>
4:39 pm - Tuesday September 28, 2021

እኔና እናንተ - የጋንግስተሮቹ የመንፈስ ልጆች (ወንድማገኝ ለማ)

አብሮ አደጌ ሳይሆን አብሮ አበዴ ነው። ሚዩዚክ ሜይደይ ቲያትር ስጀምር አብሮኝ በጥበብ አብዷል። የጥበብ መጀመሪያ ስካርፕ ማድረግ ፣ ሲጋራ ማጨስ ፣ በግድ የቡና ሱሰኛ መሆን ፣ ፀጉር ማንጨባረር (አሁን አሁን ተሻሻለ እንጂ የአማተር አርቲስት/በተለይ ፀሀፊ ዋንኛ መለያው  የቅጫሞቹ ብዛት ነበር/ ፣ ጫት መቃም ፣ አረቄ መጠጣት (ጅን) ፣ ፈጣሪ የለም ማለት ፤ ቢነበብም ባይነበብም አሮጌ መፅሐፍ መያዝ፣ አርቲስቶችን ማማት…… በሆነባት ሀገር ላይ ተወልደን አንድ ሰሞን ሁሉንም ሞካክረናል። ፊልም እናሰራችሁ ብለን እንዳቅሚቲ ቺኮችን ጎትተናል። ተንቀን ተሰድበናል ፣ ተሳክቶልንም ከክተናል…….ብቻ ለሰው የማይወራም ቢፅፉት የማያምር ዕንጢቅ(የልጅነታችን ቋንቋ ናት) ነገር አድርገናል። ሁሉን ቢፅፉት ፖስቱ ይረዝማል ድድ አስጪን ያሰለቻል ብለን ወደነገርየው ገብተናል።

.
ዛሬ ግን በኔና በሱ መሀከል ያለው ሰፊ ልዩነት በእምዬ ሚኒሊክና በሀይለማርያም ደሳለኝ መካከል እንዳለው አይነት ነው! እኔ አንገት ማስገቢያ 2 ጃንቦ ስጠጣ ዋሌቴ የሚሳሳባኝ እሱ ብላክና ብሉ ሌብል ቦትል አስወርዶ ሲጠጣ የሚያድር ፣ እኔ እንደጉንዳን ብርድና ፀሐይ ሳይበግረኝ ረዥም ሰንሰለታማ ሰልፍ ተሰልፌ ሰማያዊና ነጯን የከተማ አህያ ስጠብቅ የምውል ፣ እሱ ነፃነት ወርቅነህ ሲያስተዋውቅ የምሰማውን መኪና ያለሀሳብ የሚነዳ መንግስቴ ከፈጠራቸው ወጣት ሀብታሞች መካከል ውስጥ አንዱ ነው። ብቻ የሆነ ጊዜ ላይ ተለያየን። እኔ የሙሉ ጊዜ ፀሀፊ ነኝ እያልኩ የፒያሳ ካፌዎች ላይ አፌን ከፍቼ ስውል እሱ ሜቴክ ውስጥ ገብቶ የሙሉ ጊዜ ካድሬ ሆኖ ባጭር ጊዜ ውስጥ ብፈልገው የማላገኘው ዲቪ ሆነብኝ። ሀብታም ስትፈልገው ሳይሆን ሲፈልግህ ነው የሚያገኝህ እንዲሉ……. እንደ ድንገት ትናንት በቅርቡ የገዛው ባልደራስ ኮንዶሚኒየም (የሰፈሬ ልጆች ይሄንን ቦታ አዲሲቷ መኧለ ይሉታል) ( ሁሌም ኮንዶሚኒየም በገባሁ ቁጥር ባላንጣዬ #ፍቃዱ_ጫኔ የሚለኝ ነገር ትዝ ትለኛለች
“አንተ ጎዶሎ…..ቢገባህ ኮ ለእኛ ሸገር ልጆች በጣም በጣም ትንሹ መብታችን ኮንዶሚኒየም ሳንሰቃይ ማግኘት ነበር”) (በፊት በፊት ኮንዶሚኒየምን ደሃ ይደርሰዋል ሀብታም ይከራየዋል ይባል ነበር ዛሬ ዛሬ ግን ገ/መድን ይደርሰዋል ገ/ፃዲቅ ይከራየዋል በሚለው ተቀይሯል)
ላይ የሚገኝ ባለ ሁለት መኝታ ቤቱ ውስጥ ጋብዞኝ ሄድኩኝ። ከሱ ጋ ያለንን ሰፊ የኑሮ ልዩነት ሳስብ የእርጅና ዘመኔን አስቤ መፍራት ጀመርኩ። የኔ የምለው ቤት መቼ ይኖረኛል? በፉጨት ከመልከፍ ተላቅቄ በክላክስ ቺኮችን የማበስለው መቼ ይሆን? እስከመቼ ሳይደላኝ በድራፍት ቦርጭ የደላው መስዬ እታያለሁ? ልጆች ብወልድ ምንድነው የሚውጠኝ? በእርጅና ዘመኔ ከጎረምሳጋእየተጋፋሁ 33 ቁጥር ባስ ላይ እንዳልሳፈር ካሁኑ ምን ባደርግ ይሻለኛል?
