>

ወሊሶ: በአንድ ቀን “ከሱናሚ ወደ ሰላም!” (ስዩም ተሾመ)

በትላንትናው ዕለት በአንዳንድ የኦሮሚያ አከባቢዎች ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ እንደነበር ይታወሳል። ሰላማዊ ሰልፉ በተለይ በአምቦ ከተማ በሰላም ሲጠናቀቅ፣ በሻሸመኔ ደግሞ የስምንት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ “Down Down Woyane” የሚል መፈክር ሲሰማ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያዎች ተገልጿል።

ነገር ግን፣ ትላንት ቀኑን ሙሉ በሌላ ጉዳይ ላይ እየፃፍኩ ነበር። ማታ ደግሞ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በአንድ የድህረገፅ ውይይት ላይ ተጋባዥ እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ነበር። በመጨረሻ ወደ መኝታ ስሄድ ከሌሊቱ 8፡00 ሆኗል። ስተኛ ግን “Down Down Woyane” የምትለዋን መፈክር እያሰብኩ ነበር። ምክንያቱም፣ መፈክሩ በራሱ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ወደየት እየሄደ እንደሆነ በግልፅ ይጠቁማል።

በእንቅልፍ ሰመመን ውስጥ ሆኜ “Down Down Woyane” የሚል ድምፅ ይሰማኛል። ትላንት ማታ በፌስቡክ ገፄ ላይ የተመለከትኩት ቪዲዮ ትዝ አለኝ። ለእኔ ለራሴ በሕልም ውስጥ ያለው መስሎኛል። አንዴ ተገላብጬ እንቅልፌን ልቀጥል ስል የመኪና ድምፅ ተሰማኝ። አንድ ዓይኔን አጮልቄ ሰዓት ስመለከት 2፡00 ሆኗል። ዘልዬ ተነሳሁና መጋረጃውን ገለጥ አድርጌ ስመለከት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች “Down Down Woyane” እያሉ ከግቢው እየወጡ ናቸው።

የተመለከትኩትን ማመን አቃተኝ! በእንቅልፍ ልብ ሁለት ወደኋላ የተመለስኩ መሠለኝ፡፡ አዎ… ህዳር 25/2008 ዓ.ም ላይ ያረፍኩ መሠለኝ፡፡ ከታች የምትመለከቱት ፎቶ ህዳር 25/2008 ዓ.ም ልክ እንደዛሬ ከእንቅልፌ በርግጌ ተነስቼ  በመስኮት ያነሳሁት ነው፡፡ የካምፓሱ ግቢ ውስጥ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ከውጪ በር ላይ ደግሞ የኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊሶች ወደ ግቢው ለመግባት ተሰልፈዋል፡፡ “በዚያን ዕለት ምን ሆን?” ለምትሉኝ ለመጀመሪያ ግዜ በድህረገፅ ላይ ከወጣሁት ፅሁፍ የተወሰነውን ቀንጭቤ እንዴት የወሊሶ ከተማ ከሰላም ወደ ሱናሚ እንደተቀየረች ላስነብባችሁ፦

“በወሊሶ የተካሄደው የሕዝብ ተቃውሞ የተጀመረው በዋናነት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች ሐሙስ፣ ህዳር 25/2008 ዓ.ም. ነበር። በቀጣዩ ቀን አርብ ዕለት የኦሮሚያ አድማ-በታኝ ፖሊሶች ወደ ካምፓሱ በመግባት ሰላማዊ የነበረውን የተማሪዎቹን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሃይል ለመበተን ጥረት አደረጉ። የክልሉ ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ የተቻኮለበት ዋና ምክንያት በካምፓሱ የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች ቦታዎች ይስፋፋል ከሚል ስጋት የመነጨ ነበር። ሆኖም ግን፣ የተቃውሞው እንቅስቃሴው በዚያኑ እለት በወሊሶ ከተማ ወደሚገኙት ሁለት የ2ኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች መስፋፋቱ አልቀረም። በተማሪዎች የተጀመረው እንቅስቃሴ በወሊሶ ከተማ ለታየው ታላቅ የህዝብ ተቃውሞ እንደ መነሻ ይሁን እንጂ በቀጣዩ ሐሙስ፣ ታህሳስ 02/ 2008 ዓ.ም በተካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው በአከባቢው ካሉ የገጠር ከተሞች የመጣው ህዝብ ነበር።”

ማታ እንዳይረብሸን ስልኬን ዘግቼ ነበር። ልክ ስከፍተው ታዲያ ጓደኞቼ እየደወሉ “ኧረ…ስዬ! እስካሁን ተኝተሃል!” ይሉኝ ጀመር። ብቻ አጠገቤ ያገኘሁትን ልብስ ልብሼ ከቤት እየሮጥኩ ወጣሁ። በአስፋልት ላይ ሰው ግራና ቀኝ እየተመመ ነው። መኪኖችና ባጃጆች በአስፋልቱ ላይ በሰላም ያልፋሉ። በመንገዱ ግራና ቀኝ ያለው ውጥረት የበዛበት ሁኔታ ባለ ባጃጆቹን ያስፈራቸው ይመስላል። ቆመው ሰው አይጭኑም። ስለዚህ በእግሬ ወደ መሃል ከተማ እየተጣደፍኩ ሄድኩ።

