>
8:31 am - Sunday January 29, 2023

ኢህአዴግ እና ፀጉራም ውሻ አንድ ናቸው!

እውነት ለዕውቀት ብቻ ተገዢ ነው!

ኢህአዴግ እና ፀጉራም ውሻ አንድ ናቸው!
 (ስዩም ተሾመ)

በአንድ ወቅት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ የነበረ ሰው የፌስቡክ ጓደኛዬ ነበር። ፅኁፎቼን በደንብ ይከታተላል። ከፌስቡክ ይልቅ በድረገፅ ላይ በማወጣቸው የትንታኔ ፅሁፎች ላይ እንዳተኩር ይመክረኛል። ታዲያ አንድ ቀን አዲስ አበባ ስትመጣ እንድደውልለት ጠየቀኝ። እኔም አንድ ቀን አዲስ አበባ፥ ቦሌ አከባቢ ከሚገኝ ካፌ ቁጭ ብዬ ደወልኩለት። ልክ ስልኩን እንዳነሳ “የት ነህ?” አለኝና ያለሁበትን ነገርኩት። ከአስር ደቂቃ በኋላ ከነበርኩበት ካፌ መጣና መኪያቶ አዘዘ። ጋጋታ የለ፥ ግርግር የለ… ብቻ ብዙ አመት እንደሚተዋወቁ ጓደኞች ተጨዋወትን።

በጨዋታችን መሃል አንድ በጣም የሚያስቅ ነገር ነገረኝ። “እኔ የኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢብኮ – EBC) የቦርድ ሰብሳቢ ነኝ። ነገር ግን፣ አንድም ቀን ኢብኮን ተመልክቼ አላውቅም። እኔ የማልመለከተውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሕዝብ እንዲመለከተው መጠበቅ አግባብ አይደለም” አለኝ። የሰውዬው ግልፅነትና አነጋገር እስካሁን ድረስ ያስቀኛል። ቀጠለና ደግሞ ከአንድ ቀን በፊት ያወጣሁትን “ኢህአዴግ አፍን ይዞ ከኋላ መምታት ለማፈንዳት” የሚለውን ፅሁፍ እንዳነበበውና ሃሳቡ እንደተመቸው ነገርኝ። “አየህ…እንዳንተ ያሉ ፀሃፊዎች ያስፈልጉናል” ሲለኝ “እኔ’ኮ የምፅፈው በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ሆኜ ነው” አልኩት። “አዎ…ይገባኛል! ነገር ግን፣ ሰው ሃሳብና አመለካከቱን ለመግለፅ መፍራት የለበትም” አለኝ። በእርግጥ የተናገረው ነገር ትክክል ነው። እኔም የፈራሁት ነገር አልቀረልኝም።

ከላይ ከገለፅኩት አጋጣሚ ሁለት ነገሮችን ለመረዳት ያስችለናል አንደኛ፡- የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመንግስት ሚዲያዎች ከእውነት የራቀ መረጃ እንደሚቀርብ በደንብ ያውቃሉ። ሁለተኛ፡- በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርተው የሚናገሩና የሚፅፉ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ያለ አግባብ ለእስራት፥ እንግልትና ስደት እየተዳረጉ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በዚህ መሰረት፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከመንግስት ሚዲያዎች እውነተኛ መረጃ መስማት ይፈልጋሉ። ነገር ግን፣ እውነትን መናገር ስለሚፈሩ በቃላትና በቁጥር የታጨቀ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ። በተመሳሳይ፣ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ዘገባና ትንታኔ የሚያቀርቡ የግል ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እንዲኖሩ ይሻሉ። ነገር ግን፣ እውነቱን መስማት ስለሚፈሩ ስለ እውነት የሚናገርና የሚፅፍ ጋዜጠኛና ጦማሪን እያሳደዱ በሽብርተኝነት ወንጀል ይከሳሉ።

