>
5:16 pm - Monday May 23, 5605

አጥብቦ ማስብ እንጅ አካል መጎዳት ከስኬት አያግድም (ነቢዩ ሲራክ)

* የእኛዋ እህት እመቤት ወደ አለም መድረክ ከፍ ስትል
የማለዳ ወግ…ትንታጓ የትነበርሽ ንጉሴ ፤ በሔለን አደም ኬለን መንገድ
* ተጽዕኖ ፈጣሪነዋ እመቤት የትነበርሽ እንኳን ደስ ያለሽ …
* ክብር ከሚገባው ክብር እሰጣለሁ …

ሰው ሁኖ ተፈጥሮ በተሰጠን አቅል ልክ አለማሰባችን ሩቅ እንዳንደርስ ያግደናል ፣ ሰፊውን አድማስ ተከትለን የሚበጅ ሰፋፊውን ጠቃሚ መንገድ ይዘን እንዳንጓዝ ፤ ላቅ ወዳለው ሰብአዊ መንገድ እንዳናስብ አጥብበን የምናደርገው ጉዞ ከስኬት አርቆናል ። በዚህ ሁሉ መካከል አጥብበን ማሰብ እንጅ የአካል ጉዳተኛ መሆን ከስኬት እንደማያግደን ብዙ ህያው መረጃዎችን ተመልክተናል ፤ እየተመለከትንም ነው ! በልጅነት የአይን ብርሃኗን ያጣችውን የእኛን እህት የየትነበርሽ ንጉሴን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እውቅና የሰጠ ሽልማት ሰምቸ ብዙ በዙሪያየ የማውቃቸውን ለስኬት የበቁ የአካል ጉዳተኞችን አስታወስኩ ። ከትውልድ መንደሬ ተነስቸ ወንድም Fisseha Gebretsadik ፍስሃ ገብረ ጻዲቅ የአካል ጉዳተኝነት ሳይገድበው ተግቶ በመስራቱ የለወጠን ህይዎቱን ዛሬ አስታውሸ ደስ አለኝ …ሁለት አስርት አመታት ተሻግሬ በቅርብ በምጡቅ እሳቤና በስኬት ጉዞው የማውቀውን ኢኮኖሚስቱ ወዳጄ ሰይፈም ሌላው አካል ጉዳት ሳይገድበው በሃገሪቱ አለ በተባለ የገንዘብ ተቋም እየሰራ ያለ ወንድም ነው … አዎ የአካል ጉዳተኛ ሆነው ራሳቸውን የቀየሩ ፤ ለሃገር ተስፋ የሆኑ ብዙ የሃገሬ ልጆች አሉ ። የሁሉም ወገኖቸ አካሄድ እንደጉራማይሌ ይለያያል ፤ ሁሉም ያስደስታል ቢባልም የየትነበርሽ ፋና ወጊ ጉዞ ግን ተጽዕኖ መፍጠር ተጨምሮበት ጎልቶ ይታይበታልና ይለያል … እናም በእኔ እሳቤ እህት የትነበርሽ የጀመረችው ጉዞ የአይን ብርሃኗንና መስማት ማናገር የማትችለው ሔለን አደም ኬለር Helen Adams Keller መንገድ ጋር ቢገናኝብኝ የሚሰማኝን ለመተንፈስና ወደድኩ …

ሔለን አደም ኬለር Helen Adams Keller ማን ናት ?

አብዛኛች የእኔ ዘመን ተማሪ በልጅነት የትምህርት ዘመን የአይን ብርሃኗንና መስማት ማናገር የማትችለው ሔለን አደም ኬለር Helen Adams Keller አትረሳንም። የአካል ጉዳተኛ መሆን ለዚያውም የዚህን አለም ህይዎት ማየትና መስማት አለመቻል ያህል ጉዳት የመክበዱን ያህል ያውም እንደ ሴት ጉዳት ሸክም ተጽዕኖውን ችሎ ነገን
ማሸነፍ ፤ ነገን ከራስ አልፎ ለቀሪው ጉዳተኛና ለአካለ ሙሉው የሰው ልጅ ህይዎት መሻሻል አልፎ ተርፎ ለሰብአዊ መብት መከበር ፋና ወጊ ሆኖ መገኘትን ሔለን አደም ኬለር Helen Adams Kelle ተምረነዋል። እአአ ከሰኔ 27, 1880 – ሰኔ 1, 1968 ዓም 87 ዓመታትን ባለንባት ምድር በህይዎት የኖረችው ሔለን ከምድረ አሜሪካ አልፎ በመላው አለም ተጽኖ መፍጠር የቻለች ትጉህ እመቤት ነበረች። ሔለን አደም ኬለር Helen Adams Kelle ከልጅናት እስከ እውቀት ያለፈችበት የህይዎት መንገድ በእርግጥም የአካል ጉዳተኛ መሆን ከስኬት እንደማይገድብ አለም በቀዳሚ ምሳሌነት ተምሮበታል ።

