>

የአንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ የአቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ

1918 – 2009 ዓ.ም

በጥበቡ በለጠ

veteran-journalist-and-author-negash-gebre-mariamበኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የዩኒቨርስቲ ምሩቅ የሚባሉትና በሙያቸው በርካታ ጉዳዮችን ያበረከቱት የአንጋፋው ጋዜጠኛ የአቶ ነጋሽ ገ/ማርያም ስርዓተ ቀብር ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በሰአሊተ ምህረት ቤተ-ክርስትያን አያሌ ሰዎች በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ቀብራቸው ተፈፀመ፡፡
ነጋሽ ገ/ማርያም በኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኝነትን ሙያ ካስፋፉና ካጎለበቱ ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ከጋዜጠኝነት ሕይወታቸው በተጨማሪ አንጋፋ ደራሲ እና ፀሐፌ- ተውኔትም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ተስፉ ከአባታቸው ከአቶ ገብረማርያም ተስፉና ከእናታቸው ከወ/ሮ ምንትዋብ አሊ በአርሲ ክፍለ ሀገር በአርባጉጉ አውራጃ ልዩ ስሙ ሚኒ በሚባል ስፍራ በ1918 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ገና በህፃንነታቸው ዘመን ከእናታቸው ጋር ወደ ሀረርጌ ክፍለ ሀገር መጥተው በጨርጪር አውራጃ በሐብሮ ወረዳ መቻራ ከተማ አደጉ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ጂልቦ በሚባል ስፍራ አያታቸው ፊታውራሪ አሊ ቢሊ ቤት ከሌሎች ህጻናት ጋር ፊደል ቆጥረው ማንበብና መፃፍ ተማሩ፡፡
በ1933 ዓ.ም ከታላቁ ወንድማቸው ከአቶ አሰፋገብረማርያም ተስፉ ጋር ወደ አሰበ ተፈሪ ከተማ በኋላም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምሀርታቸውን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡
በ1936 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተቋቁሞ በነበረው መምህራን ማሰልጠኛ ት/ቤት ገብተው በጊዜው ይሰጥ የነበረውን የሁለት ዓመት ኮርስ ከአጠናቀቁ በኋላ፤ ለአንድ ዓመት ያህል ጅማ መምህራን ማሰልጠኛ አስተምረዋል፡፡
አቶ ነጋሽ በትምህርታቸው በበለጠ ለመግፋት ይጓጉ ስለነበረ፤ በ1938 ዓ.ም ኮተቤ በሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡
በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገብተው ሁለት ዓመት ያህል የወደብ አስተዳደር ኮርስ አጠናቀው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተወሰነ ጊዜ ሰርተዋል፡፡
የባንኩን ስራ ትተው በአሜሪካን ቤተመፃህፍት ውስጥ በቤተመፃህፍት ኃላፊነት kበትርጉም ስራ ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ የአሜሪካ መንግስት ለሁለት ዓመት በሰጣቸው ስኮላርሺፕና እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት የሁለት ዓመት ትምህርት እንዲቀጥሉ ባደረጉላቸው እርዳታ በአሜሪካን አገር በሞንታና ስራኪዮስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተከታትለው በBA (ቢ.ኤ) ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡
አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በማስታወቂያ ሚኒስተር ለ15 ዓመት አገልግለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስኪጅ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል፡፡
አቶ ነጋሽ ገብረማርያም በሙያቸው ጋዜጠኛ ብቻ አልነበሩም፡፡ ደራሲም ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም “ሴተኛ አዳሪ” የተሰኘውን ልብወለድ መጽሐፍ “ከእናኑ አጎናፍር” በሚል የብዕር ስም ጽፈው ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡
በ1965 ዓ.ም “የድል አጥቢያ አርበኛ” የተሰኘ ተውኔት ጽፈው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ለህዝብ በመድረክ ቀርቧል፡፡ እንዲሁም በ1975 ዓ.ም በህዝቡ ዘንድ አድናቆትና እውቅና ያተረፉላቸውን “የአዛውንቶች ክበብ” የተሰኘ ቲያትር ወይም ተውኔት በብሔራዊ ቲያትር ለህዝብ አቅርበዋል፡፡
አቶ ነጋሽ ለተለያዩ መጽሔቶች ፅሁፍ በማቅረብና የዘመኑን ወጣቶች የጋዜጠኝነት ሙያ በማስተማር ረገድ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አቶ ነጋሽ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ተካፋይ እየሆኑ ህዝቡን አገልግዋል፡፡
በ25መድረክ ያልታዩ “ሐመልማል” “እንደወጡ ቀሩ” የሚሉ ተውኔቶችና “ስንት አየሁ” የሚል ልብወለድ መፅሐፍ አዘጋጅተው በህዝብ ዘንድ እንዲታወቅ የተቻላቸውን ያህል ሲደክሙ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የስነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በሚሰጠው ሽልማት አቶ ነጋሽ ገ/ማርያም በጋዜጠኝነት የ1994 ዓ.ም የህይወት ዘመን ሽልማት ተሸላሚ ነበሩ፡፡
አቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም በዘመዶቻች በወዳጆቻቸውና በባልጀሮቻቸው ዘንድ የተወደዱና የተከበሩ ትሁት ሰው ነበሩ፡፡ አቶ ነጋሽ ባለትዳር፣ የሁለት ልጆችና አንድ የልጅ ልጅ አባት ነበሩ፡፡ አቶ ነጋሽ ገ/ማርያም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

Filed in: Amharic