>
8:22 pm - Wednesday February 8, 2023

የማይሻሻል ሕገ መንግስት በመጨረሻ ተቀድዶ ይጣላል! (ስዩም ተሾመ)

በዓለም ላይ ሁሉም ነገር ይቀየራል። ሁሉም ነገር ሂደቱን ጠብቆ ይለወጣል። በእርግጥ በዓለም ላይ የማይለወጠው አንድ ነገር ነው። እሱም “ለውጥ” ራሱ ነው። ኢትዮጲያ ውስጥ ግን ሁለት የማይለወጡ ነገሮች አሉ። እነሱም “ለውጥ” እና “ሕገ-መንግስት” ናቸው። አሁን ላይ ሀገራችን ከዴሞክራሲና ብሔራዊ መግባባት አንፃር እያሳየችው ላለው የኋሊት ጉዞ ዋናው ምክንያት የእነዚህ የማይለወጡ ነገሮች ግጭት ነው።
በመሰረቱ ለውጥ አይቀሬ (inevitable) ተፈጥሯዊ ኃይል ነው። የኢህአዴግ ሕገ መንግስት ደግሞ ፍፁም ፀረ-ለውጥ በሆነ እሳቤ የተመሰረተ ነው። እነዚህ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች በአንድ ግዜና ቦታ ላይ በፍፁም አብረው ሊኖሩ አይችሉም። ስለዚህ ሀገራችን ከዴሞክራሲና ብሔራዊ መግባባት አንፃር ለገጠማት ችግር ዋናው መስንዔ በአይቀሬው የለውጥ ኃይል እና በኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ አቋም መካከል የተፈጠረው ግጭት ይመስለኛል።

ሕገ መንግስቱ በፀረ-ለውጥ እሳቤ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ስገልፅ ለአንዳንድ የኢህአዴግ መንግስት አመራርና ደጋፊዎች አይዋጥላቸውም። ነገር ግን፣ የተናገርኩት ነገር ሃቅ ነው። የትኛውንም የኢህአዴግ አመራር “ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል” ወይም “ሕገ-መንግስቱ ለውይይትና ድርድር ይቅረብ!” የሚለውን ሃሳብ ልክ እንደ ጦር ይፈራዋል። ለምሳሌ ባለፈው አመት አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ሕገ መንግስቱ ለውይይትና ድርድር መቅረብ ይችላል?” በሚለው ጥያቄ ዙረያ ሃሳቤን እንድሰጥ ጠይቆኝ ነበር። በወቅቱ በሰጠሁት ምላሽ ትልቁ ችግር ያለው “ሕገ መንግስቱ ለውይይትና ድርድር አይቀርብም” በሚለው እሳቤ ላይ እንደሆነ ገልጬ ነበር።

ከሁለት አመት በፊት “ሕገ መንግስት፤ ዴሞክራሲና ብሔራዊ መግባባት” በሚል ርዕስ በአንድ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ዙሪያ የቀረበ ዘገባ የአቶ በረከት ስምዖን ስለ ሕገ መንግስቱ የተናገሯትን ዓ.ነገር መነሻ አድርጎ አቅርቧታል። ዓ.ነገር እንዲህ ይላል፡ “ሕገ መንግስታችን በጥልቅ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ የተዋቀረ፣ በልካችን የተሰፋ ችግር ፈቺ ሰነድ ነው”

ከፀደቀበት ዕለት አንስቶ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አመራሮች “ሕገ መንግስቱ ለውይይትና ድርድር አይቀርብም” እያሉ በእርግጠኝነት ሲናገሩ ማየት የተለመደ ነው። እኔ ግን እንዲህ ጥራዝ ነጠቅ የሆነ ነገር በሰማሁ ቁጥጥር ሽምምቅ እላለሁ። ምክንያቱም ለውጥ አይቀሬ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ይህን ተፈጥሯዊ ሕግ ለመሻር የሚጥር ሁሉ መጨረሻ ላይ ወድቆ ሲያጣጥር ታገኘዋለህ። ታዲያ የኢህአዴግ አመራሮች “ሕገ መንግስቱ አይሻሻልም” የሚል ነገር በተናገሩ ቁጥር እኔ ለእነሱ አዝናለሁ።

ለምሳሌ የአሜሪካ ሕገ መንግስት የፀደቀው እ.አ.አ. በ1789 ዓ.ም ሲሆን ሥራ ላይ ከዋለ 228 ዓመታት ሆኖታል። በእነዚህ አመታት ውስጥ ግን አስራ አንድ ሺህ (11000) የማሻሻያ ሃሳቦች ቀርበዋል። በመሆኑም ሕገ መንግስቱ ስራ ላይ ከዋለ ግዜ ጀምሮ በየአንዳንዱ አመት በአማካይ አርባ ስምንት (48) የማሻሻያ ሃሳቦች ቀርበዋል ማለት ነው። ከ11ሺህ የማሻሻያ ሃሳቦች ውስጥ ተቀባይነት አግኝተው ሕገ መንግስቱ የተሻሻለው ግን ሃያ ሰባት (27) ግዜ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ፣ የአሜሪካ ሕገ መንግስት በአማካይ በየስምንት (8) አመቱ አንድ ግዜ ተሻሽሏል ማለት ነው።

