>
3:24 am - Tuesday January 31, 2023

የልጅነት ትዝታችን የነበሩት አባባ ተስፋዬ አረፉ (ዘመድኩን በቀለ)

    [ ከ1916 – 2009 ]
         ነፍስ ይማር

ababa-tesfayeይሄ ጦማር የሚገባው እንደእኔ ላሉና እግራቸውን ታጥበው የአባባ ተስፋዬን ” የልጆች ክፍለ ጊዜን ” ጥበቃ በቴሌቭ3ዥን መስኮት ላይ አፍጠው ይጠባበቁ ለነበሩ ለእኔ ዘመን ትውልድ ብቻ ነው ። ለእነ ቼሪ ዘመን ትውልድ ብዙም ትርጉም ላይሰጥ ይችላል ። እኔ ግን ከምር አዝኛለሁ ። ስለእውነት ትዝታዬ ነው አብሮ የተቀበረው ።

“ደህና ናችሁ ልጆች.! ፤ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች፤  እንደምን አላችሁ ልጆች። አያችሁ ልጆች የኢትዮጲያ ቴሌቭዥን የልጆች ግዜ ዝግጅት ክፍል እናንተን ለማስደሰት ልክ በሰአቱ ይገኛል። እናንተስ ዝግጁ ናችሁ? አዎዎ አባባ ተስፋዬ ሸንተረሩን አቋርጠው ዳገቱን ወጥተው ቁልቁለቱን ወርደው በጓሮ በኩል ከተፍ ሲሉ እናንተ ደሞ ቆማችኋል አይደል? አዎዎ በቃ አሁን ተቀመጡ እንዳትጋፉ ታዲያ ትንንሾች ወደፊት ትልልቆች ወደኋላ አዎዎ።”

አባባ ተስፋዬ ሳህሉ ሰኔ 20 1916 ዓም ዓ.ም በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር ከዶ የተሰኘ አካባቢ ነበር ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ የተወለዱት ። አምስት ዓመት ሲሞላቸው አባታቸው ወደ ጎባ የተጓዙ ሲሆን ጎባ ላይ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው የትምህርት ጀምረዋል ። ቤተሰቦቻቸው በሹመት ምክንያት ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲሄዱ አባባ ተስፋዬም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይሄዱ እንደ ነበር የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል ። ጊኒር ፣ በሐረርም የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው እንደነበረና በመቀጠልም በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መቀጠላቸውም ነው የሚታወቀው ።

አባታቸው ሳህሉ የመባላቸውን ጉዳይ በተመለከተም አባታቸው ኤጀርሳ የራስ እምሩ ምክትል የነበሩት ፊታውራሪ ሳህሉ በሚመሩት ክፍል ውስጥ ስለነበሩ ፤ በዛን ወቅትም ስማቸውን ሲጠየቁ “ተስፋዬ ማን.?  ሲባል ተስፋዬ ሳህሉ ካላልኩ አልታወቅም ነበረ”በዚህ ምክንያትነት ማለታቸውም ተነግሯል ።

በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ግዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሃሳቡን አቅርቦ በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጲያ ህዝብ ዘንድ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለተከታታይ 42 ዓመታት በአባትነት ስሜት አቅርበዋል። ለልጆች የሚሆኑ የተዋዙ ተረቶችን፣ ጨዋታዎችን እና አስተማሪ ዝግጅቶችን የሚያቀርቡት አባባ ተስፋዬ ያበረከቱት መተኪያ የሌለው አስተዋጾ በብዙዎቻችን ዘንድ አይረሳም ።

ጀግናዎቿን ማክበር የማታውቅበት ኢትዮጵያችን ግን ለአባባ ተስፋዬም አልተመለሰችም ። በሁለት እግራቸው ቆመው እንቅልፍ አጥተው ካቋቋሙት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በክብር ይሰናበታሉ ተብሎ ሲጠበቅ ” በ2 መስመር ደብዳቤ ነበር ሁለተኛ እዚህ ድርሽ እንዳትል ” የሚል ይዘት ባለው ደብዳቤ ተገፍተው ተባረው የቀሩት ።

ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ።

የተባለው ስንኝ እዚህ ላይ መጥቶ ቢገጠም ልክክ ብሎ ቦታውን ይይዛል ።

አባባ ተስፋዬ ከ10 በላይ ሙያ ባለቤት እንደሆኑም ይነገራል።
ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ደራሲ (የልጆች ተረት)፣ ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የምትሃት ባለሙያም እንደነበሩ ይነገራል ።