ይሁን እንጂ፣ በመንግስት የሚዲያ አውታሮች የቀረበው ዘገባ ሳይውል፥ ሳያድር በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በውስጡ የታጨቀው ውሸትና ግነት ይጋለጥና ፕሮፓጋንዳው እርቃኑን ይቀራል። ስለዚህ፣ የኢትዮጲያ ሕዝብ ኢህአዴግ የደበቀውን እውነት ሆነ የተናገረውን ውሸት ወዲያው ለይቶ ያውቀዋል። በዚህ ምክንያት፣ የኢህአዴግ መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተዓማኒነትና ተቀባይነት ከቀን ወደ ቀን እየተመናመነ መጥቷል። ለምሳሌ፣ እ.አ.አ. በ1989 ዓ.ም በምስራቅ አውሮፓ የኮሚኒዝም ስርዓት እንዳልነበር ሆኖ ሲወድቅ የመጨረሻ እስትንፋሱ የነበረው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ነበር። “’ፀጉራም ውሻ አለ’ እያሉት ይሞታል” እንደሚባለው፣ አምባገነን መንግስትም በቴሌቪዥን “ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ” እያለ ይሞታል።

የኢህአዴግ መንግስት ልክ እንደ ፀጉራም ውሻ ውስጡ ተበልቶ አልቋል። በእርግጥ ውሻ የሚሞተው የሰውነት አካላቱ በበሽታ ስለተጠቃ ነው። መንግስት ደግሞ የሚሞተው በሕዝብ ዘንድ ያለው ተዓማኒነትና ተቀባይነት ተመናምኖ ሲልቅ ነው። ምክንያቱም፣ አንድ መንግስት ሀገርና ሕዝብ መምራት የሚችለው በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት (public opinion) አመካኝነት ነው። የኢህአዴግ መንግስት ውሸት እየተነገረ እውነትን ለመደበቅ የሚያደርገው ጥረት በብዙሃኑ አመለካከት ተፅዕኖ ማሳረፍ ተስኖታል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢህአዴግ መንግስት ውሸት ሲናገር ሰሚ አያገኝም፣ እውነት ቢናገር እንኳን የሚያምነው አጥቷል። በመሆኑም፣ የኢህአዴግ መንግስት በቴሌቪዥን “አለሁ” እያለ እንደ ፀጉራም ውሻ ከመሞቱ በፊት መሰረታዊ ችግሩ በግልፅ ሊነገረው ይገባል። በዚህ መሰረት፣ ከሃሳብና የአመለካከት ነፃነት ጋር በተያያዘ “የኢህአዴግ መንግስት መሰረታዊ ችግር ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ በሚከተሉት ሁለት መርሆች ላይ ተንተርሼ ችግሩን ለማስረዳት እሞክራለሁ።

1ኛ፡- የሃሳብ/መረጃ ትክክለኝነት ከእውነትነቱ ተነጥሎ አይታይም!

የኢህአዴግ መንግስት በሚዲያ ሕጉ አማካኝነት በግል የሚዲያ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርገው፣ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንና የመብት ተሟጋቾችን ለእስር፣ ስደትና እንግልት የሚዳርግበት ዋና ምክንያት የተሳሳተ ሃሳብና መረጃ ወደ ሕዝቡ በማድረስ አመፅና ብጥብጥ ያስነሳሉ በሚል ነው። ይሁን እንጂ፣ የሃሳብና መረጃ ትክክለኝነት ከእውነትነቱ ተለይቶ አይታይም። ምክንያቱም፣ ሕዝብ ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርብለትን ሃሳብና መረጃ ዝም ብሎ ተቀብሎ ተግባራዊ አያደርግም። ይህን ፅንሰ-ሃሳብ “John Stuart Mill” እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-

“The truth of an opinion is part of its utility. If we would know whether or not it is desirable that a proposition should be believed, is it possible to exclude the consideration of whether or not it is true? You do not find those who are on the side of received opinions handling the question of utility as if it could be completely abstracted from that of truth.” On Liberty፡ Ch. 2. Of the Liberty of Thought and Discussion፣ Page 18

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የአንድ መረጃ ተቀባይነት ከትክክለኝነቱ፣ ትክክለኝነቱ ደግሞ ከእውነትነቱ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ሕዝቡ ከማንኛውም ወገን የቀረበለትን መረጃ ተቀብሎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከመጀመሩ በፊት በቅድሚያ የመረጃውን ትክክለኝነት ወይም እውነትነት ያረጋግጣል። ተቃዋሚዎች፥ የግል ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን ሆኑ የመብት ተሟጋቾች ያቀረቡት ሃሳብና መረጃ በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው ትክክልና ጠቃሚ ስለሆነ ነው። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት ያለው ብቸኛ አማራጭ እውነታውን ተቀብሎ ሥራና አሰራሩን ማሻሻል ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ውሸትና ግነት የበዛበት ሃሳብና መረጃ በማቅረብ ሕዝቡን ለማሳመን መሞከር ግን ሞኝነት ነው። የኢህአዴግ መንግስት ስህተት መስራቱ ሳያንስ ስህተቱን ለመሸፈን የተሳሳተ ወይም የተጋነነ ሃሳብና መረጃ ማቅረቡ “ሞኝን እባብ ሁለቴ ይነክሰዋል” እንደሚባለው ዓይነት ነው። በአጠቃላይ፣ የኢህአዴግ መንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት በጎደለው ሥራና አሰራሩ ሕዝቡን ማማረሩ ሳያንስ በተጨባጭ የሚያውቀውን እውነት በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለመደበቅ መሞከሩ የባሰ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ያሳጣዋል።

