>
5:16 pm - Tuesday September 28, 2021

ልዕልት የሺመቤት ዓሊ ጋምጩ እጅግ ብዙ የተነገረላቸው ንጉሠ ነገሥት እናት ምንም ያልታወሱ የወሎ ልዕልት

በይኼይስ ምትኩ ኃይሌ

Werilu WELOበየትኛውም ዘመን የሚነግሡ ነገሥታት ታሪክና ገድል ጠንካራና ደካማ ጎኖች በወቅቱ በነበሩት የታሪክ ጸሐፊዎች ተሰናድተው ለትውልድ እንዲተላለፉ ይደረጋል፡፡  አዲሱ ትውልድ በቀደመው ትውልድ የተሠሩትን ሥራዎችና ታሪካቸውን ለማወቅና ለመመራመር የታሪክ ሰነዶችን ማገላበጥ የግድ ይላል፡፡ ነገሥታት አንዳንዴ በሠሩት ሥራ ልክ አንዳንዴም ከሠሩት ሥራ በላይ ይነገርላቸዋል፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ የነገሥታት ታሪክ ቢኖርም አንዳንዶቹ ከቆይታቸውና ከሥራቸው አንፃር ብዙ የተባለላቸውና የተጻፈላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ አፄ ዮሐንስ የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከደርቡሾች ጋር ባደረጉት ተጋድሎ ትውልድ ያስታውሳቸዋል፡፡ አፄ ምኒልክ የአፍሪካውያን ድልና ኩራት በሆነው የዓድዋ ድልና ዘመናዊነትን ለኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ባደረጉት አስተዋጽኦ ትውልድ ሁሌም ይዘክራቸዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የአገር አንድነትን ለመጠበቅ፣ ዘመናዊነትን ለኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ በመሞከራቸውና የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ መቅደላ ላይ የሠሩትን ተጋድሎ በታሪክ ሁሌም ይታወሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክና የፖለቲካ ተሳትፎ ወይም አገሪቱን በመምራት ረጅም ዘመናት ያስቆጠሩት ተፈሪ መኰንን በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአገሪቱ ዘመናዊነትን ለማስፋፋት ባደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ የአፍሪካ አንድነትን ምሥረታና ተያያዥ ታሪኮች ጋር ሁልጊዜ ስማቸው ጎልቶ ይሰማል፡፡

በአዲስ አበባ ሰኔ 26 እና 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ምሥረታና ዕድገት ላይ ላደረጉት አስተዋጽኦ በኅብረቱ ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ተወስኗል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ታሪክና የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን አልጋ ወራሽ በመሆን ለ13 ዓመታት ቢያሳልፉም ከንግሥቲቱ በበለጠ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ሁሉም የታሪክ ጸሐፊዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

ከ1923 እስከ 1967 ዓ.ም. በአገራችን የቅርብ ታሪክ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ታሪክ በተነሳ ቁጥር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ መነሳቱ የግድ ነው፡፡

እኚህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለ58 ዓመታት (1909-1967) ጉልህ ሚና የነበራቸው ንጉሠ ነገሥት ከተወለዱ ዛሬ 125 ዓመት ሆናቸው፡፡ የዚህ አጭርና ታሪካዊ ጥያቄ ያላት ጽሑፍ መነሻ የንጉሠ ነገሥቱን ታሪክ ለማውሳት አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ብዙ ተጽፎላቸዋል፡፡ ብዙ ተነግሮላቸዋል፡፡ ብዙ ተዚሞላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን እኚህ በአገራችን ታሪክ ግዙፍ ስፍራ ያላቸው ንጉሠ ነገሥት፣ በአፍሪካ አንድነት ቀዳሚ ሚና የነበራቸውና በዚህም ምክንያት አፍሪካውያን በአንድ ድምፅ ለሠሩት ሥራ ሐውልት እንዲቆምላቸው የወሰኑላቸውን ንጉሥ የፈጠረው ማሕፀን ግን ሲወሳ ወይም ታሪኩ ሲነገርለት አይሰማም፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከእናታቸው ከወ/ሮ የሺመቤት (የአባታቸውና የአያታቸው ስም ሳይጠቀስ) እና ከአባታቸው ከልዑል መኰንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም. በቀድሞ አጠራር በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ጀርሳ ጎሮ ተወለዱ የሚለው ታሪክ በተደጋጋሚ ተጽፏል፡፡ አባታቸው ልዑል መኰንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳንም በተመለከተ በርካታ ገድሎቻቸውን፣ የሚወዱት ምግብና መጠጥ ሳይቀር ቁመናቸውና የሚለብሱት ልብስ ጨምሮ በፎቶ በማስደገፍ በተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎች ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕይወቴና የኢትዮጵያ ዕርምጃ በማለት በ1965 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው የልጅነት ሕይወታቸውን በተመለከተ ሲገልፁ፣ አባቴ ልዑል ራስ መኰንን የታላቁ የሸዋ ንጉሥ የሣህለ ሥላሴ ልጅ የልዕልት ተናኘ ወርቅ ልጅ ናቸው፡፡ በማለት ይቀጥሉና አባታቸውም የዶባና የመንዝ ባላባት ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ወልደ መለኮት ልጅ ናቸው ይላሉ፡፡ ይህ ሌሎች የታሪክ ጸሐፊዎች ራስ መኰንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ የሚለውን የአያታቸውን ስም ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው፡፡ እንዴት ጉዲሳ ወደ ወልደ መለኮት እንደተቀየረ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህንን ለታሪክ ተመራማሪዎች እተወዋለሁ፡፡

የወረኢሉ ታዋቂ የኦሮሞ ባላባት ከነበሩት ዓሊ ጋምጩ የሚወለዱት ልዕልት የሺመቤት ከሌሎቹ የአገራችን ባለ ታሪኮች አንፃር የተባለላቸው ወይም የተጻፈላቸው ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በርካታ የታሪክ ጸሐፊዎችን ያዘጋጁትን የታሪክ ሰነድ ስናገላብጥ የምናገኘው የንጉሡን ወይም የንጉሡን አባት ታሪክ እንጂ የልዕልቷን ታሪክ አናገኝም ወይም ቢገኝም እጅግ በጣም በጥቂቱ ነው፡፡

በተለይ የቀድሞ ታሪክ ጸሐፊዎች የልዕልቲቷን ታሪክ ሊጽፉ ቀርቶ አባት ወይም አያት የሌላቸው እስኪመስል ወይም የአባትና የአያታቸውን ስም ላለመጻፍ የተማማሉ እስኪመስል ድረስ ከስማቸው ውጭ የአባትና የአያት ስም ማለትም ዓሊ እና ጋምጩ የሚለውን አይጠቅሱም፡፡ ንጉሡ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ እንኳን የእናታቸው ሙሉ ታሪካዊ ዳራ ሊፃፍ ቀርቶ በአገራችን የስም አጠራር እንደሚደረገው የእናታቸውን አባትና አያት ስም አልተጠቀሰም፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብዬ ሁል ጊዜ ራሴን ብጠይቅ መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች መልስ እንደምትሰጡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የሺመቤት ዓሊ ጋምጩ ማናቸው?

ልዕልት የሺመቤት እናታቸው ወ/ሮ ወለተጊዮርጊስ የምሩ ሲባሉ፣ አባታቸው ደግሞ ዓሊ ጋምጩ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በቀድሞ አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት ወረኢሉ አውራጃ (አሁን ደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ) ዶሉ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከ20 ዓመት በፊት በወረኢሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር ሆኜ በማገለግልበት ወቅት የአካባቢውን ታሪክ የያዘ አጠር ያለ ታሪካዊ የጥናት ጽሑፍ ለትምህርት ቤቱ አቅርቤ ነበር፡፡