በአሜሪካ መስራች አባቶች፣ በእንግሊዝ ፈላስፎች፣ በፈረንሳይ አብዮተኞች እገዛና ድጋፍ የረቀቀው የአሜሪካ ሕገ መንግስት በእያንዳንዱ አመት በአማካይ 48 የማሻሻያ ሃሳቦች ይቀርቡበታል። የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ተግባር ላይ በዋለባቸው ሃያ ሶስት (23) ዓመታት ውስጥ አንድ የማሻሻያ ሃሳብ እንኳን ለውይይት አልቀረበም። የአሜሪካ ሕገ መንግስት ግን በእነዚህ 23 አመታት ውስጥ ከሞላ ጎደል ለሦስት ግዜ ይሻሻል ነበር።

አቶ በረከት ስምዖን እንዳሉት የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት “በጥልቅ ዴሞክራሲያዊ መስረት ላይ የተዋቀረ ነው” ቢባል እንኳን ልክ እንደ አሜሪካን ሕገ መንግስት በጥልቅ ዕውቀትና የፍልስፋና መርህ ላይ የተመሰረተ ነው ለማለት ይከብዳል። ኢህአዴግ በሕገ መንግስቱ የማሻሻያ ሃሳቦች ላይ ለመወያየት ሆነ ለመደራደር ፍቃደኛ አለመሆኑ ምን ያሳያል።

የመጀመሪያው ነገር በሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎችና መርሆች ላይ የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የማሻሻያ ሃሳባቸውን ማቅረብ አለመቻላቸው ነው። ሕገ መንግስቱ በተለየ ሃሳብና አመለካከት ተፈትሾ ትክክለኝነቱን ማረጋገጥ አልተቻለም። በዚህ መልኩ በውይይትና ክርክር ተፈትሾ በሃሳብ ወይም መርህ የበላይነቱን ማረጋገጥ አለመቻል ከሁሉም በፊት የሚጎዳው ሕገ መንግስቱን ነው። ምክንያቱም በየግዜው በተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦች እየተፈተሸ ተቀባይነቱን ማረጋገጥ ካልተቻለ የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎችና መርሆች ትርጉም አልባና ፋይዳ ቢስ ይሆናሉ።

አቶ በረከት ሕገ መንግስቱ “በልካችን የተሰፋ ችግር ፈቺ ሰነድ ነው” ብለው የተናገሩት በ2008 ዓ.ም ሲሆን ሕገ መንግስቱ የፀደቀው ደግሞ በ1987 ዓ.ም ነው። በሁለቱ ክስተቶች መሃል 21 ዓመታት አሉ። በእነዚህ አመታት ውስጥ በኢትዮጲያና በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም ብዙ ለውጦች ታይተዋል።

ለምሳሌ፣ ሕገ መንግስቱ በፀደቀበት አመት በኢትዮጲያ ሞባይል ስልክ እና ኢንተርኔት የለም ነበር። አቶ በረከት ከላይ የተጠቀሰውን ዓ.ነገር በተናገሩበት ዓመት ግን 43 ሚሊዮን የሞባይል ስልክ፣ 11.5 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ ከአስር አመት በፊት እንኳን ኢትዮጲያ ውስጥ 10 ሚሊዮን ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን ዛሬ ላይ ከ21 ሚሊዮን ናቸው።

በተለይ በትምህርትና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ረገድ የታዩት ለውጦች አዲሱን ትውልድ በሀገራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው አስችለውታል። በ1987 ዓ.ም በሀገር ውስጥ እና በውጪው ዓለም፣ እንዲሁም በገጠርና ከተማ መካከል የነበረው ድንበር ሙሉ በሙሉ ተሰብሯል ማለት ይቻላል።

በመሆኑም፣ የሀገር ውስጥ ዜጋ በውጪው ዓለም ስላለው ኑሮና አኗኗር ዘይቤ ያውቃል። በገጠር ያለው የአርሶ አድር ልጅ በአቅራቢያው አልፎ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ያለውን የቅንጦት ሕይወት ያውቃል። በዚህም ከራሱ ጋር ያለውን ልዩነት ይፈትሻል። በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ግድፈቶችን የማወቅ እድል ይፈጠርለታል። ይህ በአስተዳደርና ሃብት ክፍፍል ረገድ ያለውን ኢፍትሃዊነት በግልፅ እንዲረዳ ያስችለዋል። በመሆኑም የተሻለ ነፃነትና አገልግሎት ይጠይቃል። የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ይዞ ለተቃውሞ አደባባይ ይወጣል።

ለዚህ ትውልድ “ሕገ-መንግስቱ በልካችን የተሰፋ ችግር ፈቺ ሰነድ ነው” ማለት በአንድ (1) አመት ሕፃን ልክ የተሰፋን ልብስ ለ23 ወጣት “ልኩ ይሆናል” ብሎ እንደመከራከር ነው። የአሜሪካ ሕገ መንግስት 11ሺህ ግዜ የማሻሻያ ሃሳብ እንደቀረበበት ለሚያውቅ ወጣት “ሕገ መንግስቱ አይሻሻልም” ማለት ራስን ከመስደብ የዘለለ ትርጉም የለውም። ይህ ትውልድ ለጥያቄው  ምላሽ መስጠት የተሳነውን ሕገ-መንግስት በመጨረሻ ቀድዶ ይጥለዋል፡፡

Filed in: Amharic