>

ህውሃት የግመል ወተት እያጠጣች ያሳደገችው ዘንዶ በመጨረሻ ራሷን መዋጡ አይቀርም (ቬሮኒካ መላኩ)

በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት “ህገ መንግስቱ የተፃፈበትን ቀለም ዋጋ ያክል እንኳን የሌለው ተራ ወረቀት መሆኑን እየተመለከትን ነው። መአከላዊ መንግስትም እንደማሽላ ቂጣ ገና ሳይነኩት እየተቆራረሰ ነው።
አብዲ ኢሌ ” ኦሮሚያ ምላሱንና እና እጁን ካልሰበሰበ ጦርነት አውጃለሁ !” ማለቱ አስገርሞኛል።
በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ጦርነት የማወጅ ስልጣንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን የለውም። ይሄ ስልጣን የተሰጠው የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል ለሆነው ለፌደራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ እየታወቀ አንድ የክልል ፕሬዚደንት በድፍረት መናገሩ አገሪቱ በ 17ኛው ክፍለ ዘመን በባሰ ሁኔታ በዘመነ መሳፍንት ውስጥ እንዳለች ያመለክታል።

በ 1769 ዘመነ መሳፍንት ሲጀምር የየግዛቱ አስተዳዳሪዎች “ንንበር በበሲመታቲነ ወበበአህጉራቲነ ፣ ወኢይቅንየን መኑሂ በከዊነ ንጉስ! ”
(በሹመት አገራችን እንቆይ ፣ ማንም ንጉስ በመሆን አይግዛን ) በማለት ለመአከላዊ መንግስት እንደማይታዘዙ ተስማምተው መአከላዊ መንግስት አሻንጉሊት እንደሆነና የየክልሉ ገዥዎች አፄ ቴዎድሮስ እስኪነሳ ድረስ ለመቶ አመታት ያክል ሲፈጣፈጡ ኖሩ ። አገሪቱም በጦርነት ዶግ አመድ ሆነች ።

አሁንም ከ300 አመታት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ እነ ሱማሌ ክልል ቀድመው ዘመነ መሳፍንትን ያወጁ ይመስላሉ። ሌሎቹም ይሄን መንገድ መከተላቸው አይቀርም።

አብዲ ኢሌ የህውሃት የበኩር ልጅ ነው ። ብዙ ኢንቨስት ካደረገችበት በኋላ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር የፊት አጥቂና ጎል ጨራሽ ተጫዋች እየሆነላት ነው ። እርግጥ ህውሃት የግመል ወተት እያጠጣች ያሳደገችው ዘንዶ በመጨረሻ ራሷን መዋጡ አይቀርም።

አብዲ ኢሌ ፀባዩ ሁሉ እንደ ኢዲ አሚን ዳዳ ነው። የኡጋንዳው ኢዲ አሚን አስገራሚና ቅጥ አምባሩ የጠፋ ባህርይ ተዘርዝሮ አያልቅም ነበር ፡፡ የአንድ ታዋቂና ሃብታም እስያዊ ቤተሰብ ልጅ የሆነች ኮረዳን ለትዳር ጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ ያላገኘው አሚን፤ የአፀፋ እርምጃቸው አስደንጋጭ ነበር፡፡ በኡጋንዳ የሚኖሩ እስያዊያንን በሙሉ ከአገሪቱ አባረረ ።
የሱማሌው አብዲ ኢሌም ጃዋር መሀመድ እና አዲሱ አረጋ ቂጢሳ ስለ ሱማሌ አንድ ፅሁፍ ፖስት ባደረጉ ቁጥር 1000 ኦሮሞዎችን ከሱማሌ ክልል ያባርራል። አብዲ ኢሌ አንድ የኦሮሞ አክቲቪስት የሚለጥፋትን የፌስቡክ ፖስት በ 1000 ኦሮሞ ይመነዝራል። ይሄ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱ ወደ አጠቃላይ አስከፊ ቀውስ መግባቷ አይቀርም።

እስኪ ይሄን አሳዛኝ እውነታ በቀልድ አዘል መፍትሄ እንደምድመው ።መፍትሄው ምንድነው? መንግስቱ ሀይለማሪያም እንዳለው” ወንበሯ አንድ ሰው ነው የሚቀመጥባት ፈላጊዋ ግን ብዙ ነው ” አለ እንጅ ሀይለማሪያም የተባለ ዘለፈቶ ካለምንም ስራ ተዘርፍጦበት የሚውለውን ወንበር ቢሰጡኝ በ100 ቀን ውስጥ አንድ ታሪካዊ አገር እንደት እንደሚተዳደር አሳየው ነበር ።

Filed in: Amharic