.
ከላይ ያነሳኋቸው ጥያቄዎች የኔ ብቻ አይመስሉኝም። የትውልዴ ጥያቄ ይመስለኛል። ሁላችንም በዚህ ዕድሜያችን አሁን ያለንበትን ኑሮ መኖር እንደሌለብን እያሰብን ስንተክዝ እንውላለን። ከፊታችን ያሉን አማራጮች ግን 2 ብቻ ይመስሉኛል። በዚህም በዛም ብለን ከዚች ሀገር መሰደድ (ለሱም ቢሆን እኔ ነኝ ያለ ጨላ ያስፈልጋል) ወይ ደግሞ የጋንግስተሮቹ የመንፈስ ልጆች በመሆናችን የነሱን አርአያ መከተል………
.
የኔና የትውልዴ መገለጫ ከሆኑት ግብብድያ ነገሮች ውስጥ ግንባር ቀደም የሚሆነው የጋንግስተሮቹ የመንፈስ ልጆች መሆናችን ነው።
“የታደለች ቅማል ተጉዛ ተጉዛ
ቤተ መንግስት ገባች ኢህአዴግን ይዛ!”
ተብሎ ተተርቶባቸው ዛሬ ጆሮአቸውን ቢቆርጧቸው የማይሰሙት የሀገራችን ቢሊየነሮች የሆኑት የህውሓት ሰዎች ውዱን ኢትዮጰያዊነት ስሜት መሸርሸራቸው ሳያንስ ከወላጆቻችን የወረስነውን ሞራልና ግብረገብነት እንድንተው ተደርገናል። አገዛዙን በሙስና የምንከስ ሰዎች አብዛኞቻችን ማለት ይቻላል እድሉን ብናገኝ ከመዘርፈ ወደኋላ የማንል ነን። በርግጥ ድሮም ቢሆን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚል ተረትን እየሰማን ያደግን ነንና ስልጣን ላይ ተሁኖ የሚደረግ ዝርፊያን እንደ ሀጢያት አንቆጥርም። ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመን ጋንግስተሮቹ መዝረፋቸው ሳያንስ እኛ ላይ ጥቁር አሻራቸውን እያሳረፉብን ነው። በአዲስ መስመር ሀሳቤን ላብራራውማ…….
.
አንድ ሁለት ትውልድ ወደኋላ ብንሄድ ማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ክብር ይሰጣቸው የነበሩት ከመንግስት ሹማምንቶቹ ውጪ…… ውጪ ሀገር ተምረው የመጡ ፣ የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ አገባች አስተማሪ ተብሎ የተዘፈነላቸው ከወላጆቻችን ቀጥለው ያሳደጉን መምህራኖች ፣ ታላላቅ ደራሲዎች ፣ ጀግና አርበኞችና ወዘተ ናቸው። በአሁን ዘመን ግን ክብር የሚሰጠው አንድና አንድ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው እሱም “ገንዘብ ያለው” እደግመዋለሁ “ጨላ ያለው!” ሞራል ፣ ግብረገብነት ፣ እውቀት ገደል ገብተዋል። መሬት ላይ ያለውን እውነታ ስንመለከት ደግሞ ከታላቁ ኤፈርት ጀምሮ ባሉካ የሆኑት የኔና የትውልዴ አርአያዎች የህውሓት ሰዎች ናቸው። ዘመኑ ለአስተዋዮች የተመቸ አይደለም ፣ ዘመኑ ሀገሬ ሀገሬ ለሚሉ ሰዎች ቦታን የሚሰጥ አይደለም ፣ ዘመኑ ለፈጣን በዮች የሚሆን ነው። ዘንድሮ የሚያዋጣው ሀገሪቷን በደቦ መጋጥ ነው። የደሃውን ገንዘብ ያለህፍረትና እፍረት ማግበስበስ ነው። አገዛዙም ለዚህ የተመቸ ነው። የኔ ናቸው ብሎ የሚተማመንባቸውን ካድሬዎቹንበገፍ እንዲቀጠሩ የሚያደርገው ለዝርፊያ የሚመቹ መስሪያ ቤቶች ላይ ነው። ለዚህም ትልቁ ማሳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ ጉምሩክና መንገዶች ባለስልጣን የተሰገሰጉትን ሰራተኞች መመልከት ብቻ በቂ ማሳያ ነው። በግሉ መስሪያ ቤትም ቢሆን አብዛኛው ሰው የሚቀናበት የስራ መደብ የንብረት ግዢ ክፍል ነው። ም/ም ለዝርፊያ የተመቸን ነዋ!
.
