>
5:02 pm - Sunday December 5, 2021

አማራ፣ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ሶማሌ፣ደቡብ፣አፋር፤... የሕወሃት ታላቁ ቅዠት! (ዮናስ ሃጎስ)

የሰሞኑ “የሶማሌና ኦሮሚያ ድንበር ግጭት” ዛሬ የጀመረ ጉዳይ አይደለም። ከዓመት ሁለት ዓመት በፊትም ብዙ ሰዎች የሞቱበትና ከ40 ሚልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት የወደመበት ግጭት ተፈጥሮ ነበረ። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በደንብ የተቀናበረና የክልሎቹን ከፍተኛ ሹማምንቶችን ያሳተፈ መሆኑ ነው።

***

ሕወሃት በኢትዮጵያ ላይ ላመጣችው ቋንቋና ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ስጋት የሆኑባት የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ናቸው። ለምን ቢሉ የአማራ ሕዝብ በመጀመርያውኑም ‹የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ› እና ‹አሃዳዊ አስተዳደርን ለመመለስ የሚታገል› ተብሎ ተፈርጆዋል። የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ ተገንጣይ› የሚል ስም ተሰጥቶታል። ሁለቱም በሕወሃት አላቸው ተብሎ የተያዘባቸው አጀንዳ የሐገሪቷን ሐብት እየቦጠቦጠች በሰላም ቢልየነርና ትሪሊየነር ለመሆን ለምትሻው ሕወሃት መልካም ዜና አይደሉም።
***
ከጎንደር ተጋሩዎች ተፈናቀሉ የተባለ ጊዜ ሕወሃት በአማራ የሚገኘው የቀኝ እጇ ብዓዴን ይህን ለማክስም ፍላጎት አለማሳየቱ፣ በኦሮምያ ታላቅ ተቃውሞ በተቀጣጠለ ጊዜ የኦህዴድ ባለስልጣናት ከተቃዋሚዎቹ ጋር በኮድ መጫወት መጀመራቸው ሕወሃት የአደጋ ጊዜ መውጫ ፕላን እንደሚያስፈልጋት በደንብ ያመላከታት ሆኖ አግኝታዋለች። በወቅቱ እኛ ብቻችንን አይደለንም ዓይነት ስሜት ለመፍጠርም በአፋር እና በሶማሊ ክልል ሰላማዊ ሰልፎች እንዲደረጉ ማስተባበሯ አይዘነጋም። የአማራንና የኦሮሞ ተቃውሞዎችን በመቃወም በሁለቱ ክልሎች የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተያዘው መፈክር ሁሉ ከላይ ለአማራና ለኦሮሞ ህዝቦች በሕወሃት አላቸው ተብሎ የተገመተውን አጀንዳ በትክክል ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
***
በኦሮምያ እነሙክታርን አሰናብታ ሌሎች አሻንጉሊቶችን ከተካች በኋላና የአማራው ተቃውሞ በመሳርያ ሐይል እንዲቀዛቀዝ ካደረገች በኋላ ከዚህ በኋላ ወደርሷ ያነጣጠረ ተቃውሞ እንዳይነሳና የፌደራል ስርዓቷ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ‹አጃዒብ› የሚያሰኘውን እርምጃ የወሰደችው የሶማሊ ክልል ሐይሎችን (ፖሊስና ሚሊሺያ) በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው ትጥቅ ማስታጠቅ ነው። ይህን ዘመናዊ ትጥቅ የያዘ የክልሉን ልዩ ሐይልን ከዓመት ሁለት ዓመት የተቀሰቀሱ ግጭቶችን እንዲያገረሻቸውና ኦሮምያ ከተቃውሞው ፊቷን አዙራ ወደ ሶማሊ እሰጥ አገባ እንድትገባ የዘየደችው መላም ፈር እየያዘላት ይመስላል።
***
እቅዷ በደንብ እየሰመረ ከሄደ በሰሜን በኩል ከአማራው ለሚነሳው ተቃውሞ አግዓዚን ማሰማራትና የኦሮምያ ነገር ሲያገረሽ ደግሞ የሶማሊ ልዩ ሐይልን በማሰማራት ሳይቃጠል በቅጠልን ጨዋታ መጫወት ትችላለች።
***
ጨዋታዋ እየሰመረ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም። ለምን ቢባል በተቃዋሚው ጎራ ያሉት የአማራና ኦሮሞ ሐይሎች አሁንም እንደተኮራረፉ ነው። ጃዋር ‹በኛ ቢል ዝም ብላችሁ ተጋበዙ› ያለበት ፕሮቴስት ከከሸፈ በኋላ አሁን በድጋሚ እርዳታቸው እንደሚያስፈልገው ሲረዳ ‹አንድ እኮ ነን› ሲላቸው የአማራ ሐይሎች ‹ሞኝህን ፈልግ› እያሉት መሆኑን ከዓመት በዓል ውጭ ያለው የፌቡክ እንካስላንትያ በደንብ ያሳያል። ከሁለት ዓመት በፊት ጠንካራ መሰረት ላይ ተጥሎ የነበረው የአማራ ኦሮሞ ሐይሎች ፍቅር ጃዋር የራሱን ቻርተር አዘጋጅቶ ውኃ ከከለሰበት በኋላ በድጋሚ ሌላ ፍቅር ለመመስረት በቅርቡ የሚሳካ አይመስልም።
***
የሕወሃት ጨዋታ ግን እጅግ አደገኛ የሆነ አካሄድ መሆኑን ሕወሃት ራሷ የገባት አይመስለኝም። ለአንድ ሐገር ዋናው አደጋ ‹ሲቭል ዋር› ነው። ሰሞኑን እንደምንሰማው ዓይነት ሞት ከዚህም ከዚያም ወገን የሚቀጥል ከሆነ ይህ ነገር ወደ ሲቭል ዋር እንደማይቀየር ማንም ዋስትና ሊሰጥ አይችልም። ”ሲቭል ዋር”ን ደግሞ እኔ ነኝ ያለ የታጠቀ ዘመናዊ ጦር ሊያቆመው አይችልም። እንግዲህ ሕወሃት የፌደራል ስርዓቴን ይጠብቅልኛል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሐይል መዛባት ባላንሱን ያስተካክልልኛል ብላ የጀመረችው ይህ ጨዋታ አንድም ተሳክቶ የኦሮሞና አማራ ሐይሎች ፀባቸውን ‹ውሾን ያነሳ…› ብለው እርግፍ አድርገው ትተው ስትራቴጂካዊ ወዳጅነትን ሊፈጥሩበት ይችላሉ። አሊያም ከቁጥጥሯ ውጭ ሆኖ ሲቭል ዋር ይነሳና እሳቱ ሕወሃትን ጨምሮ ሁሉንም ያጠፋቸው ይሆናል። መጨረሻውን ማየት ነው እንግዲህ…

Filed in: Amharic