ጥናት ከቀረበባቸው ታሪካዊ የአካባቢው ጉዳዮች አንዱ የልዕልት የሺመቤት ዓሊ ጋምጩ ታሪክ ነበር፡፡ የልዕልቷ ቤተሰቦች ማለትም ተወላጆቻቸው በማነጋገር ጥርት ያለና ታሪኩን እንደወረደ ለመጻፍ ተሞክሯል፡፡ የልዕልቷ አራተኛና አምስተኛ ተወላጆች በአካባቢው በሕይወት ስላሉ የሚያውቁትንና ከቀደምት ቤተሰቦቻቸው የተነገራቸውን ምንም ሳይሸራረፉ ቃል በቃል ነግረውኛል፡፡

የተወለዱበት ቦታ ሳይቀር በአካል በመገኘት አይቼዋለሁ፡፡ አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባላውቅም በወቅቱ እጅግ በጣም ትልልቅ ዕድሜ ጠገብ ዛፎችና በመፈራረስ ላይ የሚገኝ ቤትና አጥር ነበረው፡፡ ልዕልት የሺመቤትን የተመለከተ የሰነድ ማስረጃ ማግኘት ግን አልቻልኩም፡፡ ይህ ምናልባትም ልዕልቲቷ አካባቢውን በሕፃንነታቸው ስለለቀቁት ይመስለኛል፡፡ ዘውዴ ረታ ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ በሚባለው መጽሐፋቸው ገጽ 18 ላይ፣ ወ/ሮ ወለተ ጊዮርጊስ ከወረኢሉ ባላባት ከሼሕ ዓሊ የወለዷትን ሴት ልጅ ይዘው ወደ ሸዋ ለመመለስ የቻሉት አፄ ምኒልክ ከቴዎድሮስ አምልጠው ከተመለሱ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሕፃኗ የሺመቤት የአራት ዓመት ልጅ ነበረች፤ ይላሉ፡፡ ይህ የሚያመለክተው ልዕልት የሺመቤት አካባቢውን የለቀቁት በሕፃንነታቸው ስለነበር ታሪካዊ የሰነድ ማስረጃዎች በአካባቢው አለመገኘቱ ግልጽ ነው፡፡

ልዕልት የሺመቤት፣ ሐሰን ዓሊና ስናፍቅሽ ዓሊ የሚባሉ ሁለት ወንድምና እህት ነበራቸው፡፡ ሆኖም ግን በእናት የሚገናኙ አይመስለኝም፡፡ የስናፍቅሽና የሐሰን ዓሊ ተወላጆች ወረኢሉና ጃማ ወረዳ በብዛት ስለሚገኙ የልዕልቷን ታሪክ መፃፍ ለሚፈልጉ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በተለይ የስናፍቅሽ ዓሊ ልጅ የነበሩትና በኃይለ ሥላሴ ጊዜ የጃማ ወረዳ (በደቡብ ወሎ የሚገኝ ወረዳ ነው) አስተዳዳሪ የነበሩት ፊታውራሪ ከበደ ባንተ አይምጣ የአባቴ የቅርብ ጓደኛ ስለነበሩ ቤታችን እየመጡ ስለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተሰብና አንዳንድ ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከአባቴ ጋር የሚያደርጉት ውይይትና ጭውውት ሁልጊዜ አስታውሰዋለሁ፡፡

የፊታውራሪ ከበደ ልጆች ጋር አብሮ አደጎች ስለሆንን ይኼንን የታሪክ ማስታወሻ ሳዘጋጅ ኑሮዋን ጃማ ወረዳ ያደረገችውን ልጃቸውን ወ/ሮ ተዋበች ከበደን በስልክ አናግሬአት ነበር፡፡ በማዘጋጀው ማስታወሻ ደስተኛ ብትሆንም የልዕልት የሺመቤት ዓሊ ጋምጩ ታሪክ አስታዋሽ ማጣቱ ግን ቅር እንዳሰኛት አልሸሸገችኝም፡፡

