>
4:53 pm - Wednesday May 25, 1853

የመገንጠል ሥነ ሥርዓት በኢትዮጵያ፤ ከሰላም ይልቅ ግጭት አስከታይነታቸው፤ (በውብሸት ሙላት)

(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ላይ የሚገነጠለው ብሔር/ብሔረሰብ ምክር ቤት ውሳኔ እና የማሰላሰያ ጊዜን በተመለከተ እንከኖቹን በተለይም መገንጠልን ሥራ ላይ ማዋል ቢፈለግ በሰላም መለያየትን እንደማያስችሉ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ለመገንጠል የሚፈልግ ብሔር ሕዝበ ውሳኔ በማከናወን በአብላጫ መወሰን ስለሚያስፈልግ በምንም መንገድ በሰላም ለመለያየት በሚጠቅም መንገድ አለመቀመጡን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

ለሕዝበ ውሳኔ የሚቀርቡ አማራጮች፤

የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ላይ ተጽእኖ የሚያሳርፉ ሁኔታዎችም ብዙ ናቸው፡፡ የጥያቄው ዓይነት ለምሳሌ ኤርትራ እንዳደረገችው “ነጻነት” ወይስ “ባርነት” ሊሆን ይችላል፡፡ መቼም ማንም ጤነኛ ሰው “ባርነትን” ሊመርጥ አይችልም፡፡ ከዚህ አንጻር የሴንት ኪትስና ኔቪስ ጥሩ ተሞክሮ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡

አማራጮቹ ለምን እንደተመረጡ የሚያሳይ ማብራሪያ ጭምር ውሳኔ ከመሰጠቱ ቢያንስ ዘጠና ቀናት ቀደም ብሎ ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግን ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ አድርገውታል፡፡እንደ ኤርትራው ኃላፊነት የጎደለው አድራጎት ላለመፈጸም ነው፡፡

በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ የመገንጠል ኢፍትሐዊነት፤

በኢትዮጵያ፣ የፌደራሉ መንግሥት ሕዝበ-ውሳኔ አዘጋጅቶ ድምፅ ከሰጡት ውስጥ፣ ከግማሹ በአንድ ሰው ከፍ ያለ፣ ለመገንጠል ይሁንታውን ከሰጠ፣ ብሔሩ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ጋብቻ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ የሩሲያው ሁለት ጊዜ በሚከናወኑት ሕዝበ-ውሳኔዎች በእያንዳንዳቸው ሕዝቡ ቢያንስ 2/3ኛው የድጋፍ ድምፅ ካልለገሰ በስተቀር መገንጠል አይቻልም፡፡ በኔቪስም 2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ ማግኘት ግድ ነው፡፡

በዚሁ መሠረት፣ በ1998 (እ.ኤ.አ.) በኔቪስ የነበሩት የገዥው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚዎች መገንጠልን በመደገፍ በምክር ቤቱ በ2/3ኛ ድምፅ አሳልፈውት ኋላ ለሕዝቡ ሲቀርብ 61.7% ብቻ ድጋፍ በማግኘቱና ሁለት ሦስተኛ ስላልሞላ የኔቪስ ሕዝብ ሳይገነጠል ቀርቷል፡፡ ከዚህ አንጻር አንቀጽ 39(4) የማሰላሰያ ጊዜ ካለመኖሩ በተጨማሪ እንደ ተራ ጉዳይ መለኪያውን ተራ የአብላጫ ድምፅ ሆኗል፡፡ በተራ አብላጫ ድምፅ እንዲህ አቅልሎ ማስቀመጥ ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉት፡፡

ችግር ቁጥር አንድ፣ መገንጠሉን የሚወስኑት ከጠቅላላው የብሔሩ አባላት አናሳው ሊሆኑ መቻላቸው ነው፡፡ የብዙኃኑን ዕድል አናሳዎች እንዳሻቸው ሊያሽከረክሩት ይችላሉ፡፡ ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት ለአካለ መጠን ያልደረሱ፣ የአእምሮ ሕሙማን፣ በሕግ እንዳይመርጡ የተከለከሉ ሕዝቦች በሕዝበ-ውሳኔው ተሳታፊ ስለማይሆኑ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በትንሹ የብሔሩን 20% እንኳን ይሸፍናሉ ቢባል፣ ድምፅ የሚሰጠው ቀሪው 80% ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ በተራ አብላጫ ድምፅ ውሳኔው ሲሰጥ የሰማኒያው ግማሽ 40% ስለሚሆን ዞሮ ዞሮ 40%ን ከዘለለ መገንጠሉ እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ መምረጥ የማይፈልገው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ድምፅ መስጠት ያልቻለው ሲደማመርበት እየተመናመነ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡

በኔቪስ ሕዝበ-ውሳኔ ጊዜ ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቦ ከነበረው ውስጥ መጨረሻ ላይ ድምፅ የሰጠው 58% ብቻ ነበር፡፡ ተራ አብላጫ ቢሆን ኖሮ ኔቪስ ተገንጥላ ነበር፡፡ በካናዳም፣ ኪውቤክ ልገንጠል ብላ ሕዝበ-ውሳኔ ብታደርግም ውሎ አድሮ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዴሞክራሲ ማለት ተራ አብላጫ ድምፅ ማለት ብቻ እንዳልሆነና ለካናዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሄንን የሚያብራራ ሕግ እንዲወጣ አስተያየት ስለሰጠ ኪውቤክ ለመገንጠል ከፈለገች አንዱ ቅድመ-ሁኔታ በሕዝበ-ውሳኔ ወቅት መገንጠሉ በ2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ መታጀብ እንዳለበት ሕግ አውጥቷል፡፡ ይህ እንግዲህ የብዙኃኑን ዕድል በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ሕዝብ ቢደገፍ መልካም መሆኑን ስላመኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ችግር ቁጥር ሁለት፣ አንገነጠልም ባዮች ቢያሸንፉ በሌላ ጊዜ ለመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔ ሊኖር ሲችል እንገነጠላለን ባዮች ካሸነፉ ግን ድጋሜ ለመወሰን የሚኖር ዕድል የለም፡፡ ስለሆነም እዚህ ግባ በማይባል ቁጥር ተበልጠው መገንጠልን የተቃወሙ ሰዎች “ብዙሃን ይመውኡ” የሚለው የዴሞክራሲ መርሕ ወደ ከፋ አፋኝነትና ጨፍላቂነት ስለሚቀየር ቢያንስ ድጋሜ አቋማቸውን አጢነው እንዲወስኑ ዕድል ስለማይሰጥ ተራ አብላጫ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፡፡

ማን ነው ድምጽ ሰጩ?

ለመገንጠል የሚደረግ ሕዝበ-ውሳኔን በተመለከተ አራት ነጥቦችን እናንሳ፡፡ የመጀመሪያው ድምፅ-መስጠት የሚችሉት መገንጠል የሚፈልግው ብሔር ባለበት ክልል ውስጥ የሚኖሩት የብሔሩ አባላት ብቻ ና ቸው ወይንስ በሌላ ክልልምና አገራትም ጭምር የሚኖሩትን ያካትታል? የሚለው ነው፡፡ በምርጫ ሕጉ የሚገዛ ከሆነ በአካባቢው ኗሪ መሆንን ይጠይቃል፡፡

የሌሎች ብሔረሰቦች ሚና/ዕጣ ምንድን ነው?

ሁለተኛው መገንጠሉን በሚፈልገው ብሔር ክልል ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሚናቸው ምንድን ነው? ለምሳሌ የአማራ ብሔር አሁን ያለውን ክልል ይዞ መገንጠል ቢፈልግ የአማራ ሕዝብ ምክር ቤት የሚባለው የክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ፣የአዊ፣ የኻምራ፣የአርጎባና የኦሮሞ ሕዝብን ያቀፈ ምክር ቤት እንጂ የአማራ ሕዝብ ስላልሆነ እንዴት ሊወስን እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡ የእነዚህ ብሔረሰቦች ተወካዮች ከተነሱ ምክር ቤቱ ጎደሎ ነው የሚሆነው፡፡

ድምፅ የሚሰጡ ከሆነ በሌሎች መብት ውሳኔ ሰጭ እየሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር በአማራ፣ በትግራይና ሐረር በዋናነት የሚያጋጥም ሲሆን ኦሮሚያ፣አፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌም የብሔሩ አባላት ያልሆኑ የምክር ቤት አባላት ካሉ ድምፅ መስጠት ይችላሉ ወይንም አይችሉም የሚለው ጥያቄ አስቸጋሪ ነው፡፡ ድምፅ የማይሰጡ ከሆነም ሌላ ችግር መውለዱ አልቀረም፡፡

