>
7:25 pm - Thursday September 16, 2021

የእያንዳንዳችን እጅ ለጋዜጠኛ ግርማየነህ ማሞ መዘርጋት አለበት

[በወንድወሰን ተክሉ]

FB_IMG_1502696254395የጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን አገላለጽ የባልደረባችንን ያለበትን ጽልመታዊ ህይወትና የከበበውንም የጽልመት ደመና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ አይደለም በአካል ለሚያውቁት የስራ ባልደረባ ይቅርና እስከነመፈጠሩንም ለማያውቁት አንባቢዎችም የሚፈጥረው የስቃይ እና የቁጭት ስሜት ቀላል አይደለም።

ግርማየነህን ለማየት ወደ መኖሪያ ቤቱ ያቀናው ወሰንሰገድ ብቻውን ሳይሆን ሳይሆን ከሌላ ብእረኛው አናኒያ ሶሪ ጋር ቢሆንም ሁሉቱም ጋዜጠኞች ባልደረባቸውን አይተው ለእኛ እናየው ዘንድ ያሰፈረልን ቃላቶች እያንዳንዳቸው እንደ ወስፌ የሚዋጉ ናቸው..”ጭልምልም ባለች ክፍል ውስጥ ግርማየነህ ማሞ እጅግ ጠቃቁሮ፣ከሰውነት ተራ ወጥቶ ተኝቶ አገኘነው..”የሚለን ወሰንሰገድ ለምን እና እንዴትስ ሆኖ ለዚያ ደረጃ እንደበቃ ከግርማየነህ የደበቀውን እንባውን ለእኛ ሳይደብቅ እያነባ ነበር የጻፈው።

ጋዜጠኛ ግርማየነህ ማሞ ባደረበት ህመም አንደኛ እግሩን በመቆረጡ እቤት በጉስቁልና የቀረ ሰው ሆናል።እንግዲህ ሁላችንም በምናውቃት ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመነ ህወሃት የስርዓቱ ተፈቃሪ ሳትሆን ባለህበት ሁኔታ አይደለም እግር ተቆርጦ ከእነ እግርና እግርም ተቀጥሎ ለመኖር አዳጋችነቱ የታወቀ ነው።

“ድሮም አልነበረንም አሁን ደግሞ ያንኑ አጣንና ባዶ ወና ሆነን ቀረን” ሲል ግርማየነህ ለጎብኚዎቹ ወሰንሰገድና አናኒያ ተናግራል።

ሀገራችን አይደለም የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኛ ሀብትና ደሞዙ እስር፣እንግልት እና መጨረሻም ስደት የሆነለት ባለሙያ ቀርቶ በሁሉም ዘንድ ተወዳጅነት እንዳላቸው እና ስራዎቻቸውንም በእያንዳንዳችን ቤት የምንኮመኩምላቸው አርቲስቶቻችን እንካን እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ሲታመሙ እየተለመነ እና እየተዋጣላቸው የሚታከሙበት ሀገር አይደለችምን?
ባልደረባችን ግርማየነህ ደግሞ ከእነዚህ እጅግ በባሰ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ሆኖ እናየለን።

በመጀመሪያ ደረጃ ዛሬ ጋዜጠኛ ግርማየነህ ማሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቀሩት እጅግ በጣት የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ አባላት ውስጥ አንዱ ሲሆን ከ200በላይ ከተሰደዱት ውስጥ ሊካተት ያልቻለበት ዋና ምክንያት በሀገሩ በነጻነት የመስራት መብቱ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ተከብሮለትና ተጠብቆለት ሳይሆን የደረሰበትን ዘረፍ ብዙ ችግሮች፣ተጽእኖዎችና መንገላታቶችን ችሎ የተቀመጠ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል።

ከተሰደድነው የበለጠ እስር፣እንግልት፣ክትትል እና ጭቆና እየተፈጸመበት ግን በቃ የመጣውን ተቀብሎ በዚያች በሚያፈቅራት ሀገሩ የቻለውን ለማድረግ ከእነ እስክንድር፣ወሰንሰገድ፣ እና ሌሎችም ጋዜጠኞች ጋር በሀገሩ የቀረ ባለሙያ ነው።

