>
9:08 pm - Wednesday February 8, 2023

መዝሙሯን በሙሾ፣ እምቡጥ ህልሞችዋን በጭንገፋ ያጣች ምስኪን ሀገር! (ደረጀ በላይነህ)

“የአማራ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የኛ ህዝብ ነው፡፡ የሲዳማ፣ የሶማሌ፣ የአኙዋክ፣ የጉራጌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል – ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ የእኛ ሕዝቦች ናቸው፡፡–”

ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የተሰሩ መዝሙሮች ያደመጠች፣ እንቡጥ ህልሞች ያየች፣ ግና መዝሙሯን በሙሾ፣ እምቡጥ ህልሞችዋን በጭንገፋ ያጣች ምስኪን ሀገር ናት፡፡ ጦርን ወደ ማጭድ፣ የጥይትን አረር ወደ ስንዴ ዛላ ለመቀየር፣ ትውልዶች እንደ ጅረት ሲፈስሱ ለማየት ተመኝተው፣ ዘምረውላታል። አንዳንዶቹም ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው፣ ደማቸው እንዲያዘምር፣ ምድረበዳው ፅጌረዳ እንዲያበቅል ተማፅነው አልፈዋል፡፡
መዝሙር ደስ ይላል፣ ምኞትም ያጓጓል። ህልም መሬት ሲረግጥ፣ ፍሬ ሲያፈራ ደግሞ ለትውልድ የፍስሃ መስክ ያበጃል፡፡ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ከሰማናቸው እሾሃማ ህልሞች፣ የቂምና የበቀል ሻካራ ድምፆች አስቀድሞ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሳይገዛና ሳይጠቀልል በፊት በየዐውደ ግንባሩ፣ ምኞቱ ሰማይ የቧጠጠው ህዝብ ዘምሮለት ከሽፏል፡፡
የጭቆና ቀንበር ከብዶ በላያችን
በግብር በጉቦ አልቆ ጉልበታችን
በጦር በሰፈራ – አልቆ ወዘናችን
መጣልን ኢሕአዴግ የነፍስ አባታችን፡፡
— በማለት የወሎና የጎንደር ህዝብ፣ አጥናፋት የሚያስተጋባ የተስፋ መዝሙር ዘምሯል፡፡ ይሁንና ይህ መዝሙር ውሎ ሲያድር እውን አልሆነም፤ ሳቃችን ተነጥቆ፣ በእንባው ውስጥ ተደፍቋል፣ የሚሉ ምሬቶች ጎልተዋል፡፡
እንደታሰበውና እንደተወራው፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበርና ብልፅግና ሳይሆን መናቆርና መባላት በዝቷል፣ የሚል ማልጎምጎም ምድሩን ሞልቶታል፡፡ ለሃያ ስድስትና ሃያ ሰባት ዓመታት!
ይህንን ድምፅ ፈትሾ፣ ጎልጉሎና መዝኖ፣ ለነገ ሌላ ተስፋ የሚሰጥ ሌላ ድምፅ ደግሞ ሰሞኑን ብቅ ብሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ድምፅ ነው፡፡ ለሃያ ሰባት ዓመታት የተበታተነውን ልብ ባንድ ፍቅር የሚያስር፣ የተቃቃረውን ስሜት በይቅርታ ስሜት፣ በይቅርታ ፀበል የሚያጠምቅ፣ የተስፋ ብርሃን አድማሳትን እየታከከ ነው፡፡ ሳቅ እየፈጠረ፣ ልብ እያበረታ ነው፡፡
በተለይ ሰሞኑን በመገናኛ ብዙኃን ያደረጉዋቸው ንግግሮች፣ የብዙዎችን ልብ ሰርቆ፤ ሃሳባቸውን አቁሞ፣ ደግመው ስለ አገራቸው እንዲያስቡ የሚያደርግ አዲስ ክብሪት ጭረዋል፡፡ ክብሪቱም በሰዎች ልብ ውስጥ ሻማ እየለኮሰ፣ የደበዘዘውን ሀገር በብርሃን ያጥለቀልቀዋል የሚል ምኞት ፈጥሯል፡፡ በተለይ፣ “አንድ ህዝብ አንድ ሀገር፣ አንድ ዓላማ ነው ያለን፡፡ ይህ ከሆነ ለምን እንከፋፈላለን? ለምን እርስ በርስ እንበላላለን? አንደኛችን በሌላችን ላይ ለምን በተንኮል እናሴራለን?” ሲሉ የተናገሩት፡፡
