>
3:52 am - Monday July 4, 2022

ለህወሐት ለሸጡን ባንዳዎች ተመጣጣኝ መልስ ያስፈልጋል (ያሬድ ከፍያለው)

 

ላለፉት 26 አመታት በብአዴን፣ ኦህዴድ እና ሌሎች አሻንጉሊት ድርጅቶች ስር  ተጠልለው   የህወሐትን ተልእኮ ሲያስፈጽሙ የቆዩት ብዙዎቹ አመራሮች በአካዳሚክና ማህበራዊ ተቀባይነታቸው ደካማዎች እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ህወሐት  እነዚህን ደካሞች መልምሎ ማሰለፉ  ትርጉሙ ግልጽ ነው፤ እኔ በአቅምህ የማትደርስበትን ኑሮ እሰጥሀለሁ አንተ ደግሞ በፍጽምና ታዘዘኝ የሚል።  የመሀይሞቹ ሲገርመን ባለፉት ሁለት ዓመታት ምሁራንም ይህን የባንዳ ተግባር ተቀላቅለውታል ። እነዚህ  ምሁራን ህወሐት  ከሰማይ የተሰጠን ጸጋ ነው አይነት ስብከታቸውን ቀጥለውበታል።  እኔ እስከሚገባኝ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ማለፍ ከሚሰጠን በረከቶች መካከል ማንኛውንም ነገር አረጋግጦ መቀበል ይመስለኛል፤ ምክንያታዊነት።  ሆኖም ግን ዘረኛው ህወሀት በሚሰፍርላቸው ጥቅማ ጥቅም ተደልለው የደጉን ህዝባቸውን  ክብር  ከህወሐት ጫማ ስር ያስገቡ ምሁር ተብዬዎች ተበራክተዋል።

እነዚህ ምሁራን ተብዬዎች  ህወሐት 1000  ሰው ሲገድል 10 ነው ብለው ሲሟገቱ ይታያል።  የወገናችንን መሬት የህውሐት ወርቅ ተብዬ  ሰዎች  እየሸነሸኑ  ሲቸበችቡት ቃል እይተነፍሱም። ግዙፍ ጨረታዎችና ኮንትራቶች  ከመውጣታቸው በፊት የህወሐት ነጋዴ አባላት  ዝርዝር መረጃ እንዲደርሳቸው ሲደረግ በምን አገባኝነት ዝምታን ይመርጣሉ ።  ቁልፍ የውሳኔ ሰጪ ቦታዎች  በህወሃት  ሰዎች ሲወረርም ምንም አይናገሩም።  አዳዲስ ህጎችና መረጃዎች ይፋ  ከመውጣጣቸው በፊት የህወሀት ሰዎች ቀድመው እንዲዘጋጁ መረጃ ሾልኮ ሲወጣም ያቃሉ። ቢሊየን ብሮች የሚዘዋወሩበት የህወሐት ሰዎች የኮንትሮባንድ ንግድንም አይጠየፉም።  በአጠቃላይ ህወሀት  የሀገሪቱን የፖለቲካና ኢኮኖሚ መስኮች ተደራጅቶና አቅዶ ሲወርና ሲያስወርር  ምንም እተነፍሱም። ወይም የህወሐት የበላይነት አይታይም ብለው  ምስክር ይሆናሉ።

ለመሆኑ ምሁራን ሳይቀር ግዙፉን  የህዝባቸውን ፍላጎት፣ መብት እና ክብር  እዚህ ግባ በማይባል የግል ጥቅም ለህወሐት ለመሸጥ ለምን ተነሳሱ? ለምንስ ህብረተሰቡን የመፍራት ባህርይ አይታይባቸውም?  ትልቁ ጥያቄ። ለኔ ምክንያቱ ህብረተሰባችን እነዚህን  ትውልድ ሻጮች መጠየፍ ሲገባው በተዘዋዋሪ ማበረታታቱ ይመስለኛል። ባህላችን ከነዚህ ደም መጣጮች ይልቅ  አማራጭ አጥታ በራስዋ ሰውነት ላይ የጨከነች ሴትኛ አዳሪን ለማግለልና ለመጠየፍ ይበረታል።  እነዚህ የአሻንጉሊት ድርጅቶች አባላት  ህዝባቸውን እንደተበላ እቁብ ነው የሚያዩት። የትም አይሄድም  መልሶ ያቅፈናል በሚል። ህብረተሰቡ በማህበራዊ ዝግጅቶች ሁሉ የክብር ቦታ ይሰጣቸዋል፤ ያበረታታቸዋል። በቅርቡ ያየነው አቶ ለማ መገርሳን የክልሉን የኢኮኖሚ አብዮት አቀጣጣይ እንዲሁም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  ቅማንትና አማራ አንድ ናቸው ፈጽሞ አይለያዩም ማለቱን ተከትሎ የህዝብ ልጅ  የሚል ማእረግ ሲሰጣቸው ሰምተናል። ሆኖም አመል አይለቅምና አቶ ገዱ  የግጨውን መሬት የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ሳያውቀው ለህወሐት በቅርቡ አስረክቦአል። በአጠቃላይ  ለረጅም ዓመታት ህወሐትን ወግነው ያቆሰሉንን ሰዎች በአንድ ቀን ውሃ በማይቋጥር ንግግራቸው ማንገስ ይታያል፤ ይሰማልም።   ህዝባቸውን ለአንድና ሁለት አስርት አመታት ሲሸጡ ቆይተው  በመጨረሻ ከአገልጋይነት ህወሐት  የሸኛቸው  ባንዳዎችም ተመሳሳይ የክብር አክሊል ሲደፋላቸው ይታያል።

እኔ  እስከሚገባኝ ህዝቦችዋ በሚተላለቁባት ኢትዮጵያ ላይ ጠንካራዋን  ትግራይ ለመውለድ  እየሰራ የሚገኘውን ህወሐት መርዳት የውጭ ወራሪን  ከመርዳት የሚለይ አይደለም። እንደውም ይከፋል ባይ ነኝ።  ስለዚህ ንቀታችንና መጠየፋችንን  ከምስኪኗ  ሴትኛ አዳሪ ወደ እነዚህ ባንዳዎች ማዞሪያው ወቅት አሁን ነው።

Filed in: Amharic