ለአብነት፣ የአማራ ሕዝብ መገንጠል ቢፈልግ በክልሉ ውስጥ የሚገኙት ብሔረሰቦች የአማራ ሕዝብ ውሳኔ ሲሰጥ ‘ቁልጭ፣ቁልጭ’ እያሉ ውሳኔውን ከመጠበቅ ውጭ አማራጭም ተሳትፎም አይኖራቸውም፡፡ምንም እንኳን የአማራ መገንጠል ወይንም አለመገንጠል ውጤት እነሱንም ጭምር የሚመለከትና ተጽዕኖ ያለው ቢሆንም ውሳኔው ውስጥ ተሳታፊ መሆን አይችሉም፡፡

ከመገንጠሉ በኋላ የሌሎች ዜጎች ዕጣ ፋንታ፤

ሦስተኛው፣ መገንጠሉን በሚፈልገው ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኗሪዎች ድምፅ የመስጠት ጉዳይና መገንጠሉ ከተፈጸመ በኋላ ስለሚኖራቸው እጣ ፋንታ የሚመለከት ነው፡፡ በሩሲያ ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 72 በዋናነት ነጻ አገር የመመሥረት ወይም የመገንጠል መብት የታወቀላቸውም ለሪፐብሊኮቹ እንጂ ለብሔሮች አይደለም፡፡ድምፅ የሚሰጡት በሪፐብሊኩ በቋሚነት የሚኖሩት ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግን የመገንጠልን ጥያቄ ያቀረበው ብሔር አባላት እንጂ ሌሎቹን የክልሉን ኗሪዎች አይመለከትም፡፡

ከላይ የተነሱት ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ጭብጥ በተመለከተ የካናዳና የኪውቤክን ልምድ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ኪውቤክ ልገንጠል ብላ ሕዝበ-ውሳኔ አከናውና ለትንሽ ከግማሽ ከፍ ያለው ሕዝብ መገንጠልን ቢቃወምም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም ሲሰጥ በካናዳም ይሁን በዓለማቀፍ ሕግ የተናጠል መገንጠል የሚባል መብት ስለሌለ ኪውቤክ ባሰኛት ጊዜ በተናጠል መገንጠል አትችልም፤ከሌሎቹ ክልሎችና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መደራደር አለባት በማለቱ ይህንኑ የሚያጠናክር ሕግ አውጥታለች፡፡

የተናጠል መገንጠል እንደማይቻልም አስረግጣ ደንግጋለች፡፡ በኢትዮጵያም፣ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተናጠል መገንጠል እንዲችሉ ሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም ቢያንስ የሚገነጠለው ብሔር በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚደራደሩበት ዕድል መመቻቸት አለበት፡፡

ሦስተኛውን ጭብጥ በተመለከተ ካናዳ እንደፌደራል መንግሥትነቷ ሕግ ስታወጣና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ኪውቤክም ተጨማሪ ሕጎችን ማውጣት እንዳለባት አስተያየት ሰጥቶ ስለነበር እሷም በበኩሏ ብትገነጠል የእንግሊዝኛ ተናጋሪና ነባር ብሔሮችን መብት እንደምታከብር የሚገልጽ ሕግ ወዲያውኑ አውጥታለች፡፡

ሕዝበ ውሳኔውን ማነው የሚያስፈጽመው?

የመጨረሻው ሕዝበ-ውሳኔውን ከሚያስፈጽመው አካል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ሕዝበ-ውሳኔ የሚያደራጀው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይህንና ሌሎች ምርጫዎችን ለማስፈጸም ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ይሄው ተቋም ነው ሕዝበ-ውሳኔውንም ሊያስፈጽም የሚችለው፡፡ ይህ ተቋም የቀሪዋ ኢትዮጵያ ተቋም ነው፡፡የመራጮች ምዝገባ የሚያከናውነው፣ ታዛቢዎችን የሚያስመርጠው፣ ቅሬታም ቢኖር የሚመረምረው ይሄው ተቋም ነው፡፡

ለመገንጠል የሚፈልገው ብሔር በፍትሐዊነት ወይንም በእኩልነት የሚወከልበት ወይንም በራሱ የሚያስፈጽምበት ሕገመንግሥታዊ መዋቅርም አካሔድም የለም፡፡በሴንት ኪትስና ኔቪስ፣ ኔቪስ ለመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔ ስታከናውን አስመራጮቹ ከላይ እንደተገለጸው በራሷ በኔቪስ ገዥ የሚሰየሙ እንጂ በፌደራል መንግሥቱ የሚቋቋም አስመራጭ አይደለም፡፡

ምርጫ ቦርድ ያው ነጻና ገለልተኛ ተቋም ነው ሊባል ቢችልም የቄሳርን ድምፅ የሕዝብ ድምፅ ከማድረግ ላይቦዝን ይችላል፡፡ እንዲህ ሲሆን ያው ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፡፡

Filed in: Amharic