>
5:13 pm - Tuesday April 19, 6281

የመቀሌ ጉራማይሌ (ግርማ ሰይፉ ማሩ)

ጉብኝት አዋሳ ላንጋኖ ብቻ ነው ያለው ማነው? ያልን ሰዎች ትግራይ መቀሌ ለጉብኝት ጎራ ብለንለ ነበር፡፡ አንድ አንዶች ኤርትራ ሊሄዱ ነው ሲሉን ተመስገን ደሳለኝን ኤርፖርት ያዩት ሰዎች ደግሞ ተሰደደ ማለታቸውን ሰማን፡፡ አውሮፕላን ልትጠልፉ ነው ወይ ያሉንም ፌዘኞች ነበሩ፡፡ ስደትና ጠለፍ የትግላችን አካል አለመሆኑን የተረዱት ቢሆኑ ይህን ግምት ይተዉት ነበር፡፡ በቁጭት የተነጋገርንበት ግን አሰመራ የሰው ሀገር ሆኖ መሄድ ያለመቻላችን እንዲሁም ምፅዋ ከመሄድ ሞምባሳ መሄድ መቅለሉን ነው፡፡ ይህ የገዢዎች አጥር ፈርሶ አሰመራ ምፅዋ እንደምንሄድ ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
በመቀሌ ባሰለፉክት ቆይታ የተረዳሁት ጥቂት ሰዎች በቁርጥና ውስኪ ቤት የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛው ህዝብ ደግሞ የእለት ኑሮ ለመግፋት የሚውተረተር መሆኑ ነው፡፡ በሰራ ቀን በቡና መጣጫ ሰፈሮች የሚገኘው ወጣት ብዛት የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ከአንድ የወዳጃችን ዘመድ ጋር የነበረን ቆይታ ነው፡፡ ሌላው ካስፈለገ በሌላ ቀን እመለስበታለሁ፡፡
ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ሰሙን ጥበቡ ብለነዋል፡፡ ጥበቡ በዚህ ጉዳይ ሰሙ እንዲነሳ ፈቃደኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥበቡን ያገኘነው ከሰማዕታት ሀውልት ጉብኝት በኋላ 16 በሚባለው መዝናኛ ሰፈር ነው፡፡ ባንኮኒ ላይ ሆነን ስንጫወት ፈንጠር ብሎ ብቻውን ተቀምጦ ይተክዛል አብሮን ቢሆንም ልቡ ከእኛ ጋር አልነበረም፡፡ አንድ ሌላ ጓደኛውን ጠርቶት ሲቀላቀለን ከብቸኝነቱ ተገላገልን ብለን አርፈን እራት በልተን ሌላ ቤት ለማይት ጎራ አለን፡፡ ብቸኝነቱ ፍላጎት ስለመሰለን አላሰጨነቀንም፡፡ አብረውን ያሉት እነ አርሃያ እና ክብሮም በጫወታ ወጥረው ስለያዙን የጥበቡ ነገር ብዙም ልብ አላልነው፡፡ አርሃያና ክብሮም ትክክለኛ ሰማቸው ነው፡፡

ጥበቡና እኔ ጎን ለጎን ቁጭ ብለን በሙዚቃ መሃል አንድ አንድ ነገር እንጫወታለን፤ ከፊት ለፊታችን ተመስገን ደሳለኝ እና የጥበቡ ጓደኛ ቁጭ ብለዋል፡፡ ድንገት ከእኔ እና ጥበቡ ፊት ለፊት አንዲት ሴት በምሽት ዳንስ አለባበስ የሆነች እና አንድ የቪዲዮ ካሜራ የያዘ ወጣት ቁጭ አሉ፡፡ ጥበቡ እነዚህ ሰዎች እየቀረፁን ነው ወይ? ብሎ ሲጠይቀኝ አዎ አልኩት እንደቀልድ፡፡ ጥበቡ ከእኔ ጋር የነበረው ጫወታ ጠፋበት ይርበደበድ ጀመር፡፡ ሰዎቹ ተነስተው ወጡ፡፡ ቀስ ብሎ በጆሮዬ ግርማ አንተ ታወቂ ስለሆንክ ምንም አትሆንም እኔን ግን አያኖሩኝም አለ፡፡ ቀልዱን መስሎኝ ምን ያደርጉሃል? ሰለው ፍርሃት ያመጣለትን ሁሉ ነገረኝ፡፡ ፍርሃቱ ገባኝ፡፡ ሰቀልድ ነው እየቀረፁን አልነበረም ካሜረው እኮ አልበራም ብዬ ለማረጋገት ሞከርኩ፡፡ እጁን ሰጥቶኝ መታሁለት እንድምልለት ጠይቆኝ ማልኩለት፡፡ እጁን ጭኔ ላይ አድርጎ ለመረጋጋት ሞከረ፡፡ እጁ ሲንቀጠቀጥ ይሰማኛል፡፡ ግርማ ልብ አላልክም እንጂ ድሮም ከእናንተ ጋር መሆን አልፈለኩም ለዚህ ነው ራቅ ብዬ ቁጭ ያልኩት ብሎ የፍርሃቱን መጀመሪያ ነገረኝ፡፡
ሳቅም አዘንም ተሰማኝ፡፡ ቤት እንቀይር ብለን ስንወጣ ባለካሜራው ሰራውን እየሰራ ነው፡፡ አብራው የነበረችውን ልጅ ከምሽቱ ድባብ ጋር ይቀርፃታል፡፡ ሌሎችም ታዳሚዎችም አብረው አሉ፡፡ በግምት በፊልም ቀረፃ ላይ ናቸው፡፡ የጥበቡን ልብ ግን ሳያውቁ እሰኪጎን ድረስ በፍርሃት አርበድብደውት፡፡ ጥበቡን ጠርቼ እመነኝ ይኽውልህ ሰዎቹ በሌላ ስራ ላይ ናቸው፤ ብዬ እንዲረጋጋ መከርኩት፡፡ የምታውቀው የደህንነት ሰው ቢኖር እንኳን እየጠበቁን ነው ብለህ አስብ፤ ግፋ ቢል ነገ ጠርተው ከእኛ ጋር ምን ምን እንዳደረክ ይጠይቁሃል በትክክል ያደረከውን ተናገር አልኩት፡፡ የተረጋጋ መስሎ ወደ ቀጣዩ ቤት እርሱ ባመጣልን ጓደኛው መሪነት ገባን፡፡ ጥበቡ ድንገት ተሰወረብን እምጥ ይግባ ስምጥ ማወቅ አቃተን ጓደኛው ደውሎ መሄዱን አረጋገጠ፣ ጥበቡም በማግሰቱ ጠዋት ደውሎ ይቅርታ ማታ ተረብሼ ስለረበሽኳቹ ብሎን በዝርዝር ፍርኃቱን ነገረን፡፡ ይህንን ፍርሃት ቀን ስንጎበኘው የነበረው የሰማዕታት ሀውልት ላይ ያየነው ተጋድሎ ያመጣው ሳይሆን በዚህ ትግል ጀርባ ለድል የበቁት እና በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ዘርተውት መሆኑን መረዳት አያሰቸግርም፡፡ ስንት የትግራይ ልጆች በእንደዚህ ያለ ፍርሃት ስር እንደወደቁ ማሰብ አያሳቸግርም፡፡

Filed in: Amharic