>
4:35 pm - Monday October 19, 8201

ወና ቤተ-መንግሰት (ታምሩ ተመስገን)

ከሰሞኑ እየተቀሰቀሱ ስላሉ ትኩሳቶች ጥቂት ነገር ማለት ፈለኩ፡፡ እኔ ወግ ፀሀፊ እንጂ የፖለቲካ ተንታኝ አይደለሁም ግና አዕምሮየ ውስጥ ደባል ማስቀመጥ አልሻምና የተወሰነ ልበላችሁ…
አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው 2007 
 ላይ የአመራር ስነ-ልቦና የሚል አንድ መፅሀፍ አሳትሟል፡፡ በአንድ ወቅት በአካልም የማግኘት እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ለማታውቁት አምባሳደር አሳምነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ ዲግሪ አግኝቷል፡፡ በአሜሪካኑ አለምአቀፍ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በአለምአቀፍ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪ ሰርቷል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መ/ቤት ፣ በናይሮቢና ዋሽንግተን የኢትዮጲያ ኤምባሲዎች በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች አገልግሏል፡፡ በሱማሊያም ባለሙሉ አምባሳደር ነበር፡፡ እስከማውቀው ድረስ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር በገባው ቅራኔ መነሾ ከስርዓቱ ተለያይቶ አሜሪካን ሀገር ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ ይገኛሉ፡፡
.
መፅሀፉ ውሰጥ ያገኘሁትን አንድ ግንጣይ ታሪክ ልንገራችሁ…
…. ኦሪያና ፋላሲ የታወቀች ኢጣሊያዊ ጋዜጠኛ ነበረች፡፡ ከመሞቷ በፊት ዴንግሻዎ ፒንግ ፣ ዳይላላማን ፣ ጎልዳማየርን ፣ ኢንድራ ጋንዲን ፣ አያቶላ §ሚኒን ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ታላላቅ የዓለም መሪዎችን ቃለ መጠየቅ አድርጋለች፡፡ ሙአመር ጋዳፊም ቃለ መጠይቅ ካደረገቻቸው መሪዎ አንዱ ነበሩ፡፡ ሙአመር ጋዳፊ የፖለቲካ ፍልስፍናቸው የተብራራበት ነው ተብሎ የሚነገርለት አረንጓዴው መፅሃፍ የተሰኘ መፅሀፍ ነበራቸው፡፡ ሙአመር ጋዳፊ መፅሀፉ ዓለምን ነፃ ለማውጣት በመለኮታዊ መንፈስ እንደተፃፈ ያምኑ ነበር፡፡ ጋዳፊ በስልጣን ሀብት ታውረው እንኳንስ የታመቀውን የህዝብ ቁጣ ሊገነዘቡ ይቅርና ምድራዊ መሆናቸውንም ረስተው ነበር፡፡ ደፋርና ጥልቅ ጋዜጠኛዋ ኦሪያና ከበርካታ አስቸጋሪ ጥያቄዎች በኋላ ስለአረንጓዴው መፅሀፍ አነሳችባቸው፡፡ “እውነት ይህች ትንሽ አረንጓዴ መፅሀፍ አለምን እንደምትቀይር እርግጠኛ ነዎት?” ብላ ስትጠይቅ ቅዱስ መፅሀፍ እንዳራከሰች ቆጥረው ፊታቸው ተለዋውጦ እንደእብድ ማንባራቅ ጀመሩ፡፡ “አረንጓዴ መፅሀፉ አዲስ ቅዱስ መፅሀፍ ነው፡፡ መፅሀፌ ውስጥ ያለው አንድ ቃል ዓለምን ሊያጠፋ ይችላል፡፡ በመፅሀፌ ውስጥ ያለው አንድ ቃል ዓለምን ማዳን ይችላል፡፡ የሁሉምንም ዋጋ መለወጥ ይችላል፡፡ ክብደታቸውን መጠናቸውን፡፡ ምክንያቱም እኔ አዲሱ መሲህ ነኝ፡፡” አሏት፡፡ የመሲሁ ጋዳፊ የመጨረሻው እጣ ፈንታ በስልጣን እብሪት የናወዘው አዕምሯቸው በግፍ ስርዓታቸው በተማረረው ህዝባቸው የቁጣ በትር መቀጥቀጥ ነበር፡፡
.
