>
5:28 pm - Tuesday September 28, 2021

የፍቅር እስከ መቃብር - ፍቅር (ጥበቡ በለጠ)

fb_img_1502296282263የዛሬ ፅሁፌን እንዳዘጋጅ የገፋፉኝ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው በፍቅር እስከ መቃብር ላይ ተመርኩዞ የተሠራው የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ደብረማርቆስ ከተማ ላይ የተሠራው የታላቁ ደራሲ፣ ዲፕሎማትና አርበኛ የክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ ሐውልት ነው፡፡

ቴዲ አፍሮ /ቴዎድሮስ ካሣሁን/ ፍቅር እስከ መቃብርን መሠረት አድርጐ ግሩም የሆነ ሙዚቃ አቀንቅኗል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ርዕሠ ጉዳዮችን በተለይም ገፀ-ባህሪያቱን፣ ደራሲውን እና ተራኪውን ወጋየሁ ንጋቱን ሳይቀር ለዛ ባለው ሙዚቃው ሌላ ፍቅር ሰርቶላቸዋል፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ወደር የማይገኝለት ልቦለድ ታሪክ ነው፡፡

ፍቅር እስከ መቃብር ዘመን አይሽሬ /Eternal/ ብለን የምንጠራው የጽሑፎች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ታዲያ ወደዚህ መጽሐፍ ንባብ የገባ ሰው ሁሉ በመጽሐፉ ፍቅር ተሳስሮ እንደሚቀር ይታወቃል፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር መፅሐፍ በውስጡ ያለው ታሪክ ሲነበብ፣ አንባቢውን ራሱ በፍቅር ወጀብ አላግቶ፣ አላግቶ የፍቅር እስረኛ የሚያደርግ ተአምረኛ መጽሐፍ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮም በመጽሐፉ ፍቅር ወድቆ ይህን የመሰለ ግሩም ዜማ አቀነቀነ፡፡

ከራሳችን፣ ውስጣችን ካለው ታሪካችን ላይ መሠረት አድርጐ ሙዚቃ መስራቱ አንዱ ስኬቱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ኢትዮጵያዊ ቅርሶችና ታሪኮች ላይ መሠረት ተደርገው የሚቀርቡ የኪነ-ጥበብ ስራዎች የታዳሚን ቀልብ በቀላሉ የመውሰድ አቅም አላቸው፡፡ ከዚህ ሌላም ከያኒው ራሱ በሀገሩ ታሪክ ላይ ተመስጦ የጥበብ ስራዎቹን ማቅረቡም ምን ያህል የዕውቀት አድማሱም ሰፊ እንደሆነ ማሳያም ነው፡፡ አንድ ከያኒ የአገሩን እና የሕዝቡን ታሪክ ሲያውቅ በሕዝቡ ውስጥ ግዙፍ ሆኖ ብቅ ይላል፡፡

ቴዲ አፍሮ ፍቅር እስከ መቃብርን ሲዘፍነው የመጀመሪያው አቀንቃኝ አይደለም፡፡ በ1995 ዓ.ም እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ መጽሐፉን መሠረት አድርጋ “አባ ዓለም ለምኔ” የተሰኘ ውብ ዜማ አቀንቅናለች፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ መሠረት አድርጐ ዜማ ማቀንቀን እንደሚቻል ያሳየች ቀዳሚት ባለቅኔ ነች፡፡

ጂጂ ለቴዲ አፍሮ፣ የታላላቅ ርዕሠ ጉዳዮች መነቃቂያው /inspiration/ የሆነች ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ፍቅር እስከ መቃብርን እርሷ 1995 ዓ.ም ተጫውታዋለች፡፡ እርሱ ደግሞ በ2009 ዓ.ም ተጫወተው፡፡ አባይን በተመለከተ ጂጂ ከ15 ዓመት በፊት አቀንቅናለች፡፡ ቴዲ አፍሮ ደግሞ በቅርቡ ተጫውቶታል፡፡ አድዋን በተመለከተ ጂጂ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ድንቅ አድርጋ አዜመችው፡፡

ቴዲ አፍሮ ደግሞ እርሷ ካቀነቀነች ከ13 ዓመት በኋላ አድዋን ውብ አድርጐ ሠራው፡፡ ብዙ ነገሮችን ሳይ ጂጂ የቴዲ መነቃቂያ ትመስለኛለች፡፡ እርግጥ ነው ሁለቱም አቀንቃኞች የአንድ ዘመን ወኪሎች ናቸው፡፡ እነርሱ በተፈጠሩበትና ባደጉበት አስተሳሰብ ውስጥ ነው ማቀንቀን የሚፈልጉት፡፡ የርዕሠ ጉዳይ ምርጫቸውም ተመሳስሎ ማሳየቱ ከፈለቁበት ሕዝብና አስተሳሰብ ውስጥ ይመነጫል፡፡ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ እንዳሉት “ነበልባል ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ እና ቴዲ አፍሮ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን ሙዚቃ ባልተጠበቀ ፍጥነት ወደ ላይ አመጠቁት” ብለው ነበር፡፡ ኃይሌ ገሪማ ለጂጂ ሙዚቃ የነበራቸውን ፍቅር ሳስታውስ ወደር አላገኘሁላቸውም፡፡

ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር ብዙዎችን በፍቅር የጣለ መጽሐፍ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ ዲፓርትመንት ውስጥ ላለፉት 50 ዓመታት የጥናትና ምርምር ፅሁፎች ሲሰሩበት የኖረ መጽሐፍ ነው፡፡ አያሌ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የድግሪ፣ የማስተርስ እና የዶክተሬት ድግሪያቸውን ለማግኘት ፍቅር እስከ መቃብር ላይ የምርምር ፅሁፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ሌሎች ምሁራን ተመራማሪዎችም ፍቅር እስከ መቃብርን በልዩ ልዩ ርዕሠ ጉዳዮቹ ላይ ተመርኩዘው ጥናት ሠርተዋል፡፡

የውጭ አገር ሰዎች ሳይቀሩ መጽሐፉ ላይ ተመራምረዋል፡፡ መጽሐፉ በእንግሊዝኛ ቋንቋም ተተርጉሟል፡፡ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ፍቅር እስከ መቃብር የአያሌዎችን ቀልብ በመሳብ ወደር አይገኝለትም፡፡ ይህን መጽሐፍ በጥናትና በምርምር ፅሁፎቻቸው ከፍ ከፍ አድርገው የሰጡን ምሁራን ሁሉ ሊታወሱ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

በርዕሴ ላይ “የፍቅር እስከ መቃብር – ፍቅረኞች” ያልኩትም እነዚህን አካላት ሁሉ ለመጠቃቀስ ፈልጌ ነው፡፡ በዚህ መፅሐፍ ታሪክ ውስጥ ከሁሉም በላይ “ፍቅር” ናቸው ብዬ የማስበው ደራሲውን ክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁን ነው፡፡ ይሄን የሁላችንም ፍቅር የሆነውን መጽሐፍ 1958 ዓ.ም ያበረከቱልን የደራሲነት ግዙፍ ስብዕና ሐዲስ ዓለማየሁ እፊቴ ተደቀኑ፡፡ አቤት ትዝታ! ትዝ አሉኝ፡፡

በህይወት ዘመኔ እስካሁን በሠራሁበት የጋዜጠኝነት ሙያዬ ቃለ-መጠይቅ ካደረኩላቸው የዚህች አገር ፈርጦች መካከል በእጅጉ ደስ የሚለኝ ከእርሳቸው ዘንድ ሄጄ ስለ ብዙ ነገር ያጫወቱኝ ወቅት ነው፡፡ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁን በ1994 ዓ.ም እና በ1995 ዓ.ም ቃለ-መጠይቅ ያደረኩላቸው ሲሆን፤ ለሦስተኛ ጊዜ ለሌላ ቃለ-መጠይቅ ቀጠሮ በያዝንበት ቀን ህይወታቸው አለፈች፡፡ ክቡር ሐዲስ ሆይ ታላቅነትዎ፣ ከሁሉም በላይ ትህትናዎን ፈፅሞ አልረሳውም፡፡

ውድ አንባቢዎቼ፤ እስኪ አንድ ነገር እንጨዋወት፡፡ በዚሁ መፅሐፍ ውስጥ ሦስቱን ዋና ዋና ገፀ-ባህሪያት አስቧቸው፡፡ ሰብለ ወንጌልን፣ በዛብህን እና ጉዳ ካሣን፡፡ እነዚህ ሦስት ገፀ-ባህሪያት አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ አንድ የሚያደርጋቸው፣ ባሰቡት አቋማቸው፣ ለወደዱት ጉዳይ ፍፁም ራሳቸውን መስጠታቸው፣ በፍቅርና በዓላማ ተገማምደው እስከ ወዲያኛው ማለፋቸው፣ በአንድ ጉድጓድ መቀበራቸው አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ ፍቅር እስከ መቃብሩም እሱ ነው፡፡ ሦስት የሚያደርጋቸው ደግሞ ሦስቱም ከየራሳቸው የኋላ ማንነት እና ተፈጥሮ አመጣጣቸው የተለያየ መሆኑ ነው፡፡

