>
11:28 am - Friday May 20, 2022

ሰልፉ ማንን ይጠቅማል? (ደረጀ ገረፋ ቱሉ)

ኦህዲድን በሰልፍ ቢዚ አድርጎ ተወዳዳሪን ዘና ማድረግ !! ሰልፉ ማንን ይጠቅማል ? 
ብዙዎቻችን ከሰልፉ ጥቅም ይልቅ ሰልፉን ማን ጠራው በሚለው ላይ አተኩረን ቆይተናል።በእርግጥ ይህ አስፈላጊ ነገር ነው።ነገር ግን ሌላ እጅግ አስፈላጊ ነገር እና ምናልባትም የሰልፉን ባለቤቶችም ለመለየት የሚረዳን የሰልፉ ጥቅም እና ውጤት ላይ ስናተኩር ነው።
አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ሁለት ነገር ግልፅ ነው።
1 በኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች መካከል መደበቅ በማይቻልባት ደረጃ ሽኩቻ አለ። አንደኛው አባል ፓርቲ ሌላኛውን በሰላማዊ ውድድር ብቻም ሳይሆን በግልፅ የጥሎ ማለፍ ደረጃ አንዱ አንዱን ለመጣል በእጁ ያሉትን የፌደራልም ሆነ የክልል ስልጣን የመጠቀም አዚማምያ እየታየ ነው።
2 ሌላው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በዚህን ጊዜ ምንም ነገር ቢፈጠር ከኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ውጭ ሀገሪቷን ሊያስተዳድር የተዘጋጀ እና በቂ ሃይል ያለው አካል የለም።ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ።ለጊዜው እዚያ ውስጥ አልገባም።
ዋናው ነገር በሀገሪቷ በዚህን ጊዜ ከኢህአዴግ ውጭ የገዘፈ እና ጠንካራ ሃይል ባለመኖሩ ማናቸውም የሚናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታቸው ቢያንስ ለጊዜው አንደኛውን የኢህአዲግ አባል ፓርቲ በመጉዳት ሌላኛውን ተጠቃሚ አድርገው የውድድር ሚዛኑን ያዛባሉ። አሊያም ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው ሀገሪቷን ለመፍረስ ያባቃሉ።
ለምሳሌ በ2008 እና በ2009 የተካሄዱትን የኦሮሞ የአመፅ እንቅስቃሴዎችን በደንብ ቢንገመግም ውጤቱ ከዚህ የተለየ ነገር አለነበረም።በወቅቱ የተደረገው እንቅስቃሴ ሰልጣን ላይ ያለው ኦህዲድ እንዲሞት በማድረግ ሌላ የኦህዲድ አካል ስልጣን እንዲያዝ አድርጓል።የዛኔው ሰልፍ ለኦሮሞ ሊጠቅም የቻለው ተላላኪ ኦህዲድ በማውረድ አላቃችን ህዝባችን ነው የሚል የኦህዲድ አመራር ስልጣን እንዲቆጠጠር ማድረግ መቻሉ ነው።ቀጥሎ በሰልፍ የሚመጣ ነገር ካለ ተቃራኒ ውጤት ነው።
ከዚህ በኃላ የኦሮሞ ህዝብ ከሰልፍ ለመጠቀም ከፈለገ ለተወሰነ ጊዜ(የስልጣን ሽኩቻው እስክጠናቀቅ) ኦህዲድ እራሱ የሚጠራው እና የሚመራው ከሆነ ብቻ ነው።
ከዚያ ውጭ የ2008/9 ሰልፍ በሌሎች ተቀዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ላይ ያለው ተፅዕኖ ከሞላ ጎደል ጥሩ አልነበረም ።አመፁ የተቃዋሚውን ገመና ገልፆ ለህዝቡ በማሳየት ህዝብ ከተቃዋሚው ጎራ ምንም እንዳይጠብቅ ነው ያደረገው።በእርግጥ እንደ OFC ዓይነቱ ደግሞ አመፁን ተንተርሶ በኢህአዲግ በተወሰደበት የሃይል እርሚጃ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ተደርጓል ።ካለፈውም ዓመፅ የሚንረዳው የአመፁ ተፅዕኖ አዎንታው ውጤት ያስመዘገበው በዋናነት የኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች ላይ መሆኑን ነው።
ለታሪክም ሆነ ለሌላ ነገር እደግመዋለሁ!