…. ይቺን ታሪክ መንደርደሪያ አድርገን ከቁልቁለቱ ደረት ላይ ስንደርስ የኛዎቹ የስልጣን ጥም ያልበረደላቸው መረዎቻችን ወደመውደቁ ሲንደረደሩ እናስተውላለን፡፡ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም፡፡ ሁሉም የእጁን ሊያገኝ የዘራውን ሊጭድ ከቁልቁለቱ ደረት ላይ እየተገፋፋ ይንደረደራል፡፡ ጨለማ ላይ ብናፈጥበት እንዳይነጋ ጨለማ ነው ግና ለእርሱ ቀን አለለት ብርሃን ያነገሰ ቀን፡፡ ዛሬ ጧት ቢቢሲ ላይ ኦክቶበር 16 የወጣ ዜና በረከት ስምዖን የስራ መልቀቂያ አስገቡ ይላል፡፡ ደነገጥኩ፡፡
 ቀደም ብሎ አባዱላ ለቀቁ በመቀጠል ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መልቀቂያ አስገቡ፡፡ በመሰለስ ደግሞ በረከት ስምዖን ሌላ መልቀቂያ አስከተለ፡፡ በቃ አትዮጲያ ቀን ወጣላት ሲሉ የደስታ ርች ት ሲተኩስ ተመለከትኩ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ መርዶ እንደሰማ ሰው ክው ብየ ነው የደነገጥኩት፡፡ እኔ ስልጣን መልቀቃቸው ሳይሆን ስልጣን የለቀቁበት መንገድና ወቅት ነው ያስደነገጠኝ፡፡ በምርጫ ተረካክበን ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ግና ምርጫው 2 ዓመት ይቀረዋል ገና፡፡ በዚህ ከቀጠሉ በአንድ ቀን ቤተ-መንግስቱ ሲከፈት ባዶ ስናገኘው አይታያችሁም? በነፃነት መሻት ብቻ እየመጣ ያለውን አደጋ እንዴት ማየት ተሳናችሁ? ሀገራችን በብሄር ልዩነት እና በስልጣን ጥማት እየታመሰች ባለበት በዚህ እሳት ወቅት ዙፋኑን እንደፈለጋቸው ከጋጡ በኋላ እሳት ላይ ጥደውን ሲከበልሉ እንዴት አይታያችሁም? ሊያጫርሱን ‘ኮ ነው? አንበልና ቤተመንግስንት ባዶ ያገኘነው ጊዜ ማነው ገብቶ የሚመራን? ማንስ ነው የሚመራ? አንተ… እኔ… እኛ… እነርሱ ወይስ እነዚያ? አይታያችሁም ስንባላ? ብሄራዊ አንድነት ሳይኖረን እንዴት ሆኖ ነው አንደኛው ሌላኛውን ይመራ ዘንድ ከዙፋኑ የሚቀመጠው? ከፈረሱ ጋሪው ሲቀድም አይታያችሁምን? ወይስ ከድጡ ወደማጡ ሆኖ እርስ በእርሱ ጦር እንዲማዘዝ ሊሆን ነው? ድል ማለት ዛሬን በድል ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን የነገም ባለቤት ለመሆን ከወዲሁ የተዘጋጀ ተቋም መፍጠር ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች አካሄድ ግን ምንም አልጣመኝም፡፡ 27 አመታት ካደረሱብን ጥፋት የሚልቅ ታላቅ ጥፋት ጥለውብን ሊያልፉ እያንዣባቡ ይመስኛል፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጲያን ያስባት፡፡
Filed in: Amharic