በቅርብ የታተመውና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 241 ላይ፣ እናቱ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን) የሺመቤት ዓሊ ጋምጩ በአባትዋ በኩል የወረሂመኑ ኦሮሞ ናት፡፡ በአዲሱ ግኝት መሠረት ይብረሁልሽ በተባለችው ሥልጤ ጉራጌ እናትዋ ‘ቂቶ’ ትባል የነበረችው አያትዋ ወ/ሮ ወለተ ጊዮርጊስ የወሎው ኦሮሞ ነብይ የሼሕ ሁሴን ጅብሪል ልጅ ናት፡፡ ይህ ማለት ሼሕ ሁሴን ጅብሪል የአፄ ኃይለ ሥላሴ ቅድመ አያት ናቸው ማለት ነው፤ በማለት ጽፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ፍጹም ስህተት የሆነ የታሪክ ግድፈት ነው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሼሕ ሁሴን ጅብሪልም ሆነ ከወረሂመኑ ተወላጆች ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ልዕልት የሺመቤት ዓሊን የሚያውቅና ስለ እሳቸው አንጀት አርስ ጽሑፍ የተጻፈው በፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ነው፡፡ እኚህ ግለሰብ በልዕልቲቷ ቤት ያደጉ በመሆናቸው ደግነታቸውን፣ ባህሪያቸውን፣ መልካቸውንና ከዚያም ባሻገር ዘግናኝ አሟሟታቸውንም ሒደት ጽፈውልናል፡፡

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት፣ የሕይወቴ ታሪክ በሚባለውና በ1998 ዓ.ም. ቤተሰቦቻቸው ባሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 32 ላይ፣ ተክለ ሐዋርያት ልዕልት የሺመቤትን መጀመሪያ ያዩዋቸው ቀን የነበረውን ሁኔታ ሲገልፁ ወ/ሮ የሺመቤት በጣም ወፍራም ብስል ቀይ ናቸው፡፡ ቆንጆ ናቸው፡፡ ሹሩባቸው በትከሻቸው ላይ ተንዘርፍፏል ይላሉ፡፡ በእርግጥ ቁንጅናቸውን ለመመስከር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መልክ ማየት በቂ ይመስለኛል፡፡

ራስ መኰንን ቤት አገልጋይ ሆኜ ቤተሰብ ነበርኩ የሚሉት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ልዕልት የሺመቤት ደግና ሩህሩህ መሆናቸውንም በዚሁ ከላይ በተገለጸው መጽሐፋቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ሐረር በነበሩበት ወቅት በተፈጠረባቸው በሽታ ምክንያት የሰውነታቸውን መጎዳት ልዕልት የሺመቤት በማየታቸው በወቅቱ የተፈጠረው ሲገልፁ፣

እንኮዬ ተመዋረድ (የልዕልቲቱ አገልጋይ) መዳኔን ለእመቤቴ ነግራቸው ኖሮ አምጪው ብለዋት ወሰደችኝ፡፡ ባዩኝ ጊዜ ደነገጡ ‹‹ምነው አቡነ ተክለ ሃይማኖት! እንዴት ከሳ! አወይ ልጄን ክፉኛ ተጎድትዋል፡፡ አብሽሬ እባክሽ አብሊልኝ በቶሎ እንዲያገግም እንድታጎርሺው›› ማለታቸውንና በዚሁ በተደረገላቸው ቤተሰባዊ እንክብካቤ ከበሽታቸው ማገገማቸውን ጽፈዋል፡፡

በመጨረሻም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታናሽ ወይም አሥረኛ ልጃቸውን ሲገላገሉ የተፈጠረውን የልዕልት የሺመቤት አሟሟት ገጽ 45 ላይ በዓይን ያዩትን በዝርዝርና ልብ በሚነካ ስሜት የጻፉትን እንዲህ አንብቡት፡-

