>
12:40 pm - Monday November 29, 2021

አዲስ አበባ እንደገና (ጌታቸው ሃይሌ)

addis-abeba-2የዋና ከተማችን ስም የተነሣበት ውዝግ ለጊዜው ገብ ቢልም ወያኔዎች በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ሊያገረሽበት ይችላል እንዳልኩት፥ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሦስት ሰዎች አቶ ካሣሁን ነገዎ ከአውስትራልያ በሚያስተላልፈው ራዲዮ አማካይነት ሲተቹት ሰማሁ። በዚያው አያይዘው፥ በቅድስት ኢትዮጵያ ላይ ስለነገሠው ዘረኝነት ከሦስቱ ተቺዎች አንዱ ደጋፊ፥ ሁለቱ ተቃዋሚዎች ሆነው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አስተያየቴን አክልበታለሁ።

መጀመሪያ በራሴ ትችት ላይ ስለተነሡት ቅሬታዎች ላውጋችሁ።

፩. ሽማግሌው አበጣብጦን ሊሄድ ነው።

በዚህ ቅሬታ ላይ ሁለት ስሕተቶች ይታያሉ። አንደኛ፥ የምጽፈው ሁሉ የታሪክ ማስረጃ ይዤ ስለሆነ ከአንባቢዎቹ ዘጠና በመቶ (ምናልባትም ከዚያ በላይ) የሚሆኑት ይደግፉታል። ያን ያህል ሰው ከደገፈው በጽሑፌ ምክንያት ተበጣባጭ የለም ማለት ነው። ጽሑፌን ለሌሎች የሚያጋሩትን (share የሚያደርጉትን} ብዛት ሁሉም ይየው አይየው አላውቅም፤ ብዙ ነው።
ሁለተኛው ስሕተት እኛን ሂያጆችና ቀሪዎች አድርጎ መክፈል ነው። በአምላክ የግል መብት መግባት ነው። ሁላችንም ጥቂት ጊዜ ኖረን ሂያጆች ነን። ሽምግልና የአምላክ በረከት እንጂ፥ ብቻውን የቀድሞ መሄድ ምልክት አይደለም። ብዙዎች ታናናሾቼ ቀድመውኛል፤ ሐኪሞቼን ካመንኳቸው ገና ብዙ ዓመታት እቆያለሁ። ደካማ አካል የለብኝም። የሚጸልዩልኝም ብዙዎች ስለሆኑ የአምላኬና የሐኪሞቼ ቃል አንድ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። “ጆሮን የፈጠረ አይሰማምን?” ብሏል ቅዱስ ዳዊት። በኔ ቀድሞ መሄድ ተስፋ የሚጥል ካለ፥ እንዳይሳቀቅ እሠጋለታለሁ።

፪. ፍንፊኔ አማርኛ ከሆነ ምን አስፈራችሁ?

ዋና ከተማችን “ፍንፍኔ” ብትባል ያልተቀበልነው ለሐሳቡ በቂ ምክንያት ስላላየንበት ነው እንጂ አማርኛ አይደለም ብለን አይደለም። በአማርኛ “አዲስ ዓለም” ወይም “ሀገረ ሰላም” ትባል የሚል ሐሳብ ቢመጣ እንቀበል ነበር ማለት ነው? ያለ ምክንያት አንቀበልም። የሀገር ስም በቋንቋችን ይሁን የሚሉ የኦሮሞ ፖሊቲከኞች እንጂ አማሮች አይደሉም። አማሮች ለቦታ ስም ሲሰጡ ከታሪክና ከቅዱሳት ቦታዎች ጋር በማያያዝ (ደብረ ሲና፥ ደብረ ታቦር፥ ገሊላ፥ ወዘተ) እንጂ በቋንቋችን ካልሆነ ብለው አይደለም። እንዲያ ቢሆንማ፥ ቡታ ጅራ፥ ቱሉ ዲምቱ፥ ቱሉ ርኤ፥ ወሎ፥ ሞጆ፥ ሜጫ፥ ጉድሩ፥ ወዘተ የቱለማና የበረይቱማ ጎሳዎች አገሩን ከመውረራቸው በፊት ያልነበሩ ታሪክ ያመጣጠው አዳዲስ ስሞች ናቸው፤ ማን ነካቸው? የዋና ከተማችን ስም ይለወጥ ከተባለ፥ ሌሎቹ ስሞች ሁሉ፥ እነ አቧሬ፥ እነ ጉለሌ፥ እነ አራዳ ሁሉ ጠበቃ ገዝተው ከውድድሩ እንግባ ይላሉ። ሁሉም አንደ ፍንፍኔ የከተማዋ ክፍለ ሀገራት ስሞች ናቸው።

