>
5:13 pm - Friday April 19, 8480

አዘቅት ሲያሰምጥ እያሳሳቀ - ዘረኝነት ሲያፋጅ እያስታረቀ (ዮሃንስ )


ነገሮች እንደ ድሮ አይደሉም!

ብዙ ጨዋ ሰዎች፣ የአገሪቱን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ ሲበርድ፣ እያሰለሰ ‘ብቅ ጥልቅ’ ሲል፣ አልፎ አልፎ ‘እየረገበ ሲያገረሽ’ እያዩ፣… ተመሳሳይ ጥፋትና እርጋታ፣ ጭንቀትና እፎይታ እየተፈራረቀ ወደፊትም የሚቀጥል ይመስላቸው ነበር። ዛሬስ ይመስላቸዋል? እንግዲህ፣…
‘ብሔር ብሔረሰብ’፣ ‘ቋንቋ’፣ ‘ባህል’… ምናምን እየተባለ፣ ነጋ ጠባ የሚፈለፈለው ማመካኛ ሰበብና የሚፈፀመው ዘግናኝ ጥፋት እንዳልተቋረጠ ተመልክተዋል። በመዘዙ የሚጠፋው ሕይወትና የሚደርሰው አሳዛኝ ጉዳት እንዳልቀነሰም አይተዋል።… ሁነኛ መፍትሄ እንዳልተገኘና፣ መፍትሄ የማግኘት ፍንጭና የተስፋ ብልጭታ እስካሁን እንደሌለም ያውቃሉ።
እንዲህም ሆኖ፣…. የአገራችን ብዙ ጨዋ ሰዎች፣… “ቢያንስ ቢያንስ፣ እንደ ወትሮው ይቀጥል እንደሆነ እንጂ አይባባስም” እያሉ ራሳቸውን ያታልሉ ነበር። “የአገራችን ሁኔታ፣… መፈናፈኛ ወደሌለው ስቃይ፣ ማብቂያ ወደሌለው የከፋ እልቂት፣ መውጫ ወደሌለው የባሰ ትርምስ፣ ማብረጃ ወደሌለው ፍጅት አያመራም” በሚል ስሜት ራሳቸውን ያፅናኑ ነበር።
ዛሬስ? የአገሪቱ ሁኔታ፣ በግልፅ እየተበላሸ፣ አስፈሪነቱ ጎልቶ እየታየ ሲመጣ፣ ራስን እያታለሉ በውሸት መፅናናት ይቻላል? ያዋጣል? ያዛልቃል?
እንደማያዋጣ ገብቷቸው፣ የሚያዛልቅ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ወደመገንዘብ የሚያመሩ ሰዎች ቢኖሩም፤ አብዛኞቹ ጨዋ ሰዎች ግን፣… አሁንም፣ ወደፊትም… ራሳቸውን እያታለሉ ለመፅናናት መሞከራቸው አይቀርም። መሞከር ብቻ ሳይሆን፣ “ይታገላሉ”… “ይታትራሉ” – ራሳቸውን ለማታለል። ለምን? ምን ሊረባቸው?
እስከ ዛሬ የተደመጡ ዲስኩሮች፣ እስከ ዛሬ የተካሄዱ “የጅምላ እርቆች”፣ እስከ ዛሬ የተሰራጩ “የሕዝቦች ወንድማማችነት ስብከቶች” እና “የብሔር ብሔረሰቦች ወዳጅነት መግለጫዎች”… ሁነኛ መፍትሄ ሊሆኑ ይቅርና፣ አስፈሪውን ችግር ሊያስወግዱ ይቅርና፣… እንዲያው ለምልክት ያህል እንኳ ቅንጣት የረባ ውጤት እንዳላስገኙ በተደጋጋሚ አይተዋል፤… በተቃራኒው በዘር የሚቧደኑ ሰዎች የሚጭሩት እሳት እየተባባሰ የዘወትር ቀውስና መደበኛ አደጋ እየሆነ መምጣቱንም አይተዋል።
ቢሆንም… ቢያዩም፣… ብዙ ጨዋ ሰዎች፣ የሚያዩትን እውነታው በቅጡ ከመገንዘብ ይሸሻሉ፤ ወይም ለመገንዘብ ይፈራሉ። “ምንድነው ችግሩ?” ብለው አብጠርጥረው ከማሰብ ይቆጠባሉ። የእስከዛሬዎቹ “መፍትሄዎች”፣ ውጤት አልባ የሆኑት፣ ‘የፍቅር ስብከቶች’ እንደ ብናኝ ያለ አሻራ ተንነው የሚጠፉት ለምንድነው? ለምንድነው አደገኛው ችግር እየተባባሰ የመጣው?… ብለው አይጠይቁም።
“መፍትሄ” ተብለው የተካሄዱት ስብሰባዎችስ? በዘር ጎራ መለየትንና መቧደንን የሚያበረታታ “የጅምላ እርቅ” መደገስስ? “የመንጋ ፍቅርን በጭፍን መደስኮርስ?”… እነዚህስ፣ የዘረኝነት ዘግናኝ አደጋን እያባባሱ አይደሉምን?