መጋረጃ ተጥሎ እመይቴ ያቃስታሉ ከወደ ጀርባ ዞርኩና ወደ እመይቴ ተጠጋሁ፡፡ ከመሬት በላይ ከፍ አድርገው አስቀምጠዋቸዋል፡፡ እግሮቻቸውን አንፈራጠው ጋለል ብለው ተደግፈዋል፡፡ ምጥ ይዟቸዋል፡፡ አንዲት የአደሬ ሴት (ስሟ ተዘነጋኝ ቡሽሮ ነው ይመስለኛል) አዋላጃቸው ነች ተብላ አለቃ ሀብተ ማርያም አስመጥተዋል፣ ከእመይቴ እግሮች ስር ተቀምጣ ትጠባበቃለች፡፡ ሴቶቹ ከመጋረጃ ግቢ ሲያገኙኝ ጊዜ የተመዘዘ ካራ ሰጡኝ ከእመይቴ ራስጌ አቆሙኝ እንደዚህ የጎራዴውን ደንደስ ከጫንቃዬ ላይ አስደግፌ እጠባበቃለሁ፡፡ ሴቶቹ ይማጠናሉ ‹‹ማርያም ማርያም›› ይላሉ፡፡ እኔም እንደነሱ ልመናዬን አፋጠንኩ፡፡

ምጡ እመይቴን አልጎዳቸውም ሴቶቹ መማጠናቸውን ተዉና ድምፃቸውን በጣም ዝቅ አድርገው ተንሾካሾኩ ልጅ መወለዱን በመላ አወቅሁ፡፡ ነገር ግን ድምፁን አልሰማሁትም አዲስ የተወለደውን ልጅ ወደ ጓዳ ያሸሹት መሰለኝ፡፡ አለቃ ሀብተ ማርያም ወደ ጓዳው ውስጥ እየገቡ እየወጡ እየተመላለሱ ከሴቶቹ ጋር ይነጋገራሉ፡፡ በኋላ ልጁን ወዴት እንዳደረሱት ለማወቅ አልተቻለኝም፡፡ እንደዚህ እመይቴ ተገላግለው ጥሬ ቅቤ ከራሳቸው ላይ በጉሎ ቅጠል ለጠፉላቸው፡፡ እመይቴ ውኃ ለመኑ፡፡ ‹‹እባካችሁ ውኃ ስጡኝ›› አሉ፡፡ አለቃ ሀብተ ማርያም ወተት እንዲሰጧቸው አዘዙ፡፡ ወተቱን በቀመሱ ጊዜ እመይቴ ተቆጡ ‹‹በጦም አስገደፋችሁኝ አቡነ ተክለሃይማኖት ይወዱላችኋል›› እያሉ አማረሩ፡፡ አለቃ ሀብተ ማርያም ቄሶች አስገቡና እግዚአብሔር ይፍታ አሰኝተው ‹‹ንስሐ በኋላ መቀበል ነው እንጂ ምንም ኃጢአት የለበትም›› እያሉ አጽናኗቸው፡፡ ውድቅት አለፈ የእንግዴ ልጅ አልወርድ ብሎ አስቸገረ ማታ የተገላገሉ ከዶሮ ጩኸት በኋላ እንኳ ሳይወርድላቸው ቆየባቸው፡፡ ሊነጋ አቅራቢያ ተዳከሙ መናገር ያቅታቸው ጀመር ሰውነታቸው በጣም ወፍሮ ነበርና ጉዳት በዛባቸው፡፡ እየቆዩ ሴቶቹ ሁሉ ተጨነቁ ያለቅሳሉ እኔም እየተጨነቅሁ አለቅሳለሁ እንቅልፍና ድካም አልተሰሙኝም፡፡ አለቃ ሀብተ ማርያም ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ አዋላጅዋ እጅዋን ትታጠብና ጣቶችዋን አስገብታ ቀስ ብላ የእንግዴ ልጁን ወደ ውጪ እየሳበች ታስወጣው ብለው አልጎመጎሙ፡፡ ሴቶቹ ይህን በሰሙ ጊዜ ፊታቸውን አኮማተሩ ለቅሶም አበረቱ፡፡ አዋላጅዋ እንደታዘዘቸው አደረገች እመይቴ ክፉኛ ተንሰቀሰቁ ድምፃቸውን ልቤን ነካው የባሰውን እንባዬ ፈሰሰ፡፡ እመይቴ ጮሁ ‹‹ኧረ ገደላችሁኝ፣ እባካችሁ ስለ አቡነ ተክለሃይማኖት ጥቂት አስተንፍሱኝ ምነው ጨከናችሁብኝ! ምን አልኳችሁ…›› አዋላጅዋ ፋታ አልሰጠቻቸውም ዝም ብላ ትጎለጉላለች እመይቴ ተዳከሙ ተዝለፈለፉ በዙሪያቸው ደጋፊዎች በዙ፡፡ ሊነጋ ነው ወፎች መንጫጫት ጀመሩ ጭለማው ሊገፍ ነው ጧት በማለዳ እመይቴ አረፉ፤ ይላሉ፡፡