በ1987/8 ዓ.ም በከርቸሌ ፍርድ ክልል ታስሮ በነበረበት ወቅት ህወሃቶች በእስር ቤቱ ውስጥም ሲያደርጉት የነበረውን በደል እና እሱም ሲያሳይ የነበረውን ያለመበገር ጽናትና ጥንካሬ ግርማይነህ ባያስታውሰውም እኔ ግን ፈጽሞ የምረሳለት አይደለም።

ያለውን የተባ ብእራዊ ሙያውን ለሀገራዊ ጥቅም፣ለእውነት፣ለፍትህ፣ለእኩልነትና ለጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ስር አስገዝቶ እራሱን በነጻ ፕሬስ መንደር ከሚያሰማራ ለህሊና ቢሶቹና ለግለ ጥቅም ተማጋች “ባለሙያዎች” መነሃሪያ ወደ ሆነው መንግስታዊውና የድርጅታዊዎቹ የመግናኛ ተቃማት ላይ ቢጠቀምበት ኖሮ ዛሬ ግርማየነህ ባጋጠመው የጤና ጉድለት እግሩን አጥቶ በባዶ ቤት ለጽልመት ባልበቃ ብዪ እገምታለሁ።

እየከፈለ ያለውን ዘርፈብዙ [እሱና እሱን መሰል ባልደረቦቼና ባለሙያዎች አጠቃላይ]ዋጋ ብዙዎቻችን ልብ ላንል እንችላለን እንጂ እጅግ ከፍተኛ ነው።

ስርዓቱ ከ1997 ማግስት ጀምሮ በአጠቃላይ የነጻ ፕሬስ ተቃምና በማህበሩም የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበርን [ኢነጋማ]ለማጥፋት በከፈተው ጥቃት ከሞላ ጎደል ሁሉንም አዘግቶ ማህበሩንም አፍርሶ ብዞዎችን ለስደት መዳረጉ ይታወቃል።
ከ200በላይ ጋዜጠኞችም በዘመነ ህወሃት ሀገር ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን እጅግ ጥቂት የሚባሉት ግን ዛሬም ጭምር የጥቃቱን በትርና ዱላ እየተቀበሉ ሳይኖሩ ግን የሚኖሩ ሆነው ይገኛሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት እንካን በአንድ ግዜ 14ጋዜጠኞች ወደ ኬኒያ በስደት የመጡበትን ክስተት እንካን ብናይ ግርማየነህ ባልደረቦቹ እነ ዘገየ አየለ፣ዳንኤል ድርሻ፣ቶማስ አያሌው…ወዘተ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሰደዱ ግርማየነህ በባልደረቦቼ ላይ የደረሰው በደል እና ስቃይ ስላልደረሰበት ሳይሆን አሁንም ከሀገር በመውጣት መፍትሄ አይገኝም በሚለው አቃሙ የሆነውን እየሆነ የቀረ ጋዜጠኛ ነው።

ይህም ትልቅ ዋጋ ነው-ማንኛችንም የማናስተውለው ትልቅ ዋጋ ነው። ሆኖም ዛሬ የህወሃትን በትር፣ጭቆና ግፍና ማንገላታትን ተቀብሎና ችሎ ድምጹን አጥፍቶ ሲኖር የነበረው ባልደረባችን ተጨማሪ እግሩን ነጣቂ ህመምና መጣና እግሩን ነጥቆ ለጨለመው ቤት ዳረገው።
በመጀመሪያ በሙያው እንዳይሰራ በጨቃኙ ህወሃት አፋኝ ህግ ተሽመድምዶ ያለን ሰው በተጨማሪ ወዲያ ወዲህ ተንከላውሶ የሚኖርበትን እግሩን የሚነጥቅ ክስተት ስትጨምርበት እንዴት አድርጎ ህልውናዊ እስትንፋሱን ማቆየት እንደሚችል ማሰቡ እራሱ ይዘገንናል።ሆኖም የሆነው ይህ ነው።

በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ተክብሮ የፕሬስ ስራዎች አብበው ይታዩ ዘንድ የሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር የትየለሌ ነው።ከኢትዮጵያዊያኑም ሌላ በሰው ልጅ የመናገር ነጻነት የሚያምኑት ሁሉ ከዚህ ትግል ጋር እራሳቸውን በማዛመድ የተለያየ አስተዋጽኦ የሚያደርጉም አሉ።

የነጻ ፕሬስ ህልውና ካለ ጋዜጠኛው ህልውና የሚታሰብ አይደለም። ግርማየነህ የስርዓቱ አድናቂ፣አማቂና ህሊናውን ሸጦ አጨብጫቢ ቢሆን እነ ሼህ አላሙዲን የሚቀድማቸው የለም -ለማሳከምና ለመርዳት። ገንዘብ የማሰባሰቡም ተግባር እዚያው በዚያው ይፈጥን ነበር።
ምነው ለመብት፣ለነጻነት፣ለእኩልነት እና አጠቃላይ ለተሻለ ስርዓት መፈጠር የሚያምነው የህብረተሰብ ክፍልና ብሎም ታጋይና አታጋዩ ክፍል የራሱን ታጋዩች መታዳግ ያቅተዋልን?

በኢትዮጵያ ውስጥ ለተሻለ ስርዓት ፣ለፕሬስ ነጻነት መፈጠርና እውን መሆን የሚያምን ሁሉ በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው በተለያየ ችግር፣ህመምና አደጋ ላይ ያሉትን ባለሙያዎች ህልውና የመጠበቅ ሞራላዊ ግዴታ አለበት የሚል እምነት አለኝ።

ግርማየነህ እግሩን ከማጣቱ በፊት ማንም ያወቀለት አልነበረም። እናም ህልውናውን የሚያቆይለትን እግሩን አጣ። ዛሬ ከሁላችንም የሚፈልገው ለወሰንሰገድ እንደነገረው “ያጣውን እግሩን መልሶ ማግኘት ይፈልጋል” ማለትም በህክምና የአርቲፊሻል እግር ያስፈልገዋል ማለት ነው።

ለዚህ ደግሞ የስራ ባልደረቦቹ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብዪ እንደገለጽኩት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለመብት፣ለእኩልነት፣ለፕሬስ ነጻነት ማበብ አምኖ እየተንቀሳቀሰ ላለ ሁሉ የሞራል ግዴታ ሆኖ ይሰማኛል። እነሱ [ግርማየነህ..እስክንድር…ተመስገን..ማለቴ ነው] ስለ ሁላችን ከቃተቱ -በድካማቸውና በጉዳታቸው ግዜስ እኛም ለእነሱ መቃተት አይገባንም?
የህሊና ጥያቄ የህሊና መልስ ያሸዋል።
ባለኝ መረጃ መሰረት ግርማየነህን ለመርዳት የምትፈልጉ በሁለት መንገድ መርዳት የምትችሉ ሲሆን አንደኛው በቀጥታ ለራሱ በጋዜጠኛ ግርማየነህ ማሞ በተከፈተ የባንክ አካውንት እና ስልክ ቁጥሩ ደውላችሁ በማረጋገጥ መርዳት የምትችሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በስራ ባልደረቦቹ በ ዘ-ሐበሻ-ከፋችነት በግርማየነህ ስም በተከፈተ ጎ-ፈንድ ሚ ድረ-ገጽ በመጠቀም መርዳት እንደምትችሉ ልገልጽላችሁ እውዳለሁ።

ወገን ለወገን ካልደረሰ ማን ሊደርስ ነው።

አድራሻዎቹ የሚከተሉት ናቸው

የጋዜጠኛ ግርማየነህ ስልክ-254 911122529
የባለቤቱ ወ/ሮ ሽብሬ ጥሩነህ-254 920 007416
የባንክ አካውንት -ወ/ሮ ሽብሬ ጥሩነህ ቡና ባንክ አዲሱ ገበያ ቅርንጫፍ አካውንት ቁጥር 174950100115
በጎ ፈንድ ሚ በኩል በሄኖክ ደገፉ የተከፈተ አካውንት በጎፈንድ ሚ ድረ ገጽ ላይ ታገኛላችሁ።

Filed in: Amharic