እንደኔ እንደኔ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ትልቁ ችግራቸው፣ በዘርና በጎሳ መከፋፈልና መናቆር ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት ነገር የሀገር ተስፋ ነው፤ የትውልድ ተስፋ ነው፡፡ ሰውየው፣ ሀገሪቱ ገደል ዳር የደረሰችበትን ችግር በሚገባ ያጤኑ ይመስለኛል። መራራ ጥላቻ የተፈጠረውም ልዩነታችንን ስላራገብን መሆኑ ገብቷቸዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም የኛ ዐይነት ጠባሳዎች አሏቸው። ግን ጠባሳቸውን ፈግፍገው አላቆሰሉትም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ኢሕአዴግ አንድነትና ፍቅርን አልሰበከንም። የሚያስታርቁንን ነገሮች አልቆሰቆሰም፡፡ የጥላቻ እሳት ነው ያራገበው፡፡
አሁን በቅርቡ በሀገራችን ምስራቃዊ ክፍል የተፈፀመው ዓይነት ሰቆቃ መደገም የለበትም፡፡ ማምለጥ አለብን፡፡ የመማፀኛ ከተማ ያስፈልገናል። ሰዎች ሮጠው የሚደበቁበት የብሔራዊ አንድነት ታዛ ማዘጋጀት ይገባናል፡፡
ይህቺ ሀገር ቀጣይ ጉዞዋ ሊሰምር የሚችለው በእነ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ዓይነት ህልም ብቻ ነው፡፡ በአንድነትና በፍቅር ብቻ፡፡ እንደቀደሙት ዓመታት በመጠላለፍና አንዱ ባንዱ ላይ ጠማማ ሴራ በመሸረብ የትም አይደረስም፡፡ ምድራችንን የደም ምድር ከማድረግ ውጭ የተሻለ ተስፋ አይኖረንም! መንግስትም፤ “እኔ ከሌለሁ ትፈርሳላችሁ!” እያለ የሚያስፈራራውን የልጅ ጨዋታ ማቆም ያለበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ የሚፍለቀለቅ ቁጣና ብሶት አለ፤ እርሱ አደባባይ ላይ ፈስሶ ሳያጥለቀልቀን በፊት በአጭሩ ለመግታት ምርጫው አንድ ነው … አንድነት ብቻ!
የመንግስትን “እኔ ነኝ መሲሁ፣ እኔ ነኝ ድልድዩ” የምትል ሀሳብ፣ ቀጣይዋ ግጥም ቁልጭ አድርጋ የምትገልጥልኝ ይመስለኛል፡፡
“በኔ መንገድ ካልሄድክ
መንገድህ ገደል ነው” ማለት የሚከጅል
“እንደኔ ካላሰብክ
ማሰብ አትችልም” ሊል የሚዳዳው ጅል
በህይወት መንገድ ላይ…
እንደራሴ ስሄድ፣ ነፍሴ ምትሞግተው
ብዙ ግድግዳ አለ
“ድልድይህ ነኝ!” የሚል፣ መሻገር ሲያቅተው፡፡
(በላይ በቀለ ወያ)
ይህ የኢህአዴግ መዝሙር ዳግመኛ ማስፈራሪያ አለንጋ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል ራሱም ሳይረዳው አይቀርም፡፡ በየሰፈሩ የሚነፈርቀው አመፅ፣ የብዙ ዓመታት እምቅና ማስተንፈሻ ያላገኘ ቁጣ ውጤት ነው፡፡ መንግስት ለጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ የተለየ ሀሳብ ያቀረቡ ሰዎችን ለቅሞ በማሰርና በማሰቃየት ስልጣኑን ለማዝለቅ ሲጥር ቆይቷል፡፡ የተለያዩ ታርጋዎችም መስጠት ይችልበታል፡፡ እነዚያ ሁሉ ግን የማይጠቅሙበት ቀን ይመጣል፡፡ ገጣሚው ዮናስ ኪዳኔ እንዳለው፡-
አየሽ እዚህ ሀገር ከንቱ ፍረጃ አለ!
