>

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ ደህንነት ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ አንድ ጄኔራል ስርአቱን ከድተው በአሜሪካ ጥገኝነት ጠየቁ።

(ኢሳት ዜና–መስከረም 26/2010) በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ ደህንነት ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ አንድ ጄኔራል ስርአቱን ከድተው በአሜሪካ ጥገኝነት ጠየቁ። የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ስርአቱን ከድተው በአሜሪካ የቀሩት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ጥሩነህ የተባሉ ከፍተኛ መኮንን ናቸው። ከወር በፊት በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ አዘጋጅነት በዋሽንግተን በተካሄደ ጸረ አይ ሲስ አለም አቀፍ ዘመቻ ላይ ከተገኙ የኢትዮጵያ ልኡካን አንዱ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ጥሩነህ በዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራው ልኡካን ቡድን ወደ ሀገር ቤት ሲመለስ እርሳቸው ከቡድኑ ተለይተው ቀርተዋል። ግሎባል ኮአሊሽን ቱ ዲፊት አይሲስ በተባለውና 72 ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ጥምረት ጉባኤ ላይ ለመገኘት መጥተው ከልኡካኑ ተለይተው የቀሩት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸውንም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ በወታደራዊ ደህንነት መመሪያ ውስጥ ይሰሩ እንደነበር የተገለጸው ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ነባር የብአዴን ታጋይ ነበሩ። በመስከረም 2009 የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ ካገኙት መኮንኖች አንዱ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ስርአቱን ከድተው መቅረታቸውን ኢሳት አረጋግጧል። ጄኔራሉ የብአዴን አባል ሆነው ስርአቱን መቀላቀላቸው ታውቋል። በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛው የአዛዥነት ስፍራ ከ90 በመቶ በላይ በትግራይ ተወላጆች መያዙ ሲገለጽ ቆይቷል። በዚህ ሰራዊት በተወሰነ ቁጥር ከነበሩት የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆች ባለፉት 10 አመታት ከ20 በላይ የኦሮሞና የአማራ ጄኔራሎች ታስረዋል፣ተባረዋል፣ያለዕድሜያቸው በጡረታ የተሸኙ መኖራቸውም ታውቋል። ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ፣ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ ስርአቱን ከድተው ከወጡት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። ሜጄር ጄኔራል አለምሸት ደግፌ፣ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ብርጋዴር ጄኔራል ኩመራ አስፋው ማዕረጋቸውን ተገፈው ከስርአቱ ተባረዋል። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተፈርዶባቸው በወህኒ ይገኛሉ። ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በ2001 ከሰራዊቱ አመራርነት ተይዘው የታሰሩና በግልበጣ ሙከራ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ናቸው። ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌና ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ ደግሞ ከሰራዊቱ በጡረታ ተሸኝተዋል። ቀደም ሲል በጡረታ ከተሸኙት አንዱ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሌ መለስ ከአመት በፊት ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ታውቋል። ለተባበሩት መንግስታት 72ኛ ጉባኤ ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ወደ ኒዮርክ አቅንተው የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮቶኮል ሃላፊ አቶ ባዬ ታደሰ ስርአቱን በመክዳት አሜሪካ መቅረታቸውን በሳምንቱ መጀመሪያ ለቪኦኤ መግለጻቸው ይታወሳል። የፕሮቶኮል ሃላፊው በአቶ ሃይለማርያም ከተመራው የኢትዮጵያ ልኡካን ጋር አሜሪካን የገቡት በተያዘው ወር እንደሆነም ታውቋል።

Filed in: Amharic