2ኛ፡- ለብቻ የተናገሩት እውነት እንደ ውሸት ይቆጠራል

ከላይ 1ኛ ላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት የተሳሳተ ሃሳብና መረጃ በማቅረብ አመፅና ብጥብጥ ያስነሳሉ በሚል ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል። ለምሳሌ፣ የፀረ-ሽብር አዋጁ ከወጣ በኋላ ባሉት አምስት አመታት ውስጥ ብቻ አስር ጋዜጠኞች ሲታሰሩ 57 ደግሞ ሀገር ለቅቀው ተሰድደዋል። በዚህ ምክንያት፣ አሁን ላይ የኢህአዴግ መንግስት ብቻውን በማውራት ላይ ይገኛል። በሀገር ውስጥ ካሉ የግል ሚዲያ ተቋማት አብዛኞቹ የመንግስት ደጋፊዎች ሲሆኑ የተቀሩት “ከፖለቲካ ነፃ” የሆኑ ናቸው። የኢህአዴግ መንግስት ብቸኛ ተናጋሪ በመሆኑ ውሸት ቀርቶ እውነት ቢናገር አንኳን ተቀባይነት አያገኝም። አድርጎታል። በድጋሜ ወደ “John Stuart Mill” መፅሃፍ በመሄድ የዚህ ምክንያት እንመልከት፡-

“There can be no fair discussion of the question of usefulness when an argument so vital may be employed on one side, but not on the other. And in point of fact, when law or public feeling do not permit the truth of an opinion to be disputed, they are just as little tolerant of a denial of its usefulness. The utmost they allow is an extenuation of its absolute necessity, or of the positive guilt of rejecting it.” On Liberty፡ Ch. 2. Of the Liberty of Thought and Discussion፣ Page 19

በአጠቃላይ፣ የኢህአዴግ መንግስት ራሱን ብቸኛ ተናጋሪ አድርጎ ማቅረቡ በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ሆኖበታል። ምክንያቱም፣ የሕዝብ አመለካከትና አስተያየት የሚቀየረው ከአንድ ወገን ብቻ በሚቀርብ ሃሳብና መረጃ አይደለም። የኢህአዴግ መንግስት ለሕዝቡ የሚያቀርበው ሃሳብና መረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከሌላ ተፃራሪ ሃሳብና መረጃ ጋር መጋጨት፥ መፋጨትና እውነትነቱ መረጋገጥ አለበት። በመሰረቱ፣ ሃሰት ወይም ውሸት በሌለበት እውነት ትርጉም የለውም፣ ወይም መጥፎነት በሌለበት ጥሩነትን ማድነቅ አይቻልም። የኢህአዴግ መንግስት እንደ “EBC” እና “FBC” ባሉ ሚዲያዎች ለሕዝቡ የሚያቀርበው ሃሳቦችና መረጃዎች ተዓማኒነትና ተቀባይነት እንዲያገኙ በ“OMN” እና “ESAT” በመሳሰሉ ሚዲያዎች ከሚለቀቁ ሃሳቦችና መረጃዎች ጋር መጋጨትና መፋጨት አለባቸው። በዚህ መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ለራሱ ሲል እንደ “OMN” እና “ESAT” ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዋና ስቱዲያቸውን በአዲስ አበባ እንዲያደርጉ ድጋፍና ማበረታታት አለበት። እንዲህ አንደ አሁኑ ብቻውን እያወራ የሚቀጥል ከሆነ ልክ እንደ ምስራቅ አውሮፓ አምባገነን መንግስታት በቴሌቪዥን “አለሁ” እያለ ይወድቃል

Ethiopian Think Tank Group

Filed in: Amharic