይሻማል። ቢሆንም ካድሬውዬ ቢሆንም … ታግሰህ አድምጠኝና ለያቄዬ ቪ.ፒ.አር.ን ተግባራዊ ያደረገ አፋጣኝ ምላሽ ስጠኝ!

እኔ ምለው ካድሬውዬ …. ለመሆኑ እንዴት ነው የቻልክበት በሞቴ? ከምስኪኖች ጉረሮ የተመነተፈውን እንጀራ መብላቱን እንዴት ቻልክበት? የሚሊየኖች ደምና እምባ እንደወንዝ በየጎዳናው ሲፈስ በውስኪ መራጨቱን እንዴት ቻልክበት በሞቴ? እስቲ ንገረኝ ካድሬውዬ? የህዝብ እትብት ላይ የተተከለ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ያለጭንቀት ተኝተህ ማደር የቻልከው በምን ተአምር ነው ጃል? ምስኪን እናት ጌጧን ሸጣ የሰራችውን ደሳሳ ጎጆ ፈገግ ብለህ አፍርሰህ እንዴት ወደቤትህ ገብተህ የህፃናት ልጆችህን አይን አየህ? እስቲ ልጠይቅህ ወዳጄ … አንድ ምስኪን ላይ በሃሰት መስክረህ እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ ብለህ እንዴት እጅህን ታጠብክ? እስቲ ልጠይቅህ ወዳጄ …. ሰው እንዴት በእምባ ታጥቦ ንፁህ ነኝ ማለት ይቻለዋል? ሰው እንዴት ቅርፄን ላስተካክል ብሎ የደም ውቂያኖስ ውስጥ ይዋኛል? እስቲ ንገረኝ ካድሬው ዘመዴ … በደሃ ጩኸት እስክስታ ስትወርድ ምንም አልቀፈፈህም?

ያው እኔማ ታውቃለህ  …. ወይ አንደኛዬን ለእግዚሃሩ አድሬ ቆሎዬን እየቆረጠምኩ ጮማህን አልተፀየፍኩ! ወይ በጅቦች ድግስ ላይ አብሬህ ተገኝቼ «ከፍርምባው ቁረጥ ፣ ዳቢቱንም ወዲህ በል» እያልኩ ከርሴን አልሞላሁ። እንዲሁ በአሸዋ በተቦካ እንጀራ ጥርሴን እየጨረስኩና ንፁህ ዳቢት እየናፈቀኝ አመድ ውስጥ የሰነበተ ሙዝ መስዬ አለሁልህ!

እናም ቢመረኝ ነውና ይሄን ደብዳቤ መፃፌ አባል በሆንክለት ፓርቲ ስም እማፀንሃለሁ እቺን ተናገረ ብለህ እራትህን እንዳታበስልብኝ አደራ!

ምን መሰለህ ካድሬውዬ … እኔ ብታሰር የመንግስትን እህል ከመጨረስ ውጪ ምንም ጥቅም የሌለኝ ሰው ነኝ። ጀርባዬ ቢጠናም ቀምበር ከሸረከተው ሰምበር ውጪ ምንም አይገኝም! ህገ መንግስቱን በሃይል ለማፈራረስ በሚል አይከሱኝ ነገር አይደለም ህገመንግስትን የሚያህል ተራራ የናቴን ቤት እንኳ ከመፍረስ ያላስጣልኩ ኮሳሳ ሰው ነኝ! ሽብርተኛ ነው ብለህ ብትጠቁመኝ ራሱ «ሽብርተኛና ችግርተኛ መለየት አቃተው» ብለው ነው ራስህን ሚገመግሙህ!

ይህን ሁሉ ምልህ መታሰርን ፈርቼ እንዳይመስልህ የተከበርከው ወዳጄ!
መቼም በዚህ ዘመን እታሰር ይሆን ብሎ ሚፈራ ሰው እሱ ወይ ከኢትዮጲያ ውጪ ነው ኑሮው ፣ አሊያም ህገወጥ ደላላ ወይም ኪራይ ሰብሳቢ ነው ማለት ነው! (ባንተ አማርኛ)