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ልዕልት የሺመቤት ከላይ በተገለጸው በዘግናኝ ሁኔታ በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ቢገልጹም የተወለደው ልጅ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይሁኑ ሌላ አልገለፁም፡፡ ዘውዴ ረታ፣ ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ልዕልቲቱ የሞቱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከተወለዱ በኋላ ቀጥሎ የተፀነሰውን ልጅ በሚወልዱ ጊዜ ነው ማለታቸውና በንጉሡ የተጻፈው ሕይወቴና የኢትዮጵያ ዕርምጃ በሚለው መጽሐፍ ላይ፣ እናቴ ወ/ሮ የሺመቤት ገና የሠላሳ ዓመት ዕድሜ እያሉ በ1886 ዓ.ም. መጋቢት 6 ቀን አርፈው ሐረር በጥምቀተ ባሕር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ፣ የሚለው ሲታይ ልዕልቲቷ ያረፉት ንጉሡ ከተወለዱ ከሁለት ዓመት ገደማ መሆኑን ያመለክታል፡፡

በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራቸው ሰዎች በየትኛውም አገር እንደሚደረገው ሐውልት ይቆምላቸዋል፣ ሙዚየም ይዘጋጅላቸዋል፣ ይጻፍላቸዋል፡፡ አንዳንዴም ይዜምላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ልዕልት የሺመቤት በወረኢሉ ከተማ ከሚገኘውና ደርግ ‹‹ድል በዓል›› ብሎ የሰየመውና በኋላ ወደ ቀድሞ ስሙ ከተመለሰው ‹‹ልዕልት የሺመቤት›› ተብሎ ከሚጠራው መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጭ ለስማቸው መጠሪያ ምንም ዓይነት ማስታወሻ አይገኝም፡፡ በወቅቱ የታሪክ መምህር በነበርኩበት ወቅት ያየሁትና የተወለዱበት አካባቢ፣ ቤትና ግቢ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ ሆኖም ግን በተቃራኒው ስለልጃቸው ታላቅ ሥራ ብዙ ተብሏል፣ ተጽፏል፣ ሐውልትም ሊቆም ነው፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም ባሻገር ይህን በአገራችን ታሪክ ግዙፍ ስፍራ ያለውን ባለታሪክ ያፈራ ማሕፀን ብናስታውሰው፣ ብናወሳውና ብንጽፍለት ተገቢ ይሆናል እላለሁ፡፡ ቸር ሁኑ፡፡

በመጨረሻም ይህንን የታሪክ ማስታወሻ ስጽፍ ዋናው ዓላማዬ የተዘነጉትን ልዕልት ለማስታወስና የታሪክ ተመራማሪዎች ተገቢውን እንዲሠሩ ለማስታወስና ለመጠቆም ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yiheyis.lawoffice@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Filed in: Amharic