>
10:20 am - Friday October 22, 2021

''እናንተ የሀገሬ ልጆች፣....'' (ወሰንሰገድ ገብረኪዳን)

እናንተ የሀገሬ ልጆች፣
( እናንተ በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ኢትዮጵያውኖች፣
( እናንተ በደግነት የታነፃችሁ ደጋጎች፣
በቅድሚያ ይህንን መልዕክት የምፅፍላችሁ የጓደኛዬንና የሙያ አጋሬን አንደበት ተውሼ መሆኑን ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡
ወሰንሰገድ ገብረኪዳን
ትዝ ይላችኋል?! ከአንድ ወር በፊት በወርሃ ነሐሴ 2009 የመጀመሪያ ሳምንት እጅግ ያስደነገጠኝን ወሬ ነግሬአችሁ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ከቀደምት ጋዜጠኞች መሃል አንዱ የሆነው፣ ከ20 ዓመት በላይ በብዕሩ “ሀገሬን” እያለ የዘመረው፣ ለእውነት ስለእውነት ካለመታከት ሲተጋ የነበረው ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ማሞ በድንገት ባደረበት ሕመም የተነሳ አንድ እግሩ እንዲቆረጥ መወሰኑን ነግሬአችሁ ነበር፡፡
.
ግርማዬነህ ማሞ በ1980ዎቹ አጋማሽ ነው ነፃ ፕሬስን የተቀላቀለው፡፡ “ጉራማይሌ አሳታሚ ድርጅት” ያሳትም በነበረው “ታዛቢ” ጋዜጣ ላይ፡፡ ከዚያም በ“ጦማር” ጋዜጣ ላይ ተቀዳሚ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ቀጠለ፡፡ ያኔ በ“ጦማር” ጋዜጣ አዘጋጅነቱ ክስ ተመስርቶበት ወደ እስር ቤት ተወረወረ፡፡ ከተፈራ እስማረ እና እስክንድር ነጋ ቀጥሎ በጋዜጠኝነቱ እስር ቤትን ያሟሸ ነው ግርማዬነህ ማሞ፡፡ ለነገሩ ያኔ በርካታ ጋዜጠኞች በተከታታይ ዘብጥያ የተወረወሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ግርማዬነህ አንድ ዓመት ከአራት ወር እስር ቤት ሊከርም ግድ ሆነ፡፡ ዋስትና በማጣት፡፡ በወቅቱ 10 ሺህ ብር ነበር ዋስትና የተጠየቀው፡፡ ያኔ 10 ሺ ብር ከየት ይመጣል!? እንኳን እሱ፣ አሳታሚውም አይኖረውም፡፡ በአሁኑ ዘመን እናስበው ካልን ከ100ሺ ብር በላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሆነ ሆኖ 1 ዓመት ከ4ወር በኋላ ከእስር ተለቀቀ፡፡ ግርማዬነህ እስር አላስበረገገውም፤ በጋዜጠኝነት ቀጠለ፡፡ በፅናት በትጋት፡፡
.