እነዚህ ከሦስት ማንነት ውስጥ የወጡ የሐዲስ ዓለማየሁ ፍጡሮች የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሑፍ ዋልታና ማገር ሆነው እነሆ 50 ዓመታት ሙሉ ተገዳዳሪ ሳይኖርባቸው ብቻቸውን ውብ ሆነው እንዳማረባቸው አሉ፡፡

ሰብለና በዛብህ በሁለት ሰብአዊያን መካከል የሚንበለበል የፍቅር እቶን ውስጥ የተቀጣጠሉ ቢሆንም ከዚያ ባለፈ ደግሞ የሁለት ዓለም ሰዎችን ወክለው የአንድን ማኅበረሰብ አወቃቀር የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ሰብለ ከባላባት ወገን፣ በዛብህ ከአነስተኛው ማኅበረሰብ ክፍል፡፡ የነዚህ ሁለት ዓለም ሰዎች ፍቅር ውስጥ የሚመጣ ጉድ የተባለ ግጭት ፍጭት አለ፡፡

እናም ሐዲስ ዓለማየሁ ያንን የማኅበረሰብ አወቃቀር ልዩነትና አንድነት ሊያሳዩን ፍቅር ፈጠሩ፡፡ በፍቅር ውስጥ ያለ ማኅበረሰባዊ እቶን ሲፈነዳ ሲቀጣጠል አሳዩን፡፡ ጉዱ ካሣ የተባለ ጉድ ፈጥረውም ማኅበረሰቡን የሚያርቅ፣ የሚተች፣ የሚያሄስ፣ ችግሩን ነቅሶ የሚያሳይ እና መፍትሄ የሚሰጥ የሊቆች ሊቅ ወለዱ፡፡ የጐጃሙ ዲማ ጊዮርጊስ የቅኔ ዩኒቨርሲቲ ያፈራው ጉዱ ካሣ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ፣ በሥርዓት እንድትገነባ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

“የማኅበራችን አቁዋም የተሰራበት ሥርዓተ-ልምድ፣ ወጉ ሕጉ እንደ ሕይወታዊ ሥርዓተ-ማሕበር ሳይሆን ህይወት እንደሌለው የድንጋይ ካብ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ የላይኛው የታችኛውን ተጭኖ፣ የታችኛው የላይኛውን ተሸክሞ እንዲኖር የተሰራ በመሆኑ ከጊዜ ብዛት የታችኛው ማፈንገጡ ስለማይቀርና ይህ ሳይሆን ህንፃው በሙሉ እንዳይፈርስ እንደገና ተሻሽሎ ሰውን ከድንጋይ በተሻለ መልክ የሚያሳይ የህያውያን አቁዋም ማኅበር እንዲሰራ ያስፈልጋል፡፡”
 /ፍቅር እስከ መቃብር፤ ገፅ 122/

ለመሆኑ እንደ ጉዱ ካሣ አይነት ማኅበረሰባዊ ፈላስፋ አለን ወይ? አንዱ ሌላውን ተጭኖ መኖር እንደሌለበት የሚነግረን፡፡ አንዱ ሌላኛውን ከተጫነ ከጊዜ ብዛት የታችኛው እምቢ ብሎ ይወጣል፡፡ የታችኛው ሲወጣ ካቡ ይፈርሳል፤ ሀገር ይፈርሳል እያለ በውብ ምሳሌ ኢትዮጵያን የሚያስተምር የዲማ ጊዮርጊሱ ጉዱ ካሣ ጠቢብ ነበር፡፡

እናም ሐዲስ ዓለማየሁ እንዲህ አይነቶቹን ገፀ-ባህሪያት ፈጥረው፣ የፍቅር ልቦለድ የሆነ መነፅር ሰክተውላቸው ኢትዮጵያን እንድናያት፣ እንድንመረምራት እና የሚያስፈልጋትን ሥርዓት እንድንገነባላት እኚህ ጉደኛ ደራሲ ከ50 ዓመታት በፊት በውብ ድርሰታቸው ነግረውናል፡፡ ማን ይስማ!?
1994 ዓ.ም እቤታቸው ሄጄ ቃለ-መጠይቅ ሳደርግላቸው በውስጤ ብዙ ነገር ተመላለሰብኝ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር፡፡

በዛብህ ሞተ፡፡ ሰብለ ከበዛብህ ሌላ ፈፅሞ መኖር አትፈልግም፡፡ መነኮሰች፡፡ ቆብ ጫነች፡፡ እሷም ሞተች፡፡ አጐቷ ያ ታላቅ ፈላስፋ ለዕውነት ብሎ የኖረና የሞተው ጉዱ ካሣም ተቀላቀላቸው፡፡ እነዚህን ገፀ-ባህሪያት የፈጠሩት ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ እድሜና ጤና ተጫጭኗቸው በተንጣለለው ሳሎናቸው ውስጥ በተዘረጋው የማረፊያ አልጋ ላይ ጋደም ብለዋል፡፡ ትክ ብዬ አየኋቸው፡፡ ፍፁም ትህትና፣ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የመቅረብ ተፈጥሯቸው ይሄው እፊቴ ላይ ዛሬም አለ፡፡ ይታየኛል፡፡

ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ባለቤታቸው ወ/ሮ ክበበፀሐይ ከሞቱ በኋላ ምንም ዓይነት ትዳር አልመሰረቱም፡፡ ብቻቸውን ከቤተሰባቸው ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ ሳያገቡ፣ የአብራካቸውን ክፋይ ሳያዩ አረጁ፡፡ ደከሙ፡፡ እናም ገረመኝ፡፡ ግን ጠየኳቸው፡፡ “ጋሽ ሐዲስ፤ ባለቤትዎ ወ/ሮ ክበበፀሐይ ካረፉ በጣም ረጅም ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ በነዚህ ዓመታት ግን እርስዎ ምንም ዓይነት ሌላ ትዳር አልመሰረቱም፡፡

ይህ ለምን ሆነ? ምክንያትዎ ምንድን ነው?” አልኳቸው፡፡
ጋሽ ሐዲስ የግራ እጃቸውን ከፍ አደረጉልኝ፡፡ እጃቸው ላይ ቀለበት አለ፡፡ ግራ ስጋባ እንዲህ አሉኝ፡፡ ይህን ቀለበት ያሰረችልኝ ክበበፀሐይ ነች፡፡ እኔም ለእሷ አስሬያለሁ፡፡ እሷ ድንገት አረፈች፡፡ እዚህ ጣቴ ላይ ያለው እሷ ያሰረችልኝ ቀለበት ነው፡፡ ቀለበቱን አልፈታችውም፡፡ ሳትፈታው አረፈች፡፡ ስለዚህ ይህን ቀለበት ከኔ ጣት ላይ ማን ያውልቀው? ካለ እሷ፣ ካለ ክበበፀሐይ ይህን ቀለበት ከጣቴ ላይ የሚፈታው የለም አሉኝ፡፡

ለመሆኑ ከዚህ በላይ ፍቅር እስከ መቃብር አለ ወይ? ሐዲስ ዓለማየሁ ማለት የፍቅር እስከ መቃብር መፅሐፍ ዕውነተኛ ገፀ-ባህሪ ነበሩ፡፡ የፃፉትን ልቦለድ በእውናቸው የኖሩ የፍቅር አባት ናቸው፡፡ ሰብለወንጌል፣ በዛብህ እና ጉዱ ካሣ ማለት ሐዲስ ዓለማየሁ ናቸው፡፡ ፍቅርን ፅፈው ብቻ ሳይሆን ኖረውት ያለፉ እውናዊ ፍጡር! ጋሽ ሐዲስ፤ አቤት የስብዕናዎ ግዝፈት! እንዴት አድረጌ ልግለፀው?

የፍቅር እስከ መቃብር ፍቅረኞች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በዋናነት ራሳቸው ሐዲስ ዓለማየሁ ናቸው፡፡ ሌላው ይህን ታሪክ በጥብጦ ያጠጣን ተራኪው ወጋየሁ ንጋቱ ነው፡፡ መፅሐፉ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሊቃውንትም የመፅሐፉ ፍቅረኞች ናቸው፡፡ ጂጂ እና ቴዲ አፍሮም በመፅሐፉ ፍቅር ወድቀው እኛንም ጣሉን፡፡ ፍቅረኛው በጣም ብዙ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሁፍ ጣሪያውን ያሳዩን ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ደብረ-ማርቆስ ከተማ ላይ ሐውልታቸው ከሰሞኑ ቆመ፡፡ ምስጋና ለደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ! ይህች ደብረማርቆስ ሌላ እጅግ አስደናቂ ደራሲም ወልዳለች፡፡ ተመስገን ገብሬ ይባላል፡፡ በብዕሩም ሆነ በዕውቀቱ በዘመኑ ሊቅ የነበረ አርበኛ ነው፡፡

ተመስገንን ስጠራ ዮፍታሔ ንጉሴ መጣብኝ፡፡ ባለቅኔው፣ ተወርዋሪ ኮከቡ ዮፍታሔ ከዝህቺው ደብረማርቆስ ዙሪያ ሙዛ ኤልያስ ተወልዶ ያደገ የዚህች አገር የቴአትር፣ የመዝሙር፣ የግጥም ሊቅ የሆነ አርበኛ ነው፡፡ መላኩ በጐ ሰው የተባለ ልክ እንደ ዮፍታሄ ገናና የነበረ ሊቅም ከደብረማርቆስ ወጥቷል፡፡ የዛሬው ትውልድም ሐውልት ብቻ የሚሰራ እንዳይሆን የነዚህን ታላላቅ ሰብዕናዎች ማንነት መከተል ይገባዋል፡፡

