>

በወገኔ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም የእልቂት ጥሪ አወግዛለሁ (ጣይቱ ቦጋለ)

ዝም ብለን ነበር
ዝምታ ወርቅ አይደለም
ዝምታ ኪሳራም አለው
Jawar Mohammedጭቆና መድልዎ ሙስና የመልካም አስተዳደር እጦት እና አምባገነንነት እስካለ ድረስ ትግል አይቀሬ ነው። የትግሉ ጡዘት የሚፋፋመው እየደረሰ ካለው በደል አንጻር ነው። ሆኖም በትግል ሂደት ህዝባዊነትና ህዝበኝነት ተለያይተው መቃኘት አለባቸው።
ለማሳያ ያህል፦ 6 ሚሊየን አይሁዶች በናዚ ጀርመኖች ሰለባ የሆኑበት ዋነኛ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ድቀት እና ቀድሞ የተሰበከ የዘረኝነት መርዝ ውጤት ነው። 800ሺህ ቱትሲዎች በ100 ቀናት ብቻ እዚህ ቅርባችን ሩዋንዳ ትላንትና በ1994 የተጨፈጨፉት በተመሳሳይ በዘረኝነት ቅስቀሳና ለቅስቀሳው አመቺ መፈልፈያ በሆነው የኢኮኖሚ ቀውስ እና ማህበራዊ ምስቅልቅል ነው።
ለዴሞክራሲ መቀንጨር ዋነኛ ምክንያቶች የትየለሌ ቢሆኑም የኢኮኖሚ መራቆት Economic Depression (ያው በኛ ሀገር ዘረፋ የኑሯችን አካል ሆኗል)፤ የማህበረሰብ ምንግዴነት (Civic Neglect) ፤ የገነገነ ውጣ ውረድ የሞላበት ቢሮክራሲ (Tight/ Intense) bureaucracy፤ ዘረኝነት አምባገነንነት ጽንፈኝነት ጥላቻና Their versions የመንፈስ ፍሬዎችን መድፈቅ ሲጀምሩና ገንነው ሲታዩ ነው።

የሰሞኑ ዋነኛ  የፖለቲካ ትኩሳት የጃዋር መሀመድ ጉዳይ መሆኑን ለመገንዘብ አውራዎቹ ያሰፈሩትን ስታተስ መስፈር በቂዬ ነበር። እናም አዎ በአትሌቲክስ፥ በኃይሌ ገብረሥላሴ፥ በተገለፁት ሙሰኞችና በአይነኬ ሙሰኞች ዙሪያ ሲሾር የነበረው ፌስቡክ ተረኛውን ጃዋርን በሰሌዳው ላይ ደቅኗል። በበጎም ይሁን በአሉታ ተጽእኖ ፈጣሪውን ጃዋርን።

ጃዋር መሀመድ ከሰሞኑ ያስቀመጠው አንድ መልዕክት “ባለፈው የንግድ ማቆም አድማችን ያልተሳካው በጉራጌ ነጋዴዎች ስለሆነ የመጨረሻውን እርምጃ ውሰዱባቸው” አይነት ግልፅ ያለ ማዘዣ ነበር። ምንም ሳናመቻምች ትእዛዙ በስራ ማቆም አድማው ካልተሳተፉ ጉራጌዎቹን ግደሏቸው የሚል ነው። ለመሆኑ በዴሞክራሲ ሀሁ ወይም አቡጊዳ (አባጫዳ) አድማ ላይ የመሳተፍም ሆነ ያለመሳተፍ ጉዳይ የግለሰብ ነፃ ምርጫ ሆኖ ሳለ፤ የኔን መንገድ ያልተከተሉትን ፍጇቸው (My way or the highway) ነገ ከጃዋር ጋር ምን አይነት እንደሆነ አመላካች ይመስለኛል። የበለጠ አደገኛው ጉዳይ በአድማው ማይሳተፉ አባሉ ቢቀር የኦህዴድ አመራሮች እያሉ  ምዕመናን ጉራጌዎች ላይ ማነጣጠሩ አደጋው የት ድረስ ነው?!

ደግሞስ ይህ ሚኔሶታ አይደለም፤ ከሱፐር ማርኬት በብድር አስቤዛ ተሸምቶ ሳምንት ቁጭ ሚባልበት፤ ከገበያ የወዳደቀ ቧግተው፥ ተሸክመው፣ ጉሊት ቸርችረው የእለት ጉርሳቸውን ብቻ የሚሸፍኑ፣ ሚሊዮኖች እየተራቡ ባሉባት ሀገር ለአንድ ቀን ረሀብ መጨመር መዳረሻው የት ይሆን፥ ፍርዱን ለእናንተ። ኢህአፓ መሳሪያ እስከአፍንጫው ከታጠቀው ደርግ ጋር ባዶ እጃቸውን የተነሱ ወጣቶችን አፋልማ ደርግ በሰላ ፋሱ ከሚሊዮን ያላነሱ ወገኖቻችንን በላቸው። የከተማ ትግሉ የወላዶችን ቅስም ሰብሮ፤ ትንታግ ትውልድ አምክኖ ወኔው የሸና ትውልድ ፈጥሮ እንደነበር ትንሽ ወደ ሁዋላ ሄዶ ማየቱ በቂ ነው። አመጽ አመጾች ግምገማ ህዝባዊ ግምገማ ውግዘት ኮማንድ ፖስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጉልቻ ለውጥ በሪሞት የሚመራ ትግል፤ ቆጣሪ በማጥፋት ወዲያው የሚቀጭጭ ትግል። ጃዋር ያስገኘው ፋይዳ ምንድነው፤ የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት፥ ቁቤን ቀይሮ ወደነበረበት መመለስ፥ ምርጥ ድራማ ፈረንጆቹ status quo የሚሉት አይነት። አይ የፖለቲካ ብስለት?! ….

ባለፈው ኢትዮጵያን ዲጄ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ከምሽቱ 3:00 ሰዓት እስከ 4:00 ሰዓት ያለማቋረጥ ”ጩኹ” ብሎን እኔም ‘አንጮኽም’ ብዬ ምክንያቶቼን ደርድሬ ነበር። የዓመት ፈቃዱን ተሟሙቶ የወሰደና ቤተሰቤ ዘንድ ደርሳለሁ ያለ፤ ዘመድ ታሞበት ለመጠየቅ የሚጓጓዝ፣ ለቅሶ የሚደርስ፤ ማህበራዊ ጉዞ ያለው፤ የስታፍ ጉዞ ብቻ ሁሉም ሊስተጓጎል።
ልብ አድርጉ፦ የገበያ ማቆም አድማ ለምን ጠራ አልወጣኝም። ያ የራሱ መንገድ ነው። ሆኖም እንደ ጆሴፍ ስታሊን ፦ በአድማው ያልተሳተፈን ግደሉ ምን ማለት ነው?! አንዳንድ የዋሆች በአርትዖት (Edit) ተስተካክሏልና ነገር አብርዱ ሲሉ አስተውያለሁ (ለመሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋ አዋጅ በአርትዖት ይቆማል ወይ?!)
ደግሞስ ህዝብ ትግልህን ከጥርጣሬ አልፎ በሞት ፍርሀት እየተመለከተው፥ ፍሬ አፈራለሁ ብለህ ታስባለህ?!
በወገኔ ላይ የሚቃጣ የትኛውንም የእልቂት ጥሪ አወግዛለሁ። የወገኔን ደም ከሚያፈስና ከሚያስፈስስ ሁሉ ጋር ህብረት የለኝም።

Filed in: Amharic