>
3:39 am - Tuesday January 31, 2023

ይሄ ግፍ ቁጭት፣ መጠቃትና ከጀርባ መወጋት አርግዞ ምን እንደሚወልድ መገመት አያስቸግርም (ቬሮኒካ መላኩ)

የጭቁኖች የበደል እንጉርጎራዊ ዜማ የትም ምንጊዜም ይዘመር እንጅ ቅላፄውና ምቱ ሜሎድውና ሪትሙ ተመሳሳይ ነው። ለዚህም ነው በሌላው በሐውርት ላይ በሚገኙት በበርማ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመ ድርጊት ሲያሳምመን የከረመው ።
ወያኔ በወገናችን የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ የማያባራ የዘር ማጥፋትና የመሬት ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ መላው የአማራ ህዝብ የተባበረበት ወልቃይትን ወደ ነባሩ የጎንደር ግዛት የመመለስ ትግል ከተጀመረ አመታትን አስቆጥሯል ። ትግሬ ወያኔዎች ይሄንን ህጋዊ የሆነ የህዝብ ጥያቄ የተለያየ ስያሜ በመለጠፍ በህዝብ የተመረጡ የወልቃይት ህዝብ ተወካይ ኮሚቴዎችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን አማሮች ለግድያና ለእስራት ሰለባ ዳርገዋል። ይባስ ብለው በቅርቡ የህዝቡን ጥያቄ ሊያዳፍንልን ይችላል በሚል ይመስላል በቅማንት ማሊያ የአማራን  ህዝብ ከነባር ይዞታው ለማፈናቀል ያለሙ መሆናቸውን ሾልኮ የወጣው መረጃ ያመለከተ ሲሆን በሌላ በኩል የአማራ ህዝብ ጥያቄ ያልሆነ የግጨውና ጎቤ  ጉዳይን  ፈተንላችሗል በማለት ጎቤ የተባሉ ሰፋፊ የእርሻና በእጣን ምርት የታወቁ ቦታዎችን ለትግራይ አስረክቦ በአማራ ህዝብ ትግል ላይ ማሾፋቸውን ቀጥለዋል ።
ስለሆነም መቀመጫውን መቀሌ ባደረገ ኮሚቴ አማካኝነት በቅማንት ማሊያ ወንድማማች የአማራና የቅማንት ህዝብን ለማጫረስ የሚደረግ ሸፍጥ እንዲቆም እንዲሁም የግጨውን መሬት በተመለከተ ህወሃትና ብአዴን የተፈራረሙት ውል የአማራን ህዝብ የማይመለከት መሆኑ ይታወቅ።

ወገኖቼ ፊት ላይ የተፃፈውን ቁጭትና መጠቃት እንደ ትልቅ ጥራዝ እያነበብኩኝ ነው። አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ህመም አለው። አሁንም አንዳንዶች ከታሪክ ለመማር አለመቻላቸው ያሳዝናል። እነዚህ ህዝቦች ይሄን መሬት ወስደው በሰላም እንኖራለን ብለው ካሰቡ የክፍለ ዘመኑ ሞኞች ናቸው ።

በ 20ኛው ምእተ አመት ጀርመን ውስጥ ብቅ ብሎ አለምን በአንድ እግሯ ያቆመው ሂትለር ዝም ብሎ እንደ ሙጃ የበቀለ አልነበረም ። ሂትለር የጀርመን ህዝብ የመገፋት ፣ የቁጭት ውጤት ነበር ።
ጀርመን በአሻጥረኞች ከጀርባዋ ባትወጋ ኖሮ እንደ አዶልፍ ያለ መሪ ባልወለደች ነበር። ጀርመን ሉአላዊ ግዛቶቿን ” ቨርሳይሌ ውል ” ተነጠቀች ይሄን ያስፈፅም ዘንድ እንደ እኛው ብአዴን ያለ አሻንጉሊት የሆነ Weimar Republic የሚባል ተላላኪ ስልጣን ላይ ቁጭ አደረጉለት። ከቨርሳይሌ ውል በኋላ የጀርመን ህዝብ ቂም አረገዘ ። የእርግዝናው ወራት ሲጠናቀቅ ሂትለር የሚባል ልጅ ተወለደ። ከዛ በኋላ በአውሮፓ የሆነውን ስለምትውቁት እዚህ መፃፍ አያስፈልገኝም።

አሁን ብአዴን የትግሬ ተላላኪነት ኮንትራቱን እንደ ጀርመኑ Weimar አደገኛ ውል በመዋዋል የአማራን ህዝብ ከጀርባው እየወጋው ነው። ይሄ ግፍ ቁጭት፣ መጠቃትና ከጀርባ መወጋት አርግዞ ምን እንደሚወልድ መገመት አያስቸግርም። የፖለቲካ ሳይንቲስቶች “ማንም ሰላምን የሚፈልግ ለጦርነት ይዘጋጅ ።” የሚል ብሂል አላቸው። እኔ ጦርነት እያወጅኩኝ አይደለም። ነገር ግን አማራ ህዝብ ውስጥ ያረገዘ ነገር ይታየኛል። አማራ መሬቱን ተነጥቆ ዝም ይላል ማለት ዘበት ነው። አሁንም የከፋው ነገር ሳይመጣ በፊት ወልቃይት ፣ጠገዴና ጠለምትን መመለስ የፖለቲካ ብልህነት ነው። ያ ካልሆነ ግን በህዝብ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን መፃኢ ሁኔታ ማሰብ አልፈልግም።

Filed in: Amharic