ይህ ብርቱ ጋዜጠኛ ነው እግሩ በሐኪሞች እንዲቆረጥ የተወሰነው፡፡ ነገር ግን የሕክምና ወጪውን የሚሸፍንበት ገንዘብ አልነበረውም፡፡ ይህንን አስደንጋጭ ዜና ሰምቼ ልጠይቀው በሄድኩ ጊዜ “አየህ!…ዱሮም ምንም አልነበረንም፡፡ አሁን ደግሞ ከምንም ምንም አጣን” ብሎኝ ነበር ሳግ እየተናነቀው፡፡
.
የዛሬ ወር ልጠይቀው በሄድኩ ጊዜ ወዳጄን፣ የሙያ አጋሬን ያገኘሁበትን ሁኔታ የገለፅኩት እንዲህ ነበር፡- “ሳሎኑ ጨለምለም ያለመ ነው፡፡ እዚያ ጨለምለም ያለ ድባብ መሃል እጅግ የተጎሳቆለ ፊቱ ከጥቀርሻነት አልፎ ከሰል የመሰለው ግርማዬነህ ሳሎን ውስጥ (ሳሎን ከተባለ) የሚገኝ ረዘም ያለ ሶፋ ላይ ተቀምጧል፡፡ ዐይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡ እጅግ በጣም ከስቷል፡፡ ያ ከአመታት በፊት የማውቀው፣ ያ ለ7 ዓመታት ያህል (ከ90 -97) አብሮኝ “ኢትኦጵ” ጋዜጣ እና መፅሔት ዝግጅት ክፍል የሰራው፣ ያ ሮጦ ሮጦ የማይታክተው፣ ያ የሙያ መምህሬ (አርአያዬ) ከምላቸው ሰዎች አንዱ፣ ያ ብርቱ፣ ቁርጠኛና ትንታግ የነበረ ሰው … ከሰውነት ተራ ወጥቶ፣ ‹የሰው ያለህ› እያለ ሳገኘው….. በቃላት የማይገለፅ ህመም ውስጤን አተራመሰው፡፡”
.
እናም ይህንኑ ሁኔታ እኔና ሌሎች ወዳጆቼ ለእናንተ ለደጋጎቹ፣ ለእናንተ ለሃገሬ ልጆች ነግረናችሁ የዕርዳታ እጃችሁን እንድትዘረጉለት ጥሪያችንን አስተጋብተን ነበር፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ከትናንትና በስቲያ ጋዜጠኛ ግርማዬነህ ስልክ ደውሎ ጠራኝ፡፡ ሄድኩ፡፡ ግርማዬነህ ሳሎን ውስጥ የሚገኝ ሶፋ ላይ ጋደም ብሏል፤ ከፊቱ የሚገኘው የሶፋ ጠረጴዛ ላይ ሬዲዮ እና መፅሐፍ ተቀምጧል፡ ከሶፋው በስተቀኝ የእንጨት ክራንች ቆሟል፡፡
“በክራንች መንቀሳቀስ ጀመርክ እንዴ?” ስል ጠየቅኩት፡፡
“ቤት ለቤት ብቻ፤ …. ውጪ መውጣት አልችልም፤”
“አሁን እንዴት ነህ?”
“ይመስገነው፤ አሁን ደህና ነኝ” አለ ታፋው ላይ የተቆረጠውን እግሩን እያየ፡፡ “አሁን ጳውሎስ አጠገብ የሚገኝ የአካል ድጋፍ የሚሰራበት አርተፊሻል እግር እየተሰራልኝ ነው፤ እስከዚያ ለ3 ወር ያህል ልምምድ ማድረግ አለብኝ፤ አሁን እዚያ እየሄድኩ ልምምድ እያደረግኩ ነው፡፡” አለኝ በፈገግታ ተሞልቶ፡፡ ባለፈው ወር የግርማዬነህ ፊት ክስ…..ል ያለ ጥቁረት ሸፍኖት ነበር፡፡ በጣም ከስቶ ፊቱ ምጥጥ ብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ፊቱ ፈክቷል፤ ወዙ መለስ ብሏል፡፡
“መልካም ነው፤ ጥሩ ለውጥ አሳይተሃል፤ በሰላም ነው ግን ስልክ ደውለህ የጠራኸኝ?” ስል ጥያቄ አስከተልኩ፡፡ በመጥፋቴ ጥቂት ተገቢ ወቀሳ ቢጤ ከሰነዘረ በኋላ “በሰላም ነው፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ሁሌም ደግነት ለማይለያቸው የሃገሬ ልጆች የምስጋና መልዕክት እንድታደርስልኝ ነው” አለኝ፡፡
.
( እናንተ የሀገሬ ልጆች፣
( እናንተ በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ኢትዮጵያውኖች፣
( እናንተ በደግነት የታነፃችሁ ደጋጎች፣
.
በአጋጠመኝ ሕመም የተነሳ እግሬን ማጣቴን፤ በእጄ ለመታከም የሚያስችለኝ ገንዘብ እንደሌለኝ ሰምታችሁ፣ ከያላችሁት የዓለም ክፍል የእርዳታ እጃችሁን የዘረጋችሁልኝ ደግ ኢትዮጵያውኖች በሙሉ፣ በጭንቅ ጌዜ ምርኩዝ ሆናችሁኛልና እግዜር ይስጥልኝ፡፡ የእናንተ ደግነት የእግሬ መቆረጥ ካስከተለብኝ ጉዳት በላይ የደቆሰኝን የመንፈስ ስብራት ጠግኖታልና፣ አለኝታዎቼ ሁናችኋልና፣ ምስጋና የማቀርብበት ቃል ያጥረኛል፡፡ እንደው በደፈናው በያላችሁበት ሰላምና ጤና ከእናንተ ጋር ይሁን! ክብረት ይስጣችሁ!
.
እናንተ በብዕራችሁ ስለፍትህ፣ ስለእውነት፣ ስለሃገር የዘመራችሁ፣ በዚህም ተጋድሎችሁ የተነሳ ጥርስ የተነከሰባችሁና ከሀገራችሁ ለመሰደድ የተገደዳችሁ የሙያ አጋሮቼ፣ በአስቸጋሪው የስደት ህይወት ውስጥ ሆናችሁ እኔን ለማሳከም ተረባርባችሁልና፣ በትጋታችሁ “መድኃኒት ሆናችሁኛልና” የላቀ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
.
እናንተ የ“ተዘንአ” ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያችሁ፣ እጅግ ከፍ ባለ የሙያ ስነምግባር፣ በመልካም ፍቅርና ትህትና ታድጋችሁልኛልና እነሆ ምስጋናዬን ተቀበሉ፡፡
.
ባለችሁ አቅም እኔን በገንዘብ ከመርዳት ባሻገር፡ ከያላችሁበት የዓለም ክፍል ስልክ እየደወላችሁ ላፅናናችሁኝና ላበረታታችሁ ወገኖቼ ሁሉ፣ መልካምነታችሁን የምገልፅበት ቃል የለኝም፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሌር ይስጥልኝ!
.
ይህ የጋዜጠኛ ግርማዬነህ ቃል ነው፡፡ እኔም በወገኖቼ በኢትዮጵያውያን ደግነት ኮርቻለሁ፣ እናም ይህንን እላለሁ፡፡ ስለሆነው፣ ስለተደረገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እግዚአብሔር ይስጣችሁ!!

Filed in: Amharic