አማኝ ሁሉ አክራሪ
ሙስሊሙ አሸባሪ
ጉራጌ ቋጣሪ
ትግሬ ሁሉ ወያኔ
ወጣቱ ወመኔ—
ወገኖቼ ይህ ለማናችንም አይጠቅመንም፡፡ ይህ ለአማራም ሆነ ኦሮሞ፣ ለትግሬም ሆነ ሶማሌ ለማንም አይጠቅምም፡፡ እንጀራና ክብር አይሆንም። የኛ አይነት ጠባሳ ያለባቸው ሀገራት፣ እድፉን ያጠቡት በይቅርታ ነው፡፡ ይቅርታ ደግ ነው፡፡… የአሜሪካ የእርስ በርስ ግጭት፣ የደቡብ አፍሪካ የግፍ ትዝታ ሁሉ ወሰን የተበጀለት በይቅርታና ያለፈውን ትቶ ለመጪው በማሰብ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
የኛ መንግሥት ግን ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ችግሩን ለማየት አልፈለገም፡፡ መሪዎቹ ዕድሜያቸው ሲገፋ እንኳ ስለ ትውልድና ታሪክ ማጤን አልወደዱም፡፡ ሁሌ የሚገርመኝ ያ – ነው። በስሜታዊነት ዕድሜ የወጠኑትን፣ በሰከኑ ጊዜም አላቀኑትም፡፡ ይልቅስ ልዩነትንና መከፋፈልን እንደ ክብር አራገቡት እንጂ፡፡
አዎ፤ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ደግ ነው፡፡ ማንም አንገቱን ሳይደፋ እኩል የሚደመጥበት፤ ባህሉን፣ ቋንቋውንና ማንነቱን የሚቀበልበትና የሚያሳድግበት አደባባይና ፍትህ ማግኘቱ ደስ ይላል፡፡ ግን ከገዛ ወንድሙ ጋር የጎሪጥ እየተያየ፣ ከንፈር እየተናከሰ እንዲኖር ማድረግ በደል አይደለምን?.. አንዱ ባንዱ ላይ እንዲነሳሳ – ቂም ቆፍሮ፣ መራራ ሲጠጣ ማየት ምንድን ነው መጨረሻው? ውጤቱ አሁን በቅርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች፤ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” ብለው ዜግነታቸውን እንዲፀየፉ የሚያደርግ መርዝ መቀመም ነው፡፡
ብዙዎቻችን በተማሪዎቹ ፈርደን ይሆናል፤… ግን ይህ የእነርሱ ጥፋት ነው?… አይደለም። ከተወለዱ ጀምሮ በየስብሰባው፤ በየመገናኛ ብዙኃኑ የዘራንባቸው ዘር ውጤት ነው፡፡ እነርሱ አማራና ኦሮሞ በዘመነ ደርግ እንዴት እንደኖሩ፣ ትግሬና ኦሮሞ ምን ዝምድና እንዳላቸው፣ ጉራጌና ሶማሌው እንዴት እንደተሳሰሩ የት ያውቃሉ?… የሚያውቁት የተነገራቸውን፣ አጼ ምኒልክ ሰሩት የተባለውን ግፍ ነው፡፡ እነሱ የሚያውቁት፣ አማራ— ኦሮሞ..ወላይታ— ጉራጌ ተብሎ የተወራላቸውን የተበታተነ የትዝታ አጽም ነው፡፡
እውነት ለመናገር፣ ጊዜን ቂም ላይ መጨረስ ጥቅሙ ምን ይሆን? …በተለይ ለአንድ አገር ህዝቦች። ይሄን በተመለከተ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ያለፈውን እያነሱ መውቀስና ማውራት ዋጋ የለውም፤ ይልቅስ እኛ መሥራት የሚገባንን መሥራት አለብን ነው – የሚሉት፤ ቃል በቃል እንዲህ፡-
“የአማራ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የኛ ህዝብ ነው፡፡ የሲዳማ፣ የሶማሌ፣ የአኙዋክ፣ የጉራጌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል – ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ የእኛ ሕዝቦች ናቸው፡፡”
እንደ እኔ፣ እኚህ ሰው ለቀጣይዋ ኢትዮጵያ ውበትና ሕይወት ናቸው፡፡ ሀገራችንን አሁን ከተጋፈጠችው አደጋ ሊያሻግሯት በፈጣሪ የተላኩ የኖህ መርከብም ይመስሉኛል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ልንፈርስ ጫፍ ላይ ነን፡፡ ልንበታተን ምንም አልቀረን፡፡ ክፉኛ መነቋቆር ጀምረናል፡፡ ልባችን ተለያይቷል፡፡ ስለዚህ የፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ዓይነት አቋም ያላቸው ሰዎች ያስፈልጉናል። ከተሳካልን ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ይልቅስ ትታደሳለች፡፡ በፍቅርና በአንድነት ትድናለች። ኢሕአዴግም ራሱን ከመሸንገል በዚህ ጠበል መጠመቅ ያዋጣዋል፡፡
አማራው ነፍጠኛ
ደርግ ሁሉ ግፈኛ
ናቸው እያስባለ
ቁልቁል የሚነዳን ጭፍን ጥላቻ አለ፡

Filed in: Amharic