በልጅነት እንቦቃቅላ እድሜ የአይን ብርሃኗንና መስማት መናገርን በረከት የተነጠቀችው ሔለን አደም ኬለር Helen Adams Kelle የፈጣሪ ስራ በእሷ ይገለጽ ዘንድ ሔለን ከልጅነት እስከ እውቀት ተግታ ተምራና ራሷን አስተምራ ለከፍተኛ ማዕረግ አብቅታለች ። ለከፍተኛ ማእረግ ራሷን ካበቃች በኋላም በህይዎት ዘመኗ ባደረገችው የበጎ ስራ እንቅስቃሴ ከአሜሪካ ኮንግረስ የደረሰ ተጽዕኖን ፈጣሪ ለመሆን በቅታለች። በጻፈቻቸው ድርሳናት ከትናንሽ እስከ ትላልቅ የትምህርት ማዕከላት ተደራሽ አስተማሪና አነቃቂ ስራዎቿን አዳርሳለች። ሄለን ኬለር Helen Keller በተለያዩ አጋጣሚዎች ደብዳቤዎችን ለተለያዩ ተቋማት በማቅረብ ማየት ለተሳናቸው የአካል ጉዳተኞች እርዳታን ከማሰባሰብ ፤ በጦርነት የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ተጎችዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በማማከር ፤ በመደገፍ ኑሮን ከማሻሻል ባለፈ በትምህርት ራሳቸውን እንዲያንጹ አግዛለች።

በርቱዕ አንደበቷ ፣ ልዕልናው ከፍ ባለ እሳቤ አመለካከቷ ፣ በአካል ተጎጅ ሴት እንደ መሆኗ ፣ ከአካል ጉዳተኞነት በላይ በሴትነት የሚደርስባትን ጫና ተቋቁሟ ለድምጽ አልባ አካል ጉዳተኞች ድምጽ ዋስ ጠበቃ ናት … በአካል ጉዳት መገደብ የአእምሮ ደሃ ያለመሆን እውነታ በግላጭ በአደባባይ ደጋግመን ያየነው ቢሆንም እውነቱን በእማኝ መረጃ ማስረጃ ደጋግማ የነገረችንን የእኛዋ እህት እመቤት የትነበርሽ ንጉሴ ናት ። የትነበርሽ ትጉግ እህት ናት “የትነበርሽ ቦረና አካዳሚ” የሚባል ት/ቤት አሰርታለች ። ት/ቤቱን የከፈተችው ደግሞ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ መድረኮች ላይ ለምታቀርባቸው ጥናታዊ ፅሁፎች የሚከፈላትን ገንዘብ በማጠራቀም ሲሆን ተማሪዎችን በስነ ምግባር የታነጹ ትውልዶች ማድረግ ቀዳሚ ተግባሯ መሆኑን ደጋግማ ተናግራ ለትግበራው ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች ። የትነበርሽ በ2003 በአካል ጉዳተኞችና በኤችአይቪ ዙሪያ ባደረገችው ከፍተኛ አስተዋፅዖ በደቡብ አፍሪካ የሂውማኒቴሪ አለም አቀፍ ተሸልማለች ። በምትናገርበት አጀንዳ የጉዳዩ አንኳር በአጭር ፤ በማያሻማና በሚገባ ቋንቋ በማስረዳት ትጉህ የሆነችው የትነበርሽ ተሰሚነቷ ከሃገር ቤት አልፎ ተርፎ አለም አቀፍ እየሆነ መምጣቱ የድካም ልፋቷ የትጋት ጥረቷ ክፍያ ይሆን ዘንድ ግድ ሆኗል ። እናም የትነበርሽ ዛሬ በአሜሪካ የሚገኘው Center for the Right of Ethiopian Women የተባለ ድርጅት “የዘመኑ ጣይቱዎች”ብሎ ከመረጣቸው በአሜሪካና በኢትዮጵያ ከሚገኙ አስር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶችን አንዷ አድርጎ መርጧታል ።

የትነበርሽ ንጉሴ ማን ናት ?

ስለየትነበርሽ ሙሉ መረጃ ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች ውስጥ የአትላንታው አድማስ ራዲዮ አዘጋጅ ወዳጄ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ዳኜ ያቀረበው መረጃ እህት የትነበርሽ ማን ናት ? ለሚለው ግሩም መረጃ ይሰጠናል ። ” Ethiopian Center for Disability & Development በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት በማገልገል ላይ የምትገኘው የትነበርሽ ጥር 24 ቀን በ1975 ወሎ አማራ ሳይንት ተወልዳ በስድስት ዓመቷ ባጋጠማት የሜኔንጃይትስ ሕመም የተነሳ የዓይን ብርሃኗን በማጣቷ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣችው፡፡ አዲስ አበባ ከአያቶቿ ጋር ለመኖር ብትመጣም ለዓይነ ስውራን የሚሆን ት/ቤት ባለመኖሩ ወደ ሻሸመኔ ተልካ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምራ ተመልሳ አዲስ አበባ መጥታለች፡፡ ከ7ተኛ ክፍል እስከ 12ተኛ ክፍል በተማረችበት ዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤት ለእሷ አዲስ ሕይወት እንደመጀመር እንደሆነ የትነበርሽ ትናገራለች፡፡ … እናም እንዳሰበችው በትምህርቷና በእንቅስቃሴዎቿ በአጭር ጊዜ በመምህሮቿም ሆነ በተማሪዎች ዘንድ እውቅናን አተረፈች፡፡ በዚህም የት/ቤቱ የተማሪዎች መማክርት ም/ፕሬዝዳንትና የህዝብ ግንኙኝነት ኃላፊ፣ የሙዚቃ ባንዱ ድምፃዊ፣ የስነፅሁፍ ክፍሉ ገጣሚ በመሆን መሳተፍ ጀመረች፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለች ማትሪክን በአጥጋቢ ውጤት አልፋ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገባች፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የሰራችው በሕግ ትምህርት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሶሻል ዎርክ ሁለተኛ ዲግሪዋ ሰርታለች፡፡