እውነቴን እኮ ነው ካድሬውዬ  ….. አሁን ማን ይሙት የኢትዮጲያ ህዝብ በሙሉ ተሰብስቦ ቢታሰር ምን ያጣል? በልማት ስም የማይፈርስ ወህኒ ቤት ብዙ ምስርና ሽንኩርት ያለበት ወጥ በእንጀራ በቀን ሶስቴ እየበላ ይኖራል እንጂ!
አስበው እስቲ …. የታሰረ ሰውኮ የቤት ኪራይ አይከፍልም። ምን እበላ? ብሎ አይጨነቅም። ስራ ለመቀጠር ኮቴው እስኪያልቅ በእግሩ አይኳትንም! ከኖህ መርከብ በላይ ብርቅዬ የሆኑ ታክሲዎች ውስጥ ለመሳፈር አይሰለፍም! የጤፍ ዋጋ መወደድ አያስበረግገውም! የዘይትና የነዳጅ ዋጋ ግሽበት አያስጨንቀውም! በቃ የታሰረ ሰው አንድ ማድረግ ሚጠበቅበት ነገር ወንጀሉን ማመን ብቻ ነው!
«አሸባሪ ነህ» ሲሉት
«አዎ» ካለ ሰላም ነው።
«የሻእቢያ ተላላኪ ነህ» ሲሉት
«እንዴታ!» ብሎ ያለማንገራገር ካመነ በቃ ሰላም ነው። እና የታሰረ ሰው ምን ይሆናል ብዬ ልፍራ ወዳጄ? እንደምታውቀው  በዚች ሃገር  የረባ ስራ ሳይሰሩ በመንግስት የሚቀለቡት እኮ አንተን መሰሎችና እስረኞች ብቻ ናችሁ!

አይ እኔ ርእሴን ትቼ የማያገባኝ ቦታ ገባሁ አሁንም?  አየህ ጀሶ ሚበላ ሰው ካድሬውዬ? እኔ ልጠይቅህ ያሰብኩት ሌላ በከፊል ከአሸዋና ከጀሶ ብዛት ወደሃውልትነት እየተቀረ የመጣው እጄ ሚፅፈው ደግሞ ሌላ !

መፍትሄውን ንገረኝ ነው ምልህ በቃ! ህሊናህና ሆድህ ሳይጣሉ ለዘመናት እንዴት አንተ ትብስ ፣ አንተ ትብስ ተባብለው ኖሩ? የጌቶችህ ድግስ ላይ እንደቡችላ ፍርፋሪ ስትለቅም ህሊናህ እንዴት «ሆዳም» ብሎ አልሰደበህም? እንዴት ከአንዳንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪነት ወጥተህ «ህዝብ» መሆን አልናፈቀህም? ንገረኝ ባክህ ካድሬው?
እንዴት የወንድምህ ህመም አላመመህም? እንዴት ልጆችህን ስታይ በየመንገዱ የወደቁ ህፃናት በአይነህሊናህ ድቅን አላሉም? ልጆችህ ነገ የሚሏትን ሃገር እያቆረስክ እንዳጎረስካቸው ሲያውቁ የሚያዩህ የንቀት አስተያየት እንዴት አልታየህም? መቼም ዘልአለም የሚቆይ ዙፋን የለምና የተደገፍከው ጉልበተኛ እንደሸንበቆ ሲሰበር ህዝብ እግር ስር እንደምትወድቅ እንዴት ማሰብ ተሳነህ ወዳጄ? እባክህ ካድሬውዬ መልስልኝ ….. ሆድና ህሊናህን በምን ቋንቋ አግባባሃቸው?

እኔማ ህዝብ ነኝ ምን አውቄ ብለህ? ላንተ ነው ምንገድለው ሲሉኝ «እሺ» ላንተ ነው ምንሞተው ሲሉኝ «እንዴታ» እያልኩ …. ኮብልስቶን ጠርቤ ፣ ኮብልስቶን በልቼ ፣ ኮብልስቶን የምንተራስ ምስኪን ነኝ! በቀራጮች መሃል ንፁህ እንጀራን ሳስስ ረሃብ የሚያጠናግረኝ፣ የህሊናዬን ጥያቄ ስመልስ የሆዴ ጩኸት የሚያባንነኝ ፣ በጀሶና በሸክላ ከተለወሰ ማእድ እየተቋደስኩ በከፊል ሃውልት ሆኜ የቀረሁ ምስኪን ዜጋ!

ይቀጥላል !

Filed in: Amharic