ከዚህ በኃላ ለተወሰነ ጊዜ(ሽኩቻው እልባት እስኪያገኝ) በኦሮሚያ ምድር የሚደረጉት ሰልፎች እራሱ ኦህዲድ ካልጠራው እና ካልመራው(ወይም በኦህዲድ ይሁንታ ከልተጠራ ) በስተቀር ምንም አወንታው አስተዋፆ ለኦሮሞ ህዝብ አይኖራቸውም ።ይህ የተወሰንን ሃይሎች ስለፈለግነው ወይም ስለጠላነው ሳይሆን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስገድደን ነው።

አሁን ከላይ ያነሳናቸውን ሁለት ነጥቦች (በኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግልፅ ሽኩቻ እና በሀገሪቷ የፖለቲካ ምህደር ከኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች ውጭ በቀጣዩ የሀገሪቷ እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ ድርሻ ሊኖረው የሚችል አካል አለመኖሩን ) አያይዘን በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለውን የሰላማዊ ሰልፍ እና ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ትንሽ ሰፋ አድርገን ብንገመግም፦
በሰልፉ በብዛት የሚወገዘው ህወሃት ቢሆንም ሰልፉ የሚካሄደው የህወሃት እስትራክቸር ባሌለበት ነው።ሰልፉ የህወሃት እስትራክቸር ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ የለውም።
ሰልፉ የሚካሄደው ኦሆዲድ በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ ነው።ሰልፉን የሚቆጣጠረው ኦህዲድ ነው።ፖሊስ በማዘጋጀት የተሰላፍዉን ደህንነት የሚጠብቀው ኦህዲድ ነው።ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ሰልፉ ላይ ያልተሳተፉትን ህዝቦች ሰላም እንዳያውኩ፣ንብረታቸውን እንዳያወድሙ የመጠበቅ ግዴታ ያለበት ክልሉን የሚያስተዳድረው ኦህዲድ ነው።
ለዚህ ለክልል አቀፍ ሰልፍ ጥበቃ ለማድረግ እና በክልሉ ባሉት ህዝቦች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይደርስበቸ ጥበቃ ለማድረግ የክልሉን ፖሊስ ከቦታ ቦታ እያንቀሳቀሰ ጥበቃ ማድረግ ያለበት ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ኦህዲድ ነው።ይህ ብዙ የሰው ሃይል እና ገንዘብ ይጠይቃል ።ይህ ክልል አቀፍ ሰልፍ በመሆኑ ከላይ እስከታች ያለው የኦህዲድ አመራር በአባል ፓርቲዎች መካከል ያለውን ሽኩቻ ማሸነፊያ ስልቶች ለመንደፍ ሳይሆን በክልሉ ያሉትን ተራ አገልግሎቶች ለማቅረብ እንኳን ጊዜ እንዳኖረው ያደርጋል።የክልሉ መንግስትእና ክልሉን የሚያስተዳድረው ገዥ ፓርቲ በሰላማዊ ሰልፉ ተጠምዶ ሽኩቻውን በአሸናፍነት እዲይያጠናቅቅ የሚያስችለውን ስልት መንደፍ ይቅር እና ለክልሉ ህዝብ ምንም ዓይነት የልማት ስራ የማይሰራ ከሆነ አሁንም ዘላቂ ህልውናው አደጋ ውስጥ መግባቱ አይቀርም ።