አባባ ተስፋዬ የመድረክ ቲያትር ባለሙያም ነበሩ ። ተያትር በኢትዮጵያ ውስጥ ማቆጥቆጥ በጀመረባቸው  በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በወቅቱ ወደዚህ ሙያ የሚመጡ የሴት ተዋንያኖች ባለመኖራቸው ምክንያት የሴቶችንም ገጸባህሪ ወክለው ይጫወቱ እንደነበር ይታወቃል ። እነ ‘ሀ ሁ በስድስት ወር’ ፣ ‘ኤዲፐስ ንጉስ’፣ ‘አሉላ አባነጋ’፣ ‘ዳዊትና ኦርዮን’፣ ‘ኦቴሎ’፣ ‘አስቀያሚዋ ልጃገረድ’ና ‘ስነ ስቅለት’ አባባ ተስፋዬ ሳህሉ ከተጫወቷቸው ተውኔቶች ዉስጥ የሚጠቀሱ ሲሆን ‘ብጥልህሳ’፣’ ነው ለካ’ ፣ ‘ጠላ ሻጯ’ በድርሰት ያበረከቷቸው ተውኔቶች ሲሆኑ አራት የተረት መጻሕፍትም ለልጆች አበርክተዋል።

አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገሩ የነበሩ ሲሆን በገና፣ ክራር፣ መሰንቆ እንዲሁም አኮርዲዮን፣ ትራምፔት፣ ትርምቦንና ጃዝን አሳምረው ይጫወቱ ነበር ።

በትዳር ሕይወታቸውም ከባለቤታቸው ደብሪቱ አይታገድ ጋር አንድ ልጅ ያፈሩ ሲሆን አምስት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።

አንድም እኔ ነኝ ያለ ፣ ይኽ ነው የሚባልም ምራቅ የዋጠ የሀገር አድባር የሚሆን ጎምቱ አረጋዊ ሽማግሌ በዚህ ዘመን ሳይተካና ተስፋ የምናደርግበት አረጋዊ የሚከበር ሽማግሌ ሳናይ ፤ ተተኪም ሳይኖር እንደ አባባ ተስፋዬ ያሉ ትውልድ ቀራጭ ፣ የስነምግባር መምህር ማጣታችንን ባሰብኩ ጊዜ ትካዜ ይውጠኛል ። አባባ ተስፋዬ ኤርትራን ጨምሮ በቀድሞዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተወለዱ ህጻናት በሙሉ የስነምግባር መምህር የነበሩ አባት ነበሩ ። ዘር ፣ ሃይማኖት ፣ ፖለቲካ ሳይለዩ ሁሉን እኩል በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው ያስተማሩ ፣ የመከሩ ፣ የተቆጡ ፣ የገሰፁ ፣ ያበረታቱ አባት ናቸው አባባ ተስፋዬ ።

አባባ ተስፋዬስ ዕድሜ ጠግበው ፣ ሀገራቸውን አገልግለው ፣ ትውልድ ቀርጸው በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ። ይብላኝ ለእኛ ለቀሪዎቹ ። ምሳሌ የምናደርገው ለሌለን ። ነፍስ ይማር አባባ ተስፋዬ ፤ ነፍስ ይማር ።

አሁን እንግዲ ልብ ብላችሁ ተመልከቱልኝ ፤ በህይወት እያሉ ያለከበረቻቸው ፣ አረጋዊውን የሀገር አድባር ፣ የልጆች አስተማሪና መካሪ ፤ በብጣሽ ወረቀት አዋርዳ ከሥራ ገበታ አሽቀንጥራ የገፋች ሀገር ፤ በቁማቸው ቤታቸውን በላያቸው ላይ ለማፍረስ ያልዘገነናት ሀገር አሁን ከሞቱ በኋላ እንግዲህ RIP በሚሉ አሽሟጣጮች አየሩን ሉበከል ነው ። በስተ እርጅና የጡረታ ገንዘብ ነፍጋ አደባባይ ለአደባባይ እየተዟዟሩ ከልመና ባልተናነሰ ሁኔታ ተንከራተው የሰው እጅ እንዲያዩ ተደርገው የተገፉ አባት ነበሩ ፤ አበባ ተስፋዬ ።

አሁን የክብር ዶክትሬቱ ከየአቅጣጫው ይጎርፋል ። ፈንድ ሰብሳቢ በሞተ ሰው ሸቃዮች ፕሮጀክት ዘርግተው ፣ ሱፋቸውን ግጥም እንደደረጉ ለልመና ይሯሯጣሉ ፣ ቴሌቪዥኑ ፣ ራዲዮው ፣ ጋዜጣው ፣ ፌስቡኩም ሳይቀር አባባ ተስፋዬ ፣ አባባ ተስፋዬ አባባ ተስፋዬ እያለ ይታወካል

Filed in: Amharic