ልክ በወሊሶ ከተማ የሚገኘው ሉቃስ ሆስፒታል ጋር ስደርስ በግምት ከ3000 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በሶስት ቡድን ተከፍለው “Down Down Woyane” እያሉ ወደፊት ይሄዳሉ። የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር ቢሮ ጋር ስደርስ በአይን የማውቃቸው የአከባቢው የኦህዴድ አባላትና አመራሮች ከአስፋልቱ ዳር ቆመው የተቃውሞ ሰልፉን በፈገግታ ይመለከታሉ። ከእነሱ ውስጥ አንዱን “የጥምቀት በዓል ዛሬ ነው እንዴ?” አልኩት። ለካስ አለቆቹ በአከባቢው ነበሩ። “እ…እንዴት ነህ?” ብሎ የሃፍረት ፈገግታ አሳየኝ። በሰልፉ ውስጥ መሽሎክሎክ ቀጠልኩ።

በሰው መሃል እንደምንም እየተሸለኮለኩ ፊዲዮ ለመቅረፅና ፎቶ ለማንሳት ሞክርኩ። ድንገት አንዱ “አቁም!” ሲለኝ “እሺ” አልኩ። ወዳጄ በእንዲህ ያለ ቦታ የተባልከውን እሺ ማለት አለብህ። አለበለዚያ ተስካርህ ከወጣ በኋላ ነው ማንነትህን የሚያጣሩት። ስለዚህ “ጎመን በጤና” ብዬ ከመሃል ወጥቼ ወደፊት ሄድኩ። በመጨረሻ መሃል ከተማ አከባቢ ስደርስ ከሰላማዊ ሰልፉ ፊት ወጣሁ።

ሕዝቡ ብቻ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣ መስሎኝ ነበር። ለካስ በጣም ብዙ የክልሉ ልዩ ፖሊስ እና የከተማ ፖሊሶች ከፊት ለፊት አሉ። ፖሊሶቹ ሁኔታው ወደ ብጥብጥና ሁከት እንዳይነሳ በአግባቡ ሥራቸው እየሰሩ እንደሆነ ተመለከትኩ። በእርግጥ የፖሊስ ሥራ በሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ነው። በዛሬው ዕለት በወሊሶ ከተማ የተመለከትኩት ይሄን ነው።

ከዚህ በፊት የሀገራችን ፖሊሶች ለተቃውሞ አደባባይ የወጣን ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ በባለቤትነት ስሜት ሲረባረቡ፣ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይነሳ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክቼ የማውቅ አይመስለኝም። “ይሄን ነገርማ ለታሪክ በፎቶ ማስቀረት አለብኝ” ብዬ ከሰልፉ ፊት ለፊት ቆሜ ፎቶ ማንሳት ጀመርኩ። ከዛ አንዱ ፖሊስ በቁጣ “ና!” አለኝና ስልኬን ተቀበለኝ። “ከየት ነው የመጣህው?” ብሎ አፈጠጠብኝ። ሌላኛው ደግሞ በያዘው የፖሊስ ቆመጥ ሊጠርገኝ ሲቋምጥ በቆረጣ ተመለከትኩት። ወዲያውኑ አንድ የሚያውቀኝ ፖሊስ መጥቶ ስልኬ እንዲመለስልኝ አደረገ። በእርግጥ እኔም ትንሽ እንዳበዛሁት ታውቆኛል። ከዚያ በኋላ ከአንድ ጥግ ተቀምጬ ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩ።

በተቃውሞ ሰልፉ ላይ አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ፖሊሶቹ ድንጋይ በመወርወር ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሞክሮ ነበር። ፖሊሶቹም በምላሹ አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል። ሆኖም ግን፣ ፖሊሶቹ ወጣቶቹ በፍፁም ድንጋይ መወርወር እንደሌለባቸው እና እነሱ በቦታው የተገኙት የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሆነ ተናገሩ። በምላሹ ሰልፈኞቹ “ፖሊስ የሕዝቡ ጋሻ እንጂ ጦር አይደለም! ድንጋይ የሚወረውር ሰው ሰላይ ነው!” በማለት አወገዙት።

ዛሬ በወሊሶ ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ይህን ይመስል ነበር። የተቃውሞ ሰልፉ ፍፁም ሰላማዊ እንደነበር የሚያሳየው በሃገር ሽማግሌዎች ምርቃት (Video) መጠናቀቁ ነው። ልክ አሁን ወደ ወሊሶ ከተማ ብትመጡና “ጠዋት ላይ በግምት ከ15ሺህ በላይ ሕዝብ ለተቃውሞ ሰልፍ ወጥቶ ነበር” ብላችሁ በፍፁም አታምኑኝም። ጠዋት ላይ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ አሁን ላይ ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ተረጋግታ ነዋሪዎቿ መደበኛ እንቅስቃሴያቸውን ጀምረዋል።  ከሁለት አመት በፊት የኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊሶች የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎችን የተቃውሞ ሰልፍ በሃይል ለመበተን ያደረጉት ሙከራ “የሰላም ቀጠና” በመባል የምትታወቀዋን ወሊሶን በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ ሱናሚ ቀይሯት ነበር፡፡ የዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ግን በሰላም ተጠናቀቀ! ጠዋት ላይ ትልቅ ሱናሚ ተነስቶ ከሰዓት በኋላ ፍፁም ሰላም ሆነ፡፡ ከሁለት አመት በፊት በአንድ ሳምንት ከሰላም ወደ ሱናሚ የተቀየረችው ከተማ ዛሬ ደግሞ በአንድ ቀን ከሱናሚ ወደ ሰላም ተቀይራለች!

Filed in: Amharic