በዘር የተቧደነ ብሽሽቅ እና በዘር የተቧደነ እርቅ
አዎ! “የብሔር ብሔረሰብ እርቅ” ስንል፣… ሰላምን እየተመኘን ጠቃሚ ነገር የሰራን ሊመስለን ይችላል። ለዛሬ? አዎ ይመስላል። ግን የዛሬዋ ዲስኩር ላይ ብቻ መስመጥና፣ የቅፅበት የቅፅበቱን ብቻ ማየት፣… አላዋቂነት ነው። አላዋቂነትን የሙጢኝ ይዞ መቀጠል ደግሞ፣ የጭፍንነት በሽታ ይሆናል።
ዛሬ፣ “የሕዝቦች እርቅ” ስንልኮ፣… የግድ ሰዎችን በብሔረሰብ፣ በቋንቋ፣ በዘር ለማቧደን ስንለፋ እናድራለን ማለት ነው። ግን፣ “ነገስ?” ብለን አናገናዝብም። በዘር ያቧደንነውን የቅዠት መድረክ፣ የቀረፅነውን ጠማማ የአስተሳሰብ ቅኝት፣… እንዲያ አሰናድተንና አመቻችተን ስንጨርስ፣ በማግስቱ ማን እንደሚረከበን ማወቅ ነበረብን። በዘር የመቧደን ቅስቀሳና ዘረኛ የአስተሳሰብ ቅኝት፣… ከሁሉም በላይ ክፉ ሰዎችን ያስጎመጃል። ሌላ ምን ምን ይፈልጋሉ? በዘረኛ አስተሳሰብ፣ በዘር ማቧደንና የጅምላ እልቂት መደገስ ነው የሁልጊዜ ምኞታቸው። ተመቻቸው! በእልቂት ጎዳና ግማሽ መንገድ ድረስ በራሳችን ፈቃድ ተጉዘን ጠበቅናቸው። ግማሹን ስራ ሰርተን አስረከብናቸው።
በዘር የሚያቧድን “የሕዝቦች ፍቅርን” በጭፍን ስሜት ስንሰብክስ? ያው፤ የመንጋ ጭፍን ጥላቻን ለሚሰብክ እኩይ ሰው፣ መንገድ ጠረግንለት ማለት ነው – እንደ እንስሳ፣ በዘር መቧደንን እየለመድንለት ነው።
በእርግጥ፣… “በዘር የተቧደነ ብሽሽቅ” እና “በዘር የተቧደነ እርቅ”… የጥፋት ጎዳናዎች ቢሆኑም፣ የአጥፊነት መጠናቸው ይለያያል። አንደኛ ጥፋት፣ ከወደር የለሽ ክፋት የሚመነጭ፤ ሌላኛው ደግሞ ከአላዋቂነትና ከስንፍና የሚጀምር ጥፋት ነው። ቢሆንም ግን፣… የአስተሳሰብ መሰረታቸው ተመሳሳይ ነው። በመሰረታዊ የአስተሳሰብ ስህተታቸው ላይ፣ ልዩነት የላቸውም።
በአንድ በኩል፣ “በዘር እየተቧደነ ጭፍን የመንጋ እሪታንና ጥላቻን የሚቀሰቅሱና የሚያራግቡ ክፉ ሰዎች”፣ ዘግናኝ እልቂትን ይደግሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “በዘር እየተቧደነ ጭፍን የመንጋ እልልታንና እርቅን የሚደሰኩሩ አላዋቂዎች”፣ የዘረኝነትን መድረክ ያሰናዳሉ።
አንዱ፣ በዘር እየተቧደነ፣ “ዘመቱብን፣ ዘመትንባቸው” እያለ ጭፍን ስሜትን ያቀጣጥላል። ሌላኛው ደግሞ፣ በዘር እየተቧደነ፣ “በታሪክ የተሳሰሩ፣ በቋንቋ የተዛመዱ ሕዝቦች” እያለ ጭፍን ስሜትን ይቀሰቅሳል። የሁለቱ ሰዎች የጥፋት አይነትና ደረጃ አይለያይም እያልኩ አይደለም። መሰረታዊ የአስተሳሰብ ልዩነታቸው ግን፣… በዘረኛ የአስተሳሰብ ቅኝት፣ ወደ እንጦሮጦስ የመንደርደርና የመንሸራተት ልዩነት ነው። ከተሳሳተ የአስተሳሰብ ቅኝት፣ ወደ ጥፋት ድግስ ስንሻገር ነው፤ ሰፊ ልዩነት የምናገኘው።

ብዙ መሆን ሳያስፈልጋቸው ብዙ ማተራመስና ማጥፋት!