“እነሱ ላም ሲያርዱ እኛም ጥጃ እንረድ
ቢሆንም ባይሆንም እጃችን ደም ይልመድ!” እያልን እኔና ትውልዴም በገኘናት ቀዳዳ ሁሉ የበይ ተመልካች ከመሆን አልፈን በተሰማራንበት ሙያ ሁሉ ቀንደኛ ዘራፊዎች ሆነናል።  በፊት በፊት የማይወደደው የስራ ባልደረባ ለአለቃ የሚያቃጥር ዕንባ ነበር ፤ ዛሬ ደግሞ በሰራተኞች ዘንድ የሚገፋው ሰራተኛ የወገኑን ሀብት አላስበላ የሚል ለዝርፊያ የማይመች ለሆዱ ሳይሆን ለህሊናው ያደረ ሰራተኛ ነው። ይህ ሁላችንም የተተበተብንበት የሌብነት ችግር ቆም ብሎ የሚያስተውል ካለ እንደ ሀገር እንድንራመድ ከተፈለገ ከፊታችን የገጠመን ሊቀረፍ የማይችል ጋሬጣ ነው። ማንም እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ የሚል የለም! ዛሬ በዕንቁላሉ የጀመርናት ስርቆት ነገ ደሃ ወገናችን ደም ዕንባ ቢያነባ የማይሰማን ልበ ደንዳንዶች ያደርገናል።
.
ዛሬ ያገኘሁት ካድሬው ወዳጄ አንድ ሁለት ስንወጋ መውጣት የማይችልበት የሙስና ሰንሰለት ውስጥ እንደተዘፈቀ ከነገረኝ ገጠመኞች ውስጥ አንዱን እንደመሰናበቻ ልጥቀስላችሁ….
ሜቴክ አንድ ፕሮጀክት ይሰጠዋል። ፕሮጀክቱ በአንዲት የገጠር ቀበሌ ውስጥ ንፁህ ውሃ የማውጣት ፕሮጀክት ነው። ይሄ ጓደኛዬና ሌሎች ሶስት ለስርዓቱ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ስራው ይጀመራል። የምንጭ ውሃ ሲጠጣ የኖረው ባላገርም ደስታውን ለአምላኩና ለልማታዊ መንግስቱ ያሰማል። የሆነ ቀን አራቱ ሰዎች በርጫ ላይ ተሰይመው ለፕሮጀክቱ የመጣውን  ለጊዜው አሁን ስሙን የረሳሁትን ውድ ማሽን ለምን አንሸጠውም የሚል ሀሳብ ያነሳሉ? ሁሉም ይስማማሉ። ግምገማ ላይ የሚያቀርቡትን ሪፖርት ያፀድቃሉ። አንድ ቻይና ደላላ ይፈለጋል። ዕቃው ይፖሻል። ከሆነ ወር በኋላ እንደገና ገንዘብ ተመድቦ ጓደኛዬ ወደስፍራው ያመራል። ባለ-ሀገሩ አሁንም የምንጭ ውሃ ቀድቶ ይጠጣል። የዛሬው ግን ይለያል። የውሃው ጉድጓድ ውስጥ የሞተ ውሻ ገብቷል።  ውሻውን ደግሞ ማውጣት አልተቻለም። የውሻው ሬሳ ደግሞ ፈንድቶ ተልቷል። ገጠሬዎቹም ውሃውን በገመድ ስበው ያወጡና ወደጀሪካናቸው ሲገለብጡ ትሉን በነጠላቸው እያጠለሉ ነበር። ይሄንን ያየው ጓደኛዬ አዘንኩ አለኝ።
“ለሌሎቹ ስነግራቸው ግን ገና ጀማሪ ስለሆንክ ነው ስትለምደው ይለቅሃል አሉኝ እውነትም ዛሬ አይሰማኝም ፣ ደሃን እየዘረፍኩ እንደምኖር ሳውቅ ማዘን ብፈልግም ግን  ልቤ ሊያዝን አይችልም። የደሃን ዋይታና ለቅሶ ተለማምጄዋለሁ። የህሊናዬን ጩኸት መቀነስ ተለማምጄያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ባጭሩ ለመክበር ያለህ ብቸኛ አማራጭ ዝርፊያና ዝርፊያ ብቻ ነው” አለኝ
.
እሱ ስለ ዝርፊያው ዓይነትና ብዛት ሲነግረኝ እኔ ብሆንስ አደርገዋለሁ ወይ? ብዬ ራሴን ስጠይቅ ውስጤ የምጠብቀውን መልስ መለሰልኝ “ድብን አድርጌ!”
ዛሬስ እሺ ነገስ? ኢህአዴግ ቢወድቅም የማንወጣው የትውልዴ ፈተና ዝርፊያን ነው። ተቃዋሚ ተብዬዎች ግን የኔና የትውልዴን ጭንቅላት ከማንቃት ይልቅ ጠማማ የታሪክ ሰበዞችን እየመዘዙ “እገሌ ብሔር በድሎሃል ይቅርታ ያስፈልግሃል” እያሉ ጦር ያማዝዙናል። ምድረ ከንቱ ሁላ!
ታላቁ መራራ ጉዲና “የተራበ ህዝብ መሪውን ይበላል” የሚሉትን አባባል እኔ አልቀበልም እኔ እየታየኝ ያለው “የተራበ ህዝብ እርስበርሱ ሲበላላ ነውና!”

Filed in: Amharic