>
5:18 pm - Wednesday June 15, 2327

በኦሮምያ የተጠራው የ5 ቀናት የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ተጀመረ (ኢሳት)

(ኢሳት ዜና ነሃሴ 17 ቀን 2009 ዓም) በኦሮምያ የተጠራው የ5 ቀናት የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ተጀመረ
protest-ethiopia-in-oromiaከተለያዩ አካባቢዎች የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኦሮምያ ወጣቶች የተጠራው የስራ ማቆም አድማ በአብዛኛው የኦሮምያ ከተሞች ተግባራዊ ሆኖ ውሎአል። የንግድ መደብሮች ተዘግተዋል። የትራስፖርት አገልግሎትም ተቋርጣል። በአወዳይ እና በአንዳንድ የምስራቅ ሃረርጌ ከተሞች አድማውን ተከትሎ በህዝቡና በመከላከያ መካከል መጠነኛ ግጭት ተከስቷል። የአድማውን ጥሪ በመጣስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መኪኖች ተቃጥለዋል፤ ተሰባብረዋል።
በጅማ ዞን ሊሙ ሆሳ ወረዳ ደግሞ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ንብረት የሆነ 200 ሄክታር መሬት ላይ የተለቀመ ቡና የአካባቢው ነዋሪዎች ተከፋፍለውታል። ነዋሪዎቹ በዙሪያው ለጥበቃ የተሰማሩትን ወታደሮች ከምንም ባለመቁጠር ወደ ግቢ በመግባት ቡናውን እየተከፋፈሉ መውሰዳቸውንና ገዢው ፓርቲ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ አካባቢው መላኩን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በኦሮምያ በብዛት የተሰማራው መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስና ልዩ ሃይል አድማውን ለማስቆም ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
እስካሁን ባለው መረጃ አድማው በ ወለጋ፣ ጊምቢ፣ ሆለታ፣ ሃሮማያ፣ አወዳይ፣ ደምቢ ዶሎ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ሻሸመኔ፣ ደምቢደሎሎ፣ አምቦ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ፣ ባኮ፣ ግንደበረትና በመሳሰሉት ከተሞች ተጠናክሮ ቀጥሎአል።
ከአዲስ አበባ ተነስተው ጉዞቸውን ወደ ሃረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅጅጋ፣ ሚዛን ተፈሪ ፣ ጋምቤላ እና ኦሮምያ ክልልን አቋርጠው ወደ ተለያዩ ክልሎች የሚሄዱ ሰላም ፣ ጎልደን እና ፋልኮን የሚባሉ አውቶቡሶች ጉዞአቸውን ሰርዘዋል። የተሽከርካሪ ባለቤቶች በመኪኖች ላይ የሚደርስባቸውን ጉዳት መንግስት እንደማይሸፍንላቸውና ሁኔታው ካልተረጋጋ በስተቀር እንደማይጓዙ ለመንገደኞች ገልጸዋል። አንድ አውቶቡስ መስታውቱ ቢሰባበር ለጥገና እስከ 100 ሺ ብር እንደሚከፍሉ የሚገልጹት፣ ባለሃብቶች ከዚህ በፊት በደረሰባቸው ኪሳራ በቂ ትምህርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ጅጅጋ አካባቢ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ባቢሌ አካባቢ ችግር በመኖሩ ሲመለስ፣ ሃረር አራተኛ እየተባለ በሚመጠራው አካባቢ ደግሞ የህወሃት ንብረት የሆነው ሰላም ባስ በድንጋይ ተሰባብሯል።
አወዳይ ላይ ደግሞ ሁለት አይስዙ መኪኖች ተሰብባረዋል። የአንደኛው መኪና ሹፌር ተደብድቦ ሆስፒታል ገብቷል። በአምቦና ነቀምት መስመር ምንም አይነት መኪና ዝር እንደማይል የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎችም ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም።

ከሰአት በሁዋላ ደግሞ ስራ ያቆሙ የመንግስት ሰራተኞች ነገ ስራ የማይጀምሩ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።
አድማውን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ተይዘው መታሰራቸውም ታውቋል።
ከኦሮምያ ወደ ሶማሌ ላንድና ወደ ተለያዩ የሶማሊ ክልል አካባቢዎች የሚሰራጨው ጫት ከትናንት ማክሰኞ ምሽት ጀምሮ መቆሙም ታውቋል።
አድማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞን ህዝብ ስነልቦና ለማሸነፍ የተለያዩ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን እየወሰድኩ ነው ለሚለው ኦህዴድ ትልቅ ሽንፈት ተደርጎ ተቆጥሯል።
ዘጋቢያችን እንደሚለው በምስራቅ ሃረርጌ ለሚታየው የመረረ ተቃውሞ ከግብር ጥያቄ ባሻገር የሶማሊ ክልል ልዩ ሃይል በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚወስደው እርምጃ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል። በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት ቢሰማራም ፣ በመኪኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም እንዳልቻለ ገልጿል።

Filed in: Amharic