በብሔር ብሔረሰብ ተቧድነው፣ እንደ አውሬ ለመገዳደል የሚመኙ፣ ሌላውንም ሰው ለመፍጀት የሚቋምቱና እልቂትን የሚቆሰቁሱ መርዘኞች፤… የሰው ሕይወት ሲቀጠፍ፣ አካል ሲገነጣጠል፣ ንብረት ሲጠፋ የማየት ክፉ ሱስ የለመዱ እኩይ ሰዎች፣ በጥፋት ደረጃ ሲመዘኑ፣ ከሌሎች ሁሉ የባሱ ናቸው። በቁጥር ግን ጥቂት ናቸው። ችግሩ ምንድነው? ቁጥራቸው እንጂ ጥፋታቸው ጥቂት አይደለም።
የሰውን ስቃይ ለማየት የሚመኙና አስቀያሚ የክፋት ሱስ የተጠናወታቸው መርዘኞች ጥቂት ቢሆኑም፣… የሚያስቆማቸው ሰው ከሌለ፣ ሚሊዮኖችን ለእልቂት፣ ለስቃይና ለስደት ይዳርጋሉ። በለየለት የአምባገነንነት ጭካኔ ስር የተጨፈለቁ አገራትን ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ያኔዎቹ ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ ሁሉ፣… ዛሬ በትርምስ የፈራረሱና እየፈራረሱ የሚገኙ እንደ ሶማሊያና የመን፣ ሶሪያና ሊቢያ የመሳሰሉ አገራትን መመልከት ትችላላችሁ።
በእርግጥም፣ በየትም አገር ስንመለከት፣ አተራማሾቹና አውሬዎቹ ጥቂት ናቸው። ነገር ግን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዝምተኛ ጨዋ ሰዎች፣… የግድያና የስቃይ ሰለባ ይሆናሉ። ክፉዎቹ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ነገር ግን፣ በርካታ ሚሊዮን ጨዋ ሰዎች፤ ቤት ንብረታቸውን አጥተው ይፈናቀላሉ፣ ይሰደዳሉ። በአገራችንም፣ ባለፉት ጥቂት አመታት፣ በሰበብ አስባቡ የተከሰቱ ጥፋቶችንና ብጥብጦችን ማየት ይቻላል። ጥፋት የሚፈፅሙ ጥቂት ክፉ ሰዎችን እና የጉዳት ሰለባ የሚሆኑ ብዙ ጨዋ ሰዎችን ነው የምናገኘው።
ስልጣን የያዙም ሆኑ ያልያዙ፣ በብሔር ብሔረሰብም ሆነ በቋንቋ፣ በሐይማኖትም ሆነ በባሕላዊ እምነት ሰበብ ተቧድነው ጥፋት የሚፈፅሙ ሰዎች፣… አንዳንዴ “በርካታ” ሊመስሉን ቢችሉም፣ ከየአካባቢው የነዋሪ ብዛት ጋር ሲነፃፀሩ ግን፣ በጣም ጥቂት ናቸው። ነገር ግን፣ ብዙ መሆን አያስፈልጋቸውም – ብዙ ጥፋት ለማድረስ። ‘ጥቂት’ ቢሆኑም፣ የበርካቶችን ሕይወት ማጥፋትና አካል ማጉደል፣ ንብረት ማውደምና ማፈናቀል፣… አገር ምድሩን ማተራመስ አያቅታቸውም – የሚያስቆማቸው ሰው ካልተገኘ።
ለዚህስ ተጠያቂው ማን ነው? እነዚህን ጭፍን፣ ከንቱና መናኛ ክፉ አውሬዎችን ማስቆም ተሳነን?! ይሄስ የማን ጥፋት ነው?
