>
5:14 pm - Tuesday April 20, 7993

የእፉኝቶች እናት!... (አስሜክስ)

አንዲት እናት አለች ~ የእናቶች አውራ
እርጥብ ማህፀኗ ~ ሚሊዮኖች ያፈራ ።
ተረግማ እንደው እንጃ ~ ወይ አንሷት ምርቃት
ይኸው ስንት ዘመን ~ መከራ ‘ሚንጣት

አለች አንዲት እናት

ወልዳ የመከነች
ከብዳ የቀለለች
አምና የናቀች
ኖሯት የደኸየች

]አንዲት እናት አለች

ለምለም አፈሯ ላይ ~ ቂም እየተዘራ
ልጆቿ እያጭዱ ~ የበቀል አዝመራ
ለፍቅር ተኮንና ~ ጥላቻን ‘ምትሰፍር
የተፈረደባት ~ ደም ገብራ እንድትኖር

አለች አንዲ አንዲት

ጠግባ የተራበች
ሰብታ የሞገገች
ሰፍታ የጠበበች

አንዲት እናት አለች

ቀዳሚ ታሪኳ ~ በክፋት ደብዝዞ
የንፉቅቅ የምትሄድ ~ በኋልዮሽ ጉዞ
የስልጣኔ አልፋ ~ በኩር እንዳልነበረች
ችሮትን ጠባቂ ~ ቀላዋጭ የሆነች

አንዲት እናት አለች

ነቅታ ያንቀላፋች
ቀንታ የጎበጠች
ከብራ የወደቀች
ፈክታ የጠቆረች

አንዲት እናት አለች

#እፉኝት_ልጆቿ ~ እንደቅርጫ ስጋ
ዘ-ል-ዝ-ለ-ው………..




………………………………እየተቃረጧት
በልተው ሊጨርሷት ~ አንድ ሃሙስ የቀራት

አለች ምስኪን እናት

ፍቅርን ተጠምታ ~ ፍቅርን ተርባ
ሳቋን ተቀምታ ~ ሃዘን ተከናንባ
ጉልበቷን ታቅፋ ~ ደም የምታነባ

ከአምናው ፣ አቻምናው ~ ዘንድሮ ብሶባት
ስቃይ የምታምጥ ~ ፈውስ የቸገራት

አለች አንዲት እናት!!
==============
አሁንስ እኔ ‘ንጃ
እንጃ ፈርቻለሁ
እንጃ ሰግቻለሁ ~ በርትቷል ስቃይዋ
ደመና ውጦታል ~ ዙፋነ ሰማይዋ ።

አሁንስ እኔ ‘ንጃ
እንጃ ሰግቻለሁ

የቀስተደመና ~ አምሳል ምልክቷ
የሷነት መለያ ~ ግምጃ መቀነቷ
ላልቶ አይቻለሁ !!

አሁንስ እኔ ‘ንጃ
እንጃ ፈርቻለሁ !!

እንጃ ሰግቻለሁ ~ ለዝች “መካን” እናት
ኪዳንዋን አስቦ ~ ፈጣሪ ካልረዳት
በዛሬ ስቃይዋ
ፈራሁ ለነገዋ
ዋ!!!

Filed in: Amharic