>
2:51 am - Wednesday February 1, 2023

እርቅ ትርጉም የሚኖረው ህዋሃትን የሚፈታተን ኢትዮጵያዊነትን....

እርቅ ትርጉም የሚኖረው ህዋሃትን የሚፈታተን ኢትዮጵያዊነትን የተጎናጸፈ ተቋሞች፣ እንደ ጦር ሰራዊት፣ እንደኢሳት እና ሌሎችም ሚድያዎች፣ ስናቋቁም ብቻ ነው።

ግዛው ለገሰ

ሕወሃት የአማራ አገልጋዮቹን በአማራ ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ መቀሌ ጠርቷቸዋል። ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። በ1983 ስልጣን እንደያዙ እንድሪያስ እሸቴን እና ታምራት ላይኔን (ልክ ነኝ?) አስማራ ይዘው ለአማራው ይቅርታ ማስጠያቃቸው የሚታውስ ነው።

በተለምዶ አሸናፊዎች በተለይ ስላጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ ሆደሰፈነት ይቅርባይነት ቻይነት ትልቅነት (magnanimity) ያሳያሉ። በትንሽ በትልቁ አሸናፊነታቸውን አያሳዩም፤ ትኩረታቸው አገር ግንባታ ተኮር ስለሚሆን የሚገዙትን ህዝብ ልዩነት ሳይሆን አንድነቱን ጠላትነቱን ሳይሆን ወዳጅነቱን ተሸናፊነቱን ሳይሆን አሸናፊነቱን ይናገራሉ።

ከአገዛዙ ውጭ ያሉ ደጋፊ ምሁራንም ተሸናፊውን ወገን ለማጽናናት፣ ቁስሉን ለማሻር ይሞክራሉ፣ በአንጻሩ አሸናፊውን ለውጥ ማሻሻያ ይጠይቃሉ። ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ልማት ይጠይቃሉ።

የህወሃት የትግራይ ምሁራን ስነልቦና ከዚሁ ሁል የተለየ ነው። ህወሃት ትልቅነት፣ ሆደሰፊነት፣ የለውም ማሸነፉን አንተ ተሸናፊነትህን በየቀኑ በየአጋጣሚው ይንግርሃል፣ ታሪክህን፣ ብህልህን፣ ሃይማኖትህን ይሰድባል። ከቤትህ እስከእድርህ እስከቤት አምልኮህ ልቆጣጠር ካልሆን ዋ ይልሃል። በአደባባይ ይሰድብሃል። ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ አክራሪ ወዘተ ይልሃል። ሲፈልግም ማሰብ ያስተማርኩህ፣ ነጻነት መጠየቅ ያስተማርኩህ፣ ስኳር ያለው ሻይ መጠጣት ወይንም ጤፍ መብላት ያስተማርኩህ እኔ ነኝ ይልሃል።

አሁን አሁን ከትግራይ ብሄርተግኖች የምናየው ይህን ነው። ገለውህ እራሳቸውን ተጠቂ አርገው ማቅረብ ብቻ ሣይሆን ይቅርታ ጠይቅ ንስሃ ግባ ይሉሃል። ባለፈው አመት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልልች በተንሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ከሽህ በላይ ህይወት ጠፍቷል። በቢሾፍቱ እና በባህር ዳር መቶዎች በህወሃት ጥይት እናቶች ልጆቻቸውን አጥተዋል።  በአንጻሩም የነሱን ቁጥር ብንወስድ እንኳን ጥቂቶች ተፈናቅነዋል፣ እኔ እስከማውቀው የጠፋ ህይወት የለም። ታዲያ ዛሬ ከአሸናፊዎቹ መንደር የምናየው ለሞቱት ማዘን ወይንም ለወላጆች ማዘን ሳይሆን፣ እነሱ ተጠቂ ሆነው ይቅርታ መጠየቅ ነው።

የዘር ፖለቲካን አምጠው ወልደው፣ የመንግስት ፖሊሲ አድርገው ዛሬ ሌሎችን በዘረኝነት ይከሳሉ፣ የወልቃይትን፣ የራያን ማንነት ቀማተው ሌላውን በማንነት ስርቆት ይወነጅላሉ። እንሱ ያካለሉትን ድንበር ካልተቀበልክ እነሱን የጻፉትን ሃገ መንግስት ካላመለክ የእነሱን የቃላት ሸፍጥ (Doublespeak) ካልተቀበልክ፣ የእነሱን ኋላ ቀር የዘር ፖለቲካ ካለተቀበልክ የእንሱን ልበ ወልድ ታሪክ ካልተቀበልክ መንጋ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ ተብለህ የ”ዴሞክራሲያዊ ብሄርትኝነት” ጣላት ትባላለህ።

ምናልባትም ዴሞክራሲያዊ ብሄርትኝነት የህወሃትን እና የትግራይ ብሄርትኞችን ክስረት፣ የቃላት ሸፍጥ የሚገልጥ የልም። ዴሞክራሲያዊ ብሄርትኝነት በጠባብነት እና በትምክህተኝነት የተቀመጠ በትግራይ ብሄርተኞች የሚተረጎም የትማ አገር የሌለ መሳሪያ ነው። አማራ ወይንም ኢትዮጵያው ከሆንክ የዘር ፖለቲካን አላቀበልም ካልልክ ትምክህተኛ፣ የዘር ፖለቲካው ከህወሃት ቁጥጥር  ይውጣ ካልክ ጠባብ ተብለህ ጠላት ትባላለህ።

ይህ ሁሉ እውነት እንዳለ ሆኖ አብረን ከመኖር ውጭ ሌላ ምርጫ የለም።  ይህ እንዲሆን እርቅ የግድ ነው። የ”አማራ ሽማግሌዎች” መቀሌ ሄደው ይቅርታ መጠየቅ ወይንም በንልደቱ እና አየለ ጫሚሶ የሚደረግ የቁጩ ድርድር ወይንም በሃይሌ ገብረስላሴን እና በፕሮፌሰር አፍሬም ይስሃቅ የሚደረግ እርቅ ዋጋ የለውም። ነጋ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ወይንም አባይ ጸሃዬ እርቅ ቢጠረ እርቅ አይወርድም። እርቅ ትርጉም የሚኖረው ህዋሃትን የሚፈታተን ኢትዮጵያዊነትን የተጎናጸፈ ተቋሞች፣ እንደ መከላከያ፣ እንደኢሳት እና ሌሎችም ሚድያዎች፣ ስናቋቁም ብቻ ነው።

Filed in: Amharic