አዎ! በአምባገነንነት ወይም በትርምስ ውስጥ ለሚፈፀመው እልቂትና ውድመት ሁሉ፣ ዋናዎቹ ጥፋተኞችና ተጠያቂዎች፣ በዘር ተቧድነው እልቂትን የሚቀሰቅሱና የሚዘምቱ አውሬዎች ናቸው።
ነገር ግን፣ ሌሎቻችንስ?

ዘረኝነትን መከላከልና ጥፋትን መግታት የማንችል አቅመቢሶች ነን?
በቁጥር የሚወሰን ጉዳይ አይደለም እንጂ፣… ከክፉ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀርኮ፣ የጨዋ ሰዎች ቁጥር እጅግ ይበልጣል።
በብዙ እጥፍ የሚበዙና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ጨዋ የአገሬው ነዋሪዎች፣ የሙያ ሃላፊነትን ማክበር የሚጠበቅባቸው ምሁራንና አዋቂዎች፣ የሕግ ሃላፊነት የተሰጣቸው ባለስልጣናት፣ የመሪነት ቦታ ላይ የተቀመቱ የፓርቲ መሪዎች፣ በአጠቃላይ… እውነትንና እውቀትን የማክበር ቅንነትን መላበስ የሚገባቸው ብዙ ሚሊዮን ሰዎች፣… ለኑሮ ስኬት በፅናት የመትጋት ብርታትን መጎናፀፍ፣ እንዲሁም ለግል ብቃትና ለጠንካራ የእኔነት ሰብዕና አድናቆት የመስጠት ፍትህን መከተል የሚገባቸው፣… በሌላ አነጋገር መልካም ስነምግባርን መያዝ የሚገባቸውና የሚፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፣ እንዴት ዘረኝነትን መከላከልና ጥፋትን ማስቆም ያቅታቸዋል? ይሄስ፣ ጥፋት አይደለምን?
ለእውነትና ለእውቀት ካላቸው ክብር የተነሳ፣ “ማንኛውም መረጃና ማንኛውም ሃሳብ የሚመዘነው፣ “በዘር ወይም በጥንታዊ ባህል ሰበብ ተሰባስቦ በመቧደን”፣ “በብሔር ብሔረሰብ ተወላጅነት ወይም በቋንቋ ሰበብ በመቧደን” አይደለም… ብለው ለምን አይናገሩም?
የመረጃና የሃሳብ መመዘኛ፣ የእውነትና የሐሰት መፈተሻ፣ የትክክልና የስህተት መመርመሪያ፣ የቅዠት ንግግርና የእውቀት ግኝት መለያ፣… ሌላ ሳይሆን፣ … እውኑ ተፈጥሮና ከተጨባጭ ማስረጃ ጋር አመሳክሮ ማረጋገጥ የሚችል አእምሮ ናቸው። – (እውኑን ተፈጥሮ ለማገናዘብ አእምሮን መጠቀም)።
“እውነተኛነትና ትክክለኛነት፣… በዘርና በትውልድ ሃረግ የሚወረስ፣ በሃይማኖት ተከታይነትና በባሕላዊ እምነት የሚታደል አይደለም። በብሔረሰብ አልያም በቋንቋ ተቧድኖ በመጮህ የሚገኝ ነገርም አይደለም” ብለው ለምን አይከራከሩም?
ፕሮፓጋንዳ፣ ውንጀላና አፈና ለማቀጣጠል በመደራጀት፤… አልያም አሉባልታ፣ ስድብና አድማ (‘ቦይኮት’) ለማዥጎድጎድ በመቧደን የሚገኝ ነገር አይደለም – እውነተኛነትና ትክክለኛነት። ይልቅስ፣ በዘር፣ በብሄር በብሄረሰብ፣ በቋንቋ የመቧደን ዘመቻ፣… እውነትንና ትክክለኛ ሃሳብን ለማጥፋት፣ ውሸትንና ስህተትን ለማንገስ የሚካሄድ ዘመቻ ነው – አእምሮን የመጠቀም፣ እውነትን የመናገርና የማሰብ ነፃነትን ለማፈን ያለመ ዘመቻ ነው”… ብለው ጨዋ ሰዎች ለምን አይናገሩም? ያ ሁሉ ምሁር፣ ያ ሁሉ አዋቂ፣ ያ ሁሉ ነዋሪ… እንዴት ዝም ይላል?