በትውልድ ውስጥ እየተቀጣጠለ የሚሄድ ፍቅር የሰጡን ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ በሙዚቃው ጂጂን እና ቴዲ አፍሮን ቀልብ ወስደው ዛሬም እንደ አዲስ ፍቅር እስከ መቃብር ያሰኙናል፡፡ አቶ ሐዲስ ከአርበኝነቱ እና ከደራሲነቱ ባሻገር የሰሩትን መልካም ነገር ላስተዋውቅና የዛሬ ጽሁፌን ላብቃ፡፡
ሐዲስ ዓለማየሁ በድርሰት ስራዎቻቸው በኢትዮጵያዊን ዘንድ እጅግ ጎልተው ወጡ እንጂ መተዳደሪያቸው የመንግስት ስራ ነው።

የኢትዮጵያን መንግስት በአምባሳደርነት እና በሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ በተቋቋመችው ኢትዮጵያ ማለትም ከ1937 ዓ.ም እስከ 1938 ዓ.ም ድረስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ። ቀጥሎም በአሜሪካን ሐገር በዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያ ሌጋሲዮን ውስጥ ከራስ እምሩ ጋር ሆነው በአምባሳደርነት ለአራት ዓመታት ሰርተዋል። ኒውዮርክ ውስጥም የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ። ቀጥሎም ከኒውዮርክ መልስ ማለትም ከ1953-1958 ዓ.ም በለንደን እና በኔዘርላንድስ ውስጥ አገልግለዋል። ስለዚህ ሐዲስ በዋነኛነት አምባሳደር ነበሩ። በዚህ የአምባሳደርነት ስራቸው ደግሞ የዋሉትን ውለታ ዛሬ እንዘክረዋለን።

የፊታችን ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም 54ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫው ኢትዮጵያ እንደሆነ እስከ ዛሬ ድረስ አለ። ለዚህም ደግሞ በተከታታይ የመጡት የኢትዮጵያ መሪዎች አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው። የአፍሪካ ሕብረት ከመመስረቱ አራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ECA/ ነው። ይህ መ/ቤት ታህሳስ 20 ቀን 1951 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ተቋቋመ /ተመሰረተ/፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እንደ ዋነኛ ዓላማ አፍሪካን ለማጠንከርና ለማጎልበት ኢኮኖሚ ወሳኝ በመሆኑ በጋራ ትስስር ሐገሮች ወደ አንድ አህጉራዊ ህልም መምጣትን የሚያመቻች ተቋም ሆኖ አገልግሏል። ይህም የአፍሪካ ሐገሮች በጋራ ለሚያቋቁሙት የአፍሪካ ሕብረት እንደ መሰረታዊ የመአዘን ድንጋይ ሆኖ አስተዋፅኦ አድርጓል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ECA/ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን የደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው ያወሳል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከመቋቋሙ በፊት ሐዲስ ዓለማየሁ ኒውዮርክ ውስጥ በአምባሳደርነት ይሰሩ ነበር። እዚያ ሆነው አንድ ነገር አሰቡ። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሰረት። ይህን ሃሳባቸውን ለንጉሥ ኃይለስላሴ ፃፉ። በወቅቱ ንጉሡ በጉዳዩ ወዲያውኑ አልተስማሙም ነበር። ሐዲስ ዓለማየሁም ስለ ጉዳዩ ጠቀሜታነት በተከታታይ ደብዳቤ ይፅፉላቸው ነበር።

ንጉሥ ኃይለሥላሴ ለምን ወዲያው ሀሳቡን አልተቀበሉትም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነ የበርካታ ሐገር ዜጎችም አዲስ አበባ ውስጥ የስራ ቦታቸው ይሆናል። በዚህ የተነሳ ሁሉንም የሚታዘብ የውጭ ተመልካች ይመጣብናል። ስለዚህ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ይፋ ይሆናል። ይሔ ደግሞ ለመንግስት ስርዓት አመቺ አይሆንም በሚል ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ። በኋላ ግን በአዲስ አበባ ውስጥ እንዲቋቋም ጃንሆይ ፈቀዱ።
ዓፄ ኃይለሥላሴ ከመስማማታቸው በፊት ግን አራት ሐገሮች ጽ/ቤቱ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር። ከእርሳቸው ለአንደኛቸው ሊሰጥ በጥናት ላይ ነበር። በኋላ ኢትዮጵያ ስትጠይቅ ተሰጣት። እንዴት ተሰጣት የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነበር።