የክሉ መንግስት በሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት በክልሉ ውስጥ ያሉትን የሌሎች ብሄሮች ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ፣ በክልሉ ያሉት የፌደራል መንግስትም ሆነ የግል ንብረቶችን ከሰላማው ሰልፈኞች ጥቃት መከላከል ካልቻለ የክልሉ መንግስት እና ገዥው ፓርቲ ያለው ተዓማንነት እንዲጠፋ ከማድረግ አልፎ ከወዲሁ እንኳን ሀገር ክልልም ለማስተዳደር ያልቻለ የሚለውን ምስል ለመቅረጽ ያገለግላል።
ነገሩ ገፍቶ ከሄደም በህወሃት ቀጥታ ንብረት የሚንቀሳቀስ ሳይሆን በፌደራል መንግስት ባጀት የሚንቀሳቀሰው የመከላከያ ሃይል እና ፌደራል ፖሊስ የኦሮሚያ ክልል የሚቆጣጣራቸውን አከባቢዎች ይረከብ እና ማስተዳደር ይጀምራል።ይህ ሲሆን በለፈው ዓመት አይተናል።ነገሮች ከገፉ አሁንም ደግመን ማየታችን አይቀርም።
ለማጠቃለል አሁን በኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄዱ ባሉት ሰልፎች
እየተወገዘ ያለው ህወሃት ቢሆንም
1 ጫናው እያረፈ ያለው ኦህዲድ ላይ ነው።
2 ቢዚ እየሆነ ያለው ኦህዲድ ነው።
3 በቀጥታ ከህዝቡ ጋር እየተጋጨ ያለው ኦህዲድ ነው።
4 እየሞተ ያለው የኦሮሞ ህዝብ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ነው።
5 ኢሜጁ እየተበላሸ ያለው እና አቅም አልባ እንዲመስል እየተደረገ ያለው የኦሮሚያ ክልል እና ኦህዲድ ነው።
6 ጭቅጭቁ እየተፈጠረ ያለው በኦሮሞ ሙሁራን መካከል ነው።
7 ስለ ሰልፉ እንጂ ስለ ስልጣን ሽኩቻው እንዳያስብ እየሆነ ያለው ኦህዲድ ነው።
8 ስለሰልፉ እንጂ ስለተፈናቀሉት ከግማሽ ሚለየን ባላይ ኦሮሞዎች እንዳያስብ የሆነው የኦሮሚያ ክልል መንግስት አመራር ነው።
9 የፌደራል መንግስቱን ለማጥቃት የመዘዛቸው ትላልቅ አጀንዳዎች እርባናብስ እንዲሆነበት የተደረገው ኦህዲድ ነው።
10 ከመከላከያው ጋር አላስፈላግ ግጭት ውስጥ እንዲገባ እና እንዲጠረጠር እየተደረገ ያለው ኦህዲድ ነው።
11….
ህወሃትን እያወገዘ በለው ሰልፍ ህወሃት ምን ሆነ ?
1 ብዙ ጠላት እንዳለው በማሳየት ብዙ ተጋሩዎችን ከጎኑ እንዲቆሙ ማድረግ ችሏል።
2 በስልጣን ሽኩቻው ከሚሳተፉት አንዱ ተወዳዳር ቢዝ ሲሆንነለት ህወሃት ለሽኩቻው ስልት መንደፍያ ጊዜ ማግኘት ችሏል።
3 ተሰላፊዎች በሚያደርጉት አንዳንድ ኢ ህገመንግስታው በሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ምክንያት በኦህዲድ ላይ በህግ የክርክር መድረክ ላይ ሊያቀርብበት መረጃ እያሰባሰበ ነው።
4 ሌሎች የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እና የኢትዮጵያ ህዝብ ኦህዲድን እንዲጠራጠሩት እና እንዲፈሩት ለማድረግ እድል አግኝቷል።