ይሄ ጥፋት ነው። የብዙ ሚሊዮን ጨዋ ሰዎች ጥፋት ይሄ ነው። የዘረኝነት መዘዝና አደጋውን እያዩ፣… በቸልተኝነት ወይም በዝምታ ማለፍ፣ ወይም የዘረኝነት መዘዝ ዛሬውኑ ተዘርግፎ ስለማይመጣ ዝምታን መምረጥ! ይሄ አንዱ ጥፋት ነው።
ይህንን ጥፋት ካላረምን፣ ከመጥፋት አንድንም።
ግን፣ ከዚህ የባሰ ጥፋትም አለ። በፍቃደኝነት “ከዘረኝነት ጋር ትንሽ ትንሽ የማመንዘር” ጥፋት! “ከመጠን ያላለፈ ዘረኝነት”?!

የተመጠነ ዘረኝነት፣ እንደተመጠነ አይዘልቅም!
በዘረኝነት ጉራንጉር ውስጥ ገብተው፣ ቆሻሻ ሳይነካቸው በድብቅ መንሸራሸራር፣ መራቀቅና መቀኘት የሚችሉ የሚመስላቸው አላዋቂዎች አሉ። እነዚህ “ለዘብተኛ ዘረኞች” የሚፈፅሙት ጥፋት ቀላል አይደለም። የብዙ ፖለቲከኞችና የብዙ ምሁራን ጥፋትም ይሄው ነው። “ዘረኝነት ከመጠን እንዳያልፍ መመጠን”፣ ከ“ጨዋ ደንብ” እንዳይወጣ መቆጣጠር፣ የሚችሉ ይመስላቸዋል። ወይ አለማወቅ!
በእርግጥ፣ ያገጠጠ ያፈጠጠ ዘረኝነትን አይሰብኩም። “ጨዋ ናቸው”።
በደበስባሳውና በጨዋ ደንብ፣… ልዝብ ዘረኝነትን መቀስቀስ ግን፣ “ጥበብ እና እውቀት” መስሎ ይታያቸዋል። በዘር መቧደንንና የጅምላ ፍረጃን በዘወርዋራ ማናፈስ፣ ‘በቅኔ’ መተንኮስ፣… እንደ ብልጣብልጥነት ይቆጠራል – በነዚህ ቤት።
ምን ዋጋ አለው? “ቀልድና ተረብ እያስመሰሉ… ከዘረኝነት ጋር ትንሽ ትንሽ እያመነዘሩ” መዝለቅ እንደማይችሉ አላወቁትም። “ክብራቸውን እንደጠበቁ”፣ በየመስኩ ላይ፣ በዘወርዋራ ዘረኝነትን እየዘሩ፣ ጭፍን ስሜትን ሲቀሰቅሱ ከከረሙ በኋላ፣… መስከረም ሲጠባ፣ መስኩ ሁሉ ይቀየርባቸዋል። እየተራቀቁ ሲጨፍሩበት በነበረው መስክ ላይ፣ ሌሎች አዳዲስ ተተኪዎች ይፈነጩበታል፤ የለየላቸው ዘረኞች ይነግሱበታል።
አዳዲሶቹ ዘረኞች፣ ነገሩን… ቀልድና ቧልት ለማስመሰል፣ ወይም በቅኔ ለማድበስበስ አይሞክሩም። በግላጭ በዘር እየተቧደኑ ነው በአደባባይ ጥፋትን የሚያውጁት። በዘወርዋራ ሳይሆን በየጎዳናው ነው፣ በጭፍን ስሜት ሰክረው አገር የሚቀውጡት፤… መስኩ ላይ ገናና የሚሆኑት።
የቀድሞዎቹ መሪዎችማ… እነኛ፣ “ከመጠን ያላለፉት፣ ከልዝብ ዘረኝነት ያልዘለሉት የድሮ ጨዋ መሪዎች”፣ “በተመጠነ ዘረኝነት መዳራትና መሽኮርመምን እንችልበታለን” በማለት ራሳቸውን እንደ ብልጣብልጥ ባለቅኔ ይቆጥሩ የነበሩ እነኛ የቀድሞ ገናና መሪዎች፣… ከጊዜ በኋላ፣ አድማጭ ማጣታቸውን ሲያዩ፣ መሪነታቸው በሌሎች “ጋጠወጥ ዘረኞች” እንደተነጠቁ ሲመለከቱ፤ … ምንም መናገር ምንም መስራት አይችሉም። እንደ አፋቸው ነው የሆነላቸው። የእጃቸውንም ነው ያገኙት። የዘሩትን ነው ያጨዱት። በገዛ ራሳቸው ቅስቀሳ ነው፣ የለየላቸው ዘረኞችን ያፈሩት።