እንደ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ገለፃ ኢትዮጵያ ጽ/ቤቱ እንዲሰጣት ያደረገችው በዘዴ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው። ጽ/ቤቱን ገንዘብ አውጥቶ በቋሚነት የሚሰራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው። የሀገሮች ምላሽ ደግሞ ለጽ/ቤቱ መስሪያ የሚሆን ቦታ መስጠት ብቻ ነው። ሐገሮቹ የመስሪያውን ገንዘብ አያወጡም። ኢትዮጵያ ዘግይታ ጥያቄውን ስታቀርብ ግን አንድ መላ ቀይሳ ነበር። ይህም ቦታውን በነፃ እሰጣለሁ፤ የሕንፃውን ማሰሪያ ወጪም እራሴው እችላለሁ።

የተባበሩት መንግሥታት ገንዘቡን አያወጣም አለች። በዚህ ምክንያት ከኋላ የመጣችው ኢትዮጵያ የጽ/ቤቱ ምስረታን በአሸናፊነት ተቀበለች። ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁም በሕይወት ዘመናቸው እጅግ ደስ ያላቸው የዚያን ቀን ነው። ምክንያቱም ከበስተኋላ ሆነው የዚህ ሐሳብ ጠንሳሽም ግፊት አድራጊም እርሳቸው ስለነበሩ ነው።

ዛሬም ከአዲስ አበባ ከተማ ውብ ሕንጻዎች መካከል አንዱ የሆነው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ECA/ ጽ/ቤት የተመደበው ቦታ 26ሺ ሜትር ካሬ ነው። ስለዚሁ ኪነ-ሕንፃ አሰራር አቶ በሪሁን ከበደ በፃፉት መጽሐፍ እንዲህ ይላሉ
ሕንጻው የተለያዩ ክፍሎች አሉት። አንድ የጉባኤ አዳራሽ ፣ የኮሚቴ መሰብሰቢያዎች፣ ስድስት ክፍሎች ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሲዮን ሠራተኞችና ከዚህ ኮሚሲዮን ጋር የሥራ ግንኙነት ላላቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት ለጽ/ቤቶች የሚያገለግሉ 140 ክፍሎች፣ ከነዚህ ሌላ ለባንክ፣ ለፖስታ፣ ለቴሌግራፍና ለአየር መንገድ የሚያገለግሉ ክፍሎች አሉት።

ዋናው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የዝግጅቱ ፕላን ለሊቀ መናብርቶቹ የመቀመጫዎች ብዛት 8 ለዋና መልዕክተኞች 86፣ ለመልዕክተኞች 168፣ ለታዛቢዎችና ለልዩ ልዩ ወኪሎች 58፣ ለፀሐፊዎች 16፣ ለተርጓሚዎችና ለኦፕሬተሮች 16፣ ለልዩ ልዩ እንግዶች 37፣ ለጋዜጠኞች 106፣ ለተመልካች ሕዝብ 220 በድምሩ 715 መቀመጫዎችን የያዘ ነው።
ይህን ለመስራት የወሰደው ጊዜ 18 ወር ብቻ ሲሆን የጨረሰውም ገንዘብ አምስት ሚሊዮን አራት መቶ ሰላሳ ብር እንደሆነ አቶ በሪሁን ከበደ “የአፄ ኃይለስላሴ ታሪክ” በተሰኘው መጽሀፋቸው በገፅ 470 ውስጥ ገልፀዋል። በፅሁፋቸው ውስጥ እንዳብራሩት የጉባኤው አዳራሽ የተቀመጠበት ቦታ 3ሺ 600 ሜትር ካሬ፣ ለጽ/ቤቶቹና ለስድስቱ ኮሚቴዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ ስድስት ክፍል የፈጀው ቦታ 5500 ሜትር ካሬ፣ ለባንክ፣ ለፖስታ ቤት፣ ለቴሌግራፍና ለአየር መንገድ መ/ቤት የተሰራበት ቦታ 4500 ሜትር ካሬ እንደሆነ ጽሁፉ ያስረዳል።