5 እንደመከላከያ እና ፌደራል ፖሊስ ያሉት ተቋማት የኦሮሚያ ፖሊስ እና አስተዳደር ከሰልፉ ጋር በተያያዘ እገባለሁ አትገቡም የሚለውን አተካራ በመጠቀም ህወሃት እነዚህን ተቋማት ይበልጥ ከጎኑ ያሰልፋል።ኦህዲድን ደግሞ ይበልጥ እንዲጠራጠሩት ያደርጋል።
6…..ስለዚህ ከሰልፉ ማን ተጠቀመ? ግልፅ ነው።
በሰልፉ ማን እየተጎዳ ነው? የኦሮሞ ህዝብ እና ኦህዲድ እየተጎዳ ነው።
ሰልፉን በተቀናጀ መልኩ ማን እየደገፈው እና እያስተዋወቀው ነው? ዛሚ እና ግብረአበሮቹ እንደሆኑ ግልፅ ነው።
ህዝቡ ሰልፉ ላይ ለምን ተሳተፈ ?በቂ ምክንያቶች አሉት።
ህዝቡ እያነሳቸው ካሉት አጀንዳዎች የኦሮሚያ መንግስት የማይቀበላቸው አሉ? የሉም።

ህወሃት የሚቀበላቸው አጀንዳዎች አሉ?የሉም።
እነዚህን አጀንዳዎች የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አሁን ለብቻውን ይፈታቸዋል?አይፈታቸውም።
ህወሃት ቢፈልግ እነዚህን አጀንዳዎች መፍታት ይችላል? አዎን ይችላል።
እነዚህ አጀንዳዎች አሁን ህዝቡ እያደረገ በለው ሰልፍ ምክንያት መልስ ያገኛሉ?አያገኙም።
አጀንዳዎቹ መልስ ማግኘት የሚችሉት ኦህዲድ ተዳክሞ እጅ ሲሰጥ ወይም ተጠናክሮ በደንብ መደራደር ስችል ነው።ስለዚህ ጥያቄዎቹ መልስ እንዲያገኙ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የኦሮሞ ህዝብ ድርሻ ነው።
ኦህዲድ አሁን ሰልፍ ከቀጠለ ይዳከማል ወይስ ይጠናከራል?በጣም ይዳከማል።

በአጭሩ የሰልፉ ጥቅም ምንድነው? ኦህዲድን ቢዚ አድርጎ ህዋሃትን ዘና ማድረግ ነው።
የሰልፉ ደጋፍዎች የሰልፉ ትልቁ ስኬት አድርገው እሚቆጥሩት ምንድነው?ቀውሱ ተባብሶ ኦሮሚያን እንደገና በአስቸኲይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መክተት፤ኦህዲድን እንደገና ደካማ አድርጎ በማዋቀር የስልጣን ሽኩቻውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ነው።
አንዳንድ አርቆ(በረጅም ጊዜ እነሱም ከሰልፉ ስለማይጠቀሙ ነው።ኦህዲድ ተስፋ ከቆረጠ ሰልፉን ከመከላከል ወደ መቀላቀል መግባቱ ስለማይቀር ነው።) የማያስቡ የህወሃት ደጋፍዎች ይህንን ሰልፍ ብደግፉት ይገርማል?ለምን ይገርማል?ውድድር አይደለም እንዴ?
አንዳንድ የኦሮሞ አክስትቭስቶች ይህንን ሰልፍ ለምን ይደግፋል?ድንዙዝ ስለሆኑ ወይም ቆለጣቸው ስለተያዘ ነው።
ስለዚህ ሰልፉ የማነው ? ሰውዬው አተወኝም!
ምነው ? ፈራህ እንዴ? እኔ እንጃልህ !!
ማሳሰቢያ የህወሃት ደጋፍዎች በዚህ ፅሁፍ የተለየ ትኩረት የተሰጣቸው ዋና ተወዳዳር ስለሆኑ እና ሰልፉን ከሚደግፉት የእህት ፓርቲዎች መካከል ከህወሃት ደጋፍዎች በስተቀር ሌሎቹን ስላላየሁ ብቻ ነው።ከዚያ በተጨማሪ በሰልፉ በብዛት እየተወገዘ ያለውም ህወሃት ሰለሆነ ነው።

Filed in: Amharic