የትነበርሽ አሁን በምትሰራበት የአካል ጉዳተኞች ማዕከል ምን ምን ስራ እየተሰራ ነው ?
* የአካል ጉዳተኞችን አጠንክሮ የልማት አጋር ማድረግ
* አካል ጉዳተኞች በቡድን ተደራጅተው ሲመጡ ይደግፋል
(በዚህ ፕሮግራም በዓመት ከ3ሺህ በላይ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ )
* ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል ማመቻቸት፣ እነሱን የሚመለከቱ የሥራ ማስታወቂያዎች ሲወጡ በኢሜልና በስልክ ማሳወቅ፣ ሕፃናትን ለትምህርት ማዘጋጀት
* በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጀመሮ የነበረውን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ የትምህርት አካባቢ ወደ መቀሌና አዋሳ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሰፋ አድርጓል፡ ወደፊት ደግሞ በሌሎች ክልሎች ለመስራት ዕቅድ ተይዟል
* በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግምቱ ወደ 300ሺህ ብር የሚጠጋ ዲጂታል ስቱዲዮ አስገንብተው ለዩኒቨርስቲው አስረክበዋል፡፡
* ከዚህ በፊት ለዓይነ ስውራን የሚዘጋጀው የብሬል መፅሀፍ ከፍተኛ ገንዘብና ቦታ የሚጠይቅ በመሆኑና በየጊዜው የሚለዋወጠው የትምህርት ፖሊሲና ካሪኩለም አመቺ ባለመሆኑ ተማሪዎች በቀላሉ በሞባይላቸውም ሆነ በሚሞሪ ላይ በድምፅ የተቀረፀ የትምህርት መረጃ ያገኛሉ፡፡ ወደፊትም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተመሳሳይ ዲጂታል ስቱዲዮ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለማስገንባት እየተነጋገሩ ነው፡፡

የትነበርሽ ከአትላንታው ድንቅ መጽሔት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ በአካል ጉዳተኝንቷ የደረሰባት ተጽዕኖ እንዳለ ተጠይቃ ስትመልስ እንዲህ ብላለች “የትነበርሽ አካል ጉዳተኛነቷን አንድም ቀን አማርራው አታውቅም፡፡ እንዲያውም “ለእኔ ስኬት ከጥረቴ ባሻገር 50 በመቶውን ድርሻ ያበረከተው አካል ጉዳተኛነቴ ነው” ትላለች፡፡ “ብዙዎች ሴት ሆነሽ በዚያ ላይ አካል ጉዳተኛ ሆነሽ እንዴት ይህን ሁሉ ለመስራት ቻልሽ ? እያሉ እንደ ችግር የሚያነሷቸውን ነገሮች እኔ እንደ ዕድል ነው የማያቸው፡፡ ማንኛውንም ነገር ከተቀበልሽው ውስጡ ያለውን ማር ከፍተሸ ትበያለሽ፤ ካልተቀበልሽው ደግሞ ውስጡ ማር አይኖርም ብለሽ ስለምታምኚ እንደተራብሽ ትኖሪያለሽ፡፡ ዋናው ቅሉን የማመንና ያለማመን ጉዳይ ነው፡፡” በማለት መልሳለች

የትነበርሽ ተግታ ማንነቷን ባሳየችበት የህይዎት ፈታኝ ጉዞ ከፍ ያለ አለም አቀፍ ሽልማት የማግኘቷ መረጃ ብዙዎቻችን አስደስቶናል ይህችን መረጃ ሳካፍላችሁ ክብር ለሚገባው ክብር እንሰጥ ዘንድ አበረታታለሁ … እናም ሁሌም በምታነሳቸው ቁምነገሮች በላይ በተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ራሷን ከፍ ካለ ደረጃ ያስቀመጠችውን የማከብራትን ጀግናዬን እህት የትነበርሽ እንኳንም ደስ አለሽ እላለሁ !

ክብር ለሚገባው ክብር እሰጣለሁ !

ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 19 ቀን 2010 ዓም

Filed in: Amharic