ይህን ትልቅ ስራ ያከናወነችው ኢትዮጵያ ናት። ከበስተጀርባ ሆነው ታላቁን ሕልም እውን ያደረጉት ደግሞ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ናቸው። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ታህሳስ 20 ቀን 1951 ዓ.ም ተከፈተ።
ያ ወቅት ለብዙ የአፍሪካ ሐገሮች ጨለማ ነበር። ምክንያቱም ከቅኝ አገዛዝ ገና አልወጡም። በመከራ ውስጥ የሚዳክሩበት ነው። ከነርሱ ውስጥ ዘጠኝ ሀገሮች ብቻ ነፃ ወጥተው ነበር። እነርሱም
1- ኢትዮጵያ፣
2- ላይቤሪያ፣
3-  የተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ (ግብፅ) ፣
4- ሊቢያ፣
5- ሱዳን፣
6- ሞሮኮ፣
7-  ቱኒዚያ፣
8-  ጋና፣
9-  ጊኒ ነበሩ።
ለነዚህ ዘጠኝ ሀገራት የምታበራይቱ ፀሐይ ለሌሎም በቅኝ ግዛት ስር ለሚዳክሩት እንድታበራ ትግላቸውን ቀጠሉ። ሀገሮች ነፃ መውጣት ጀመሩ። ተበራከቱ። አፍሪካ ከባርነት ነፃ የወጣች አዲስ አህጉር ሆነች። ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ላይ ነፃ የወጡ 32 የአፍሪካ ሐገሮች አዲስ አበባ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን አቋቋሙ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከዚህም አልፎ የብዙ አስተሳሰቦችና ፍልስፍናዎችም ድምር ውጤት ነው።

ለምሳሌ የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍናዎችን የሚያራምዱ እነ ማርክስ ጋርቬይ፣ ኢትዮጵያዊው የህክምና ሊቅ ዶክተር መላኩ በያን እና ሌሎም ከ1920ዎቹ ጀምሮ የሚያቀነቅኗቸው አስተሳሰቦች እየሰፉ መጥተው የደረሱበት ደረጃ ነው። የአፍሪካ ህብረት! ጉዞው ገና ይቀጥላል። ፓን አፍሪካኒዝም ይመጣል። “United States of Africa” ይመጣል ተብሎም ይጠበቃል።

እነ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ሀሳቡ ጽንስ እንዲሆን አድርገዋል። ፅንሱም ተወልዶ እያደገ ነው። በ50 ዓመታት ውስጥ ሁሉም የአፍሪካ ሐገሮች ከቅኝ አገዛዝ ስርዓት ወጥተዋል። ቀጥሎም ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ፖለቲካቸውን፣ ኢኮኖሚያቸውን እያስተሳሰሩ መሔድ እንዳለባቸውም አውቀዋል።

የአፍሪካ ሐገሮች ትልልቅ ህልሞችን አልመው ነበር። ለምሳሌ በ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለ25 ዓመታት የሚቆይ ፕሮግራም በትምህርት ሚኒስቴሮቻቸው በኩል አቅደው ነበር። ይህም መሐይምነት ከአፍሪካ ምድር በ25 ዓመት ውስጥ እንዲጠፋ። ምክንያቱም በቅኝ የመገዛቱ አንዱ ምክንያት መሐይምነት ስለሆነ ነው። ግን ይሄ የ25 ዓመታት እቅድ አሁንስ እምን ደረጃ ላይ ነው ብሎ ማየት ከአፍሪካ ሐገራት ይጠበቃል።

ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ግን ለንጉሥ ኃይለሥላሴ እዲህ አሏቸው፡- መሐይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የትምህርት ሚኒስቴር በጀት በጣም ትንሽ ነው። መጨመር አለበት እያሉ በጣም ተከራከሩ። ሳይጨመርም ቀረ። በወቅቱ ሐዲስ የትምህርት ሚኒስቴር ነበሩ። በጀቱ አልስተካከል ሲል ሐዲስ ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ። በኋላም ወደ ለንደን አምባሳደር ሆነው ተላኩ። ሐዲስ ከሄዱ በኋላ የጠየቁት በጀት ተለቆ ነበር። የሚገርም ነው።

አፍሪካ የብዙ ነገሮች ሀብት ባለቤት ነች። ይህን ሐብቷን ተጠቅማ የበለፀገች አህጉር እንድትሆን የህብረቱ ትልቅ የቤት ሥራ ነው። ደራሲ ሐዲስም ከአስር ዓመታት በፊት እንደገለፁት ትምህርት ላይ ብዙ መስራት ተገቢ ነው።
በድርሰቶቻቸው የምናውቃቸው እኚህ ደራሲ ታላቅ ዲፕሎማት እንደነበሩ በጥቂቱም ቢሆን የዛሬው ፅሁፌ ያስረዳል። ሐዲስ ዓለማየሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። ከዚያም በምክትል ሚኒስትርነት ማዕረግ ሰርተዋል። በአምባሳደርነት አገልግለዋል። ግን አነሳሳቸው ከቆሎ ተማሪነት፣ ወደ መምህርትን፣ ከመምህርነት ወደ የቴአትር ፀሐፊነት፣ ከፀሐፊነት ወደ አርበኝነት ከአርበኝነት ወደ ዲፕሎማትነት እና ታላቅ ደራሲነት የመጡ ናቸው።
በድርስት ዓለም ውስጥ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ፅፈዋል። ለምሳሌ
1. የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም 1948 ዓ.ም
2. ፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ ታሪክ 1958 ዓ.ም
3. ወንጀለኛው ዳኛ (ልቦለድ) 1974 ዓ.ም
4. የእልምዣት (ልቦለድ) 1980 ዓ.ም
5. ትዝታ 1985 ዓ.ም

ከነዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ምን አይነት ስርዓት እንደሚያስፈልጋት እና ልዩ ልዩ ቴአትሮችን ከሰላሳ ዓመታት በፊት ሲፅፉ ኖረዋል።

እኚህ ደራሲና ዲፕሎማት በኢጣሊያ ወረራ ዘመን በአርበኝነት ሲታገሉ በፋሽስቶች ተማርከው ወደ ኢጣሊያ ሀገር ተግዘው ታስረዋል። ጣሊያን እስር ቤት ውስጥ እያሉ ኢትዮጵያ ከፋሽስቶች ወረራ ተላቀቀች። ግን ሐዲስ ከእስር አልተፈቱም ነበር። ሐገራቸውና ህዝባቸው ነፃ ሲወጡ ሐዲስ ገና ነፃ አልወጡም ነበር። በኋላ እንግሊዞች ጣሊያንን ሲወሩ ሐዲስ ዓለማየሁን እና ጓደኞቻቸውን እስር ቤት አግኝተዋቸው ለቀቋቸው። ወደ ሐገራቸው መጥተው የዲፕሎማትነት እና የደራሲነት ስራቸውንም የቀጠሉት ከዚህ በኋላ ነበር።
ሐዲስ ዓለማየሁ ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ቦታ የደረሱ የትውልድ ተምሳሌት ናቸው። “አባታቸው አለማየሁ ሰለሞን ከጎጃም ክፍለ ሐገር መተከል ወረዳ ኤልያስ ከተባለ የትውልድ አምባቸው ተነስተው ወደ ጎዛምን ወረዳ እንዶደም ኪዳምህረት ድንገት አቀኑ። በዚያው ከወ/ሮ ደስታ ዓለሙ ጋር ተገናኙ። ወ/ሮ ደስታ እንዶዳም ተወልደው፣ እንዶዳም አድገው፣ በኋልም ለወግ ማዕረግ በቅተዋል። ከአቶ ዓለማየሁ ሰለሞን ጋር ትዳር የመሰረቱት በዚሁ ቦታ ነው። በትዳራቸውም ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም የበኩር ልጃቸውን ሐዲስን ወለዱ” ብዙም አብረው ሳይቆዩ ተለያዩ፡ ፈጣሪ ያገናኛቸው ታላቁን ደራሲና ዲፕሎማቱን ሐዲስ ዓለማየሁን እንዲወልዱ ብቻ ነበር። እንኳንም ወለዱት!

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 1951 ተመስርቶ፣ ከዚያም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 1955 ዓ.ም እንዲመጣ ብዙ ውለታ ውለዋል። ዛሬ ሐዲስን የጠቀስነው ከዚሁ አምድ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ብቻ ነው። ለምሳሌ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ታህሳስ 20 ቀን 1951 ዓ.ም የተመሰረተ እለት ጉባኤውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት ክቡር አቶ አበበ ረታ ናቸው። በኋላ ደርግ የረሸናቸው ሰው ናቸው። ስለ እርሳቸውም ምንም አልተባለም። ሌሎችም ነበሩ። እነ ከተማ ይፍሩ፣ እነ ክፍሌ ወዳጆ እና ሌሎችም።

ደራሲ ሐዲስ አለማየሁ ኢትዮጵያ ምርጥ ደራሲዎችሽን ጥሪ ስትባል ከፊት የሚሰለፉ፣ ኢትዮጵያ ምርጥ ዲፕሎማቶችሽን ጥሪ ብትባል ከፊት የሚመጡ፣ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችሽን ጥሪ ብትባል ከነግርማ ሞገሳቸው ብቅ የሚሉ የታላላቅ ሰብዕናዎች ባለቤት ነበሩ፡፡ ግን ጭንቅ የሚለኝ አንድ ነገር አለ፡፡ እንደነ ሐዲስ አለማየሁ አይነት ሰዎችን እያፈራን ነው ወይ? ኢትዮጵያ ሆይ እንደነ ሐዲስ አለማየሁ አይነት ሰዎችን ውለጂ፣ ማህፀንሽም የተባረከ ይሁን፡፡

Filed in: Amharic