በዚያ ላይ ደግሞ፣ በዘወርዋራ ልዝብ የዘረኝነት ዲስኩርን ይዘው እያራገቡ፤… እንዴት ብለው፣ ያገጠጠ ያፈጠጠ ዘረኝነትን መተቸት ይችላሉ? ከንቱ ነው። ማንም፣ ከቁብ አይቆጥራቸውም።
በቃ! የድሮዎቹ ብልጣብልጦች፣ የዘንድሮ ሞኛሞኞች ሆነው አረፉት።
በሌላ አነጋገር “የተመጠነ ዘረኝነት” ላይ እየተራቀቀና ትንሽ ትንሽ እያመነዘሩ መዝለቅ አይቻልም። ከመሃል ቆመው እየቆመሩ መቀጠል አይቻልም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፤ … ወይ ወደለየለት ዘረኝነት እየተንደረደሩና እየተንሸራቱቱ ይገባሉ፤…
አልያም፤… በትክክለኛው የእውነት፣ የስኬትና የሕይወት ጎዳና ለመጓዝ አቅጣጫቸውን ያስተካክላሉ! ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ ሌላ የሚያዛልቅ አማራጭ የለም። ሁለት አማራጮች ብቻ! እና ሁለት አይነት ሰዎች ብቻ!

1ኛ. በራሱ መልካምነት የሚተማመን ሰው
ማለትም፣…ለእውነት የሚቆምና በአእምሮው የሚተማመን ሰው፣… በጭፍን መከተልም ሆነ ማስከተልን የሚፀየፍ ሰው፣… አፋኝም ሆነ ታፋኝ መሆንን የማይቀበል፣ እውነትንና አእምሮውን የሚያከብር የእውቀትና የነፃነት ሰው፣…
በራሱ ጥረት ኑሮውን የሚመራና የስራ ውጤቱንም ከንጥቂያ ተከላክሎ የሚያስከብር፣ ጥገኛ ተባይነትንም ሆነ የተባይ ተሸካሚነትን የማይፈልግ፣ የሌሎች ሰዎችን ስኬት ለመዝረፍም ሆነ በምቀኝነት ለማቃጠል የማይመኝ፣ ራሱን ችሎ ለመኖር የሚፈልግ ሰው፣…
በእለት ተእለት ሃሳቦቹና ስራዎቹ አማካኝነት፣ የራሱን ብቃትና ጠንካራ ባህሪ የሚገነባ፣ በዚህም ክቡር የእኔነት ሰብዕናን የሚቀዳጅ ሰው፣… የሌሎችን ውርደት የማይመኝ፣ በዘር ወይም በብሔር ብሔረሰብ ተወላጅነት መቧደን የማይነካካው፣ “የጋራ ማንነት” በሚል ጩኸት የሰዎችን ንብረት ‘የጋራ ንብረት’ አስብሎ የማይዘርፍና ቀማኛ ያልሆነ፤ በራሱ የግል ብቃት የሚተማመን እንጂ፣ የሌሎች ሰዎች ብቃት “የጋራ ብቃት” እንዲሆንለት የማይመኝ፣ እንዲህ አይነት የንብረት ዝርፊያም ሆነ መንፈሳዊ ዝርፊያ የማይነካካው፣ የሌሎች ሰዎችን ብቃትና ጠንካራ ሰብዕና አይቶ የሚያደንቅና በአርአያነታቸው የሚበረታታ ሰው…
እንዲህ አይነት በራሱ የሚተማመን ሰው፣… በዘር የመቧደን በሽታ ውስጥ አይገባም። እንዲህ ነው፣ ሰው የመሆን ክብር።
የእኔነት ሰብዕናን የጣለ ሰውስ?
