>

እንዲጠፋ የተፈለገው ማን ነው? (ሃብታሙ አያሌው)

የህወሓት አለቃ መለስ ዜናዊን መልዓከ ሞት ከቅዱሷ ምድር እስከ ወዲያኛው ቢያስወግደውም። የደገሰልን የ “ኢንተር ሃሞይ” እልቂት የዘር ማጥራት ዘመቻ በደኖ፤ አርባ ጉጉ፤ ጉራፈርዳ፤ በአማራን ጥረገው እቅድ “በሞፈር ዘመት” ስያሜ ስንቱን ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ጭዳ ሲያደርገው የመለስ እቅድ በስልጣን ለመቆየት ህዝብ መከፋፈል መግዛትና በኋላም ዶሮ ለቅማ (በልታ) የተረፋትን ጥሬ በእግሯ ጭራ በትና እንደምትሄደው፣ ሲሄድ በትኗት ለመሄድ የሚያመቻቻት ሀገር ስለመሆኗ ብዙዎች ሲናገሩ ጥቂቶች በተቃራኒ ሲከራከሩ ነበር። በተናጠል መለስ እንደ ጠላት የሚቆጥረው በድርጅቱ በህወሓት በኩል ሊያጠፋው ያቀደው አማራን ነው፤ የለም ኦሮሞን ነው፤ ጋምቤላን ነው ወ.ዘ.ተ ሲሉ በሌላ ወገን ኦርቶዶክስን ነው ኢስላምን ነው የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርቡ ነበር። እውነታው ግን ከወዲህ ነበር መለስ እና ህወሓት የቻሉትን ያህል ገዝተው አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል ዘርፈው ሲሄዱ የሚበትኗት ለእርስ በእርስ ጦርነት የሚተዋት አገር ኢትዮጵያ እንደምትሆን የነሱ ምሽግም በወዲህ አሰብን ከወሎ የቀረደደው በወዲያ ወገን ጎንደርና ጎጃምን ከሱዳን እየነጠለ ቤንሻንጉልና ጋምቤላን የሚረግጠው የታላቋ ትግራይ ማጠቃለያ ሻዕቢያን አስወግዶ አርጅቶ የተለወጠ የመሰለንን “የትግራይ ትግሪኝ” አጀንዳውን በድንገት ብቅ እንደሚያደርገው ሰሚው ለየቅል ቢሆንም ጉሮሯችን እስኪነቃ ጩህን ነበር።

ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄው ነው፤ ጉዳዩ አንድን ብሔረሰብ ወይም አንድን ሐይማኖት የማጥፋት አይደለም። እየተፈፀመ ያለው ደደቢት በረሃ የተጠነሰሰው ኢትዮጵያን ከታሪክ መዝገብ የማጥፈት አጀንዳ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የህወሓት እሳት ግሟል ነጋ ጠባ ጎንደርን መለብለብ ብቻ አልበቃውም። በአንድ ሀገር ህዝብ መካከል በሶማሊያ እና በኦሮሚያ ህወሓት ክብሪትም ቤንዚልም ሆኖ ዜጎቻችንን በነዲድ እየቀጠፈ ነው። የክልሎቹ መሪዎች በአፈ – ቀላጤዎቻቸው በኩል የህወሓትን እሳት እያራገቡት ነው። ሳልሳይ ወያኔዎቹ እነ ዳንኤል ብርሃኔ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ያለውን የእናት ድርጅታቸውን የህወሓትን አላማ በሚገባ እያሳለጡት ነው።በህወሓት ህገ መንግስት ልዩ ኃይል የሚል አደረጃጀት የለም። በመለስ ቀጭን ትዕዛዝ ለዚሁ አላማ የተደራጀው የሶማሊያ ልዩ ኃይል ዛሬ ወጣት አዛውንት ሴት ህፃናት ሳይል ኦሮሚኛ ተናጋሪውን መርጦ እየፈጀው ነው። በሺዎች የሚቆጠሩት ሀገር አልባ ሆነው እየተሰደዱ ነው። የሳልሳይ ወያኔ ጭፍሮች ትላንት ጎንደር ላይ አምስት የህወሓት ሰላይ ተፈናቀለ ብለው አቧራ ሲያጨሱ ነበር። የሀገር መከላከያ ነኝ የሚለው የሳሞራ ቡድንም ሔሊኮፕተር እና አውቶቡስ መድቦ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች የህወሓት ጥብቅ (ጠብቆ ይነበብ)አባላት የሆኑትን ትግሬኛ ተናጋሪዎች የስጋት ቀጠና ካለው ስፍራ ሲሰበስብ ነበር።

ያ መከላከያ ዛሬ የለም ያ የአጋዚ ልዩ ኃይል የሚገድለው ከሌለ ወደ ባህርዳር እና ወደ ሓረር የሚሄድበት ጉዳይ የለም ኃይለማርያምም የእንቁጣጣሽ ጭፈራው ድካም ስላልወጣለትና ስላላዘዙት በጉዳዩ ላይ ከመናገር ተቆጥቧል። የሓይማኖት መሪነኝ የሚሉት አባ ማቲያስም የህወሓትን ትእዛዝ እየጠበቁ ዝምታን መርጠዋል። እሳቱ ያለልክ እየተራገበ ነው። ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገብተን የመለስን ሌጋሲ ከታቀደው ቀድመን በማሳካት እንደ ሀገር እንዳንጠፋ ነገሩን በጥንቃቄ ብንመለከተው መልካምነው። በጋራ ተነስተን ሰደድ እሳት ሆነን ህወሓትን ማስወገድ የችግራችን ሁሉ ዋና መፍትሄ መሆኑን አውቀን በዚህ ላይ አነጣጥሮ ለህዝቡ አቅጣጫ የሚሰጥ የጋራ ጉባኤ ቢጠራ መልካም ይመስለኛል። የተናጥሉ ጮህት ይሰባሰብ ያን ጊዜ የህወሓት ቅጥር ይፈርሳል።

Filed in: Amharic