፫. መርካቶ፥ ፒያሳ፥ . . . የጣልያን ስሞች ናቸው።

እናስ? እነዚህን ስሞች ለምሳሌ አነሣኋቸው እንጂ ውይይታችን እነሱ ከየት እንደመጡ አይደለም። በውይይት ጊዜ ትዝ ያለ ነገር ሁሉ የውይይት ማእከል አይሰጠውም። እንዲያውም ሕዝብ የተቀበለውን ስም ስንቀበል “የምን ቋንቋ ቃል ነው?” ሳንል ለመሆኑ ጥሩ ማስረጃ ናቸው። የጠላት ቃላት ሆነው ሳለ ያላንዳች ቅሬታ እንጠቀምባቸዋለን።

ዘረኝነት በይፋ የነገሠባት አገር

የጎሳ ፌዴሬሽን መቶ በመቶ ዘረኝነት ነው። የጎሳ ፌዴሬሽን መመሥረት ዘረኝነትን በይፋ ማንገሥ ነው። አንዳችን ከሌላችን የተለየን መሆናችንን በሐሰት መመስከራችን ነው። መጀመሪያውኑ የተዘረጋው ፌዴራሊዝም የጎሳ ፌዴራሊዝም ሳይሆን የወያኔዎችንና የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ፍላጎት ማርኪያ ነው።  ሰማንያ ጎሳ ባለባት አገር ላይ ፍጹም የጎሳ ፌዴራሊዝም ሊፈጠር አይቻልም። ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ሕጸጹን እንደጻፍኩ ነው። አከላለሁ ፍጹም ቢሆንም ባይሆንም፥ ጎሰኝነት ዘረኝነት መሆኑ ግልጽ ነው። አንዱን ኢትዮጵያዊ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ፍጡር ያደርገዋል።

በየክልሉ ውስጥ ብዙ ጎሳዎች አሉ። ግን ክልሉ የነሱ አገር አይደለም፤ አገር የላቸውም፥ የኦሮሞዎች፥ የአማሮች፥ የትግሬዎች ጥገኞች ናቸው። በክልሉ ላይ መንግሥት ከተቋቋመ መንግሥቱ የኢትዮጵያውያን ሁሉ መሆኑ ቀርቶ የኦሮሞች፥ የአማሮች፥ የትግሬዎች መንግሥት ነው የሚሆነው። የኦሮሞ፥ የአማራ፥ የትግራይ መንግሥት አቋቁሞ የሌሎቹን መብት መጠበቅ አይቻልም። የሌሎቹ መብት የሚጣሰው ገና የጋራ የነዋሪዎቹ ሁሉ የጋራ መንግሥት ሲቋቋም ነው።

አንድ አካባቢ የኦሮሞ፥ የትግራይ፥ የአማራ አገር ነው ሲባል፥ በብዛት የሰፈሩበትን ሰዎች ለማመልከት ነው እንጂ፥ የሰፈሩበት መሬት የነሱ ነው ማለት አይደለም። መሬቱ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊኖርበት መብት ያለው የኢትዮጵያ መሬት ነው። በስማቸው የተጠራውን መሬት “የኛ መሬት ነው” ብለው ሌላውን ከዚያ ሊያስወጡት፥ የእኩልነት መብቱን ሊነፍጉት፥ ወይም ከመሬቱ ቈርጠው ለሌላ አገር ሊሸጡለት፥ ወይም ይዘውት ሊሄዱ አይችሉም። መሬቱን የያዙት ከሌሎች ጋር እኩል እንዲጠቀሙበት ነው።

Filed in: Amharic