አእምሮውን ለመጠቀም፣ በጥረቱ የራሱን ኑሮ ለመምራትና፣ አንዳች ብቃት ለመገንባት ፈቃደኛ ያልሆነ ሰውስ?
እንዲህ አይነቱ ጭፍን፣ ክፉ፣ አይረቤ፣ መናኛ ሰው፤… የእኔነት እጦቱን፣ የማንነት ጉድለቱን ለማካካስ የሚሞክረው፣ በዘር በመቧደን ነው። ለመቧደን የሚሰባሰቡ ሰዎች፣… ጉድለቱን፣ ጥፋቱን፣ እኩይነቱን ቢያዩም እንኳ ችግር የለውም። “የኛ ወገን” ብለው የመቀበል ግዴታ እንደሚኖርባቸው ያውቃል። በዘር መቧደን እንደዚህ ነው። በዘር ወይም በብሔር ብሔረሰብ፣… ‘ወዳጅ’ እና ‘ጠላት’ ብሎ ጎራ መፍጠር!
በቃ! በንግግሩ ውሸታም፣ በሃሳቡ ቅዠታም፣ በድርጊቱ መሰሪ፣ በባህሪው ክፉ ቢሆንም እንኳ፣ ‘ወገናችን’ ብለው ይቀበሉታል። የሚናገረው ነገር ውሸት መሆኑ ችግር የለውም… የቋንቋ ታፔላውን በማየት ብቻ፣ ውሸታምነቱን በጭብጨባና በሆታ የሚያሳምሩ መስካሪ ይሆኑለታል – ፕሮፓጋንዳ እያስተጋቡ፣ አሉባልታ እየነዙ።
ቅዠታም ሃሳቡን የሚደግፉ ተከራካሪና ተንታኝ ይሆኑለታል። በድርጊቱና በውጤቱ አይመዝኑትም። ጥፋቱን የሚክቡ ነገረ ፈጅና ጠበቃ፣ የጥላቻ ስሜቱን ተቀብለው እያራገቡ፣ ስቃይና ሞት፣ ዝርፊያና ቃጠሎ የመዝራት ሱሱን የሚካድሙ ወዶ-ዘማቾች ይሆኑለታል።
መሰሪነቱንና ክፋቱን የሚያፀድቁ አዳናቂና አወዳሽ ይሆኑለታል። ቀሽም፣ አጥፊ፣ መጥፎና ክፉ ሰው… ይሄንን ሁሉ ቲፎዞ በነፃ ማግኘት የሚችለው፣ በዘር በመቧደን እንደሆነ ያውቃል። በተቃራኒው፣ እውነትን የሚፈልጉ ቀና ሰዎች፣ ‘አፋቸውን’ እንዲዘጉ ማድረግ የሚቻለውም፣ በዘረኝነት መቧደንን በመስበክ ነው።
ያኔ፣ እውነት ላይ ተመስርተው በትክክል ለማሰብ የሚሹ ሰዎች፣ ስድብና ውግዘት ይወርድባቸዋል። ጥፋትን ለመዝራት ሳይሆን፣ ለጠቃሚ ውጤት መስራትን የሚፈልጉ ሰዎች፣ የጥቃት ኢላማ ይሆናሉ። ስቃይና ሞትን ሳይሆን፣ በራስ ጥረት ስኬታማ መሆንን የሚያልሙ ሰዎች፣ የጥፋት ሰለባ ይሆናሉ። “ተግባራቸውንና ባሕርያቸውን አይቶ፣ የግል ሰብዕናቸውን የሚመዝን ሰው” እንዲኖር የሚፈልጉ እንጂ፣ የግል ሰብዕናን ለማጥፋትና በዘር ለመቧደን ስለማይፈልጉም፣ የጥላቻ ኢላማ ይሆናሉ።
ሁለት አይነት የአቅጣጫ አማራጮችና ሁለት አይነት ሰዎች፣ እነዚሁ ናቸው።
በዘር የመቧደን በሽታ፣ ለማን ‘አትራፊ’፣ ለማን ‘አክሳሪ’ እንደሆነ ግልፅ ነው።
ይህን በሽታ ለማስወገድና ለመከላከል በቅንነትና በፅናት አለመጣር፣… ያው፣ ከሰው ተራ በሚያወርድ የጥፋት ቁልቁለት ላይ ወደ እንጦሮጦስ እንደ መንሸራተት ነው።

Filed in: Amharic