>

ሀገራዊ ዕብደት (ዳንኤል ክብረት)

ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ
በቤታችን ደኅና መጥፋቱ ነወይ

የሚል የበገና ዘለሰኛ አለ፡፡ አሁን ያለችውን ሀገራችንን ቀድሞ ያየ ደራሲ መሆን አለበት የገጠመው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ጤነኛ አካል የጠፋ ይመስላል፡፡ የገዛ ወገኑን አባርሮ የሚፎክር ወገን፣ ሕዝብ እንዳይሰደድ የሚያደርግ አሠራርና አስተዳደር መዘርጋት ሲገባው ሲያባብስ ኖሮ ሕዝብ ሲሰደድ መጠለያ ድረስ ሄዶ የሚጎበኝ ባለ ሥልጣን፣ የሀገሩን ሀብትና ንብረት አቃጥሎ በኩራት የሚደነፋ ጎረምሳ፤ ሕዝብን እያዋረደና እየተሳደበ መግለጫ የሚሰጥ የክልል ሹም፤ ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሲበላሽ እያየ መንገዱን ለመመርመር የማይፈልግ መንግሥት፤ ሀገር እየጠፋ ግደል ተጋደል የሚል ተቃዋሚ፣ ለሌላው ይተርፋል ሲሉት የራሱ የሚያርበት የእምነት ተቋም፤ ጢሱ እንዳይነካው ተደብቆ ገሞራ ሊያስነሣ የሚባዝን የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናይ፤ የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል ሳይሆን የምእመኖቻቸውን የጫማ ቁጥር የሚተነብዩ ‹ነቢያት›፣ ምኑ ቅጡ – ሁሉ በሽተኛ ሆኗል፡፡ በቤቱም ደኅና ጠፍቷል፡፡

ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት እየወደቅንም እየተነሣንም፣ እየተቃቀፍንም እየተቧቀስንም፣ ሆ ብለን እየወጣንም አድፍጠን እየተቀመጥንም፤ እየተከፋፈልንም አንድ ለመሆን እየሞከርንም፤ እያሠርንም እየታሠርንም ለመጓዝ ሞክረናል፡፡ ማንም የአንድ ዓመት የልጅነት ልብሱን በሃያ ስድስት ዓመቱ አይለብስም፡፡ ኢትዮጵያም እንዲያ ሆናለች፡፡ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት የተሰፋው ልብሷ ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ – እየተቀዳደደ ነው፡፡ ሊጣፍ፣ ሊሰፋ አይችልም፡፡ አሁን ሌላ ልብስ ያስፈልጋታል፡፡ ‹ሞኝ ማለት በተመሳሳይ መንገድ እየሄደ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ነው› ይባላል፡፡ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ ማላዘናችን አላዋጣንም፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ መንገድ ልንሞክር ግድ ነው፡፡
ሰውዬው ሴትዮዋን ወዳጁ ለማድረግ በሠፈሯ በኩል በሚያልፈው መንገድ ያለማቋረጥ ሲመላለስ አየችውና

አምናና ታች አምና ሳይሆን እያየህ
ዛሬም በዚያው መንገድ ትታክታለህ› አለቺው አሉ፡፡

ይህ ችግር የሁለት ወገኖች ችግር ነው፡፡ የመንግሥትም የተቃዋሚውም፡፡ ሁላችን ላለፉት ዓመታት የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት የተጓዝንበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ተመሳሳይ መንግሥታዊ መንገድ፤ ተመሳሳይ የተቃውሞ መንገድ፡፡ የሀገሪቱ ሁኔታ ግን እየባሰና እየተወሳሰብ ነው፡፡ የትውልድም ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ በ1983 ዓም የተወለደ ልጅ ዛሬ 26 ዓመቱ ነው፡፡ እኛ ግን በ1966 ባሰብነው መንገድ አሁንም እየተጓዝን ነው፡፡

ችግሩ ሲወሳሰብ ሀገራዊ ዕብደት ተፈጥሯል፡፡ ሰከን ብሎ፤ ለሀገርና ለወገን አስቦ፣ ሁሉም የሚያሸንፍበትን፤ ይበልጥ ደግሞ ሀገር የምታሸንፍበትን መንገድ ከመተለም ይልቅ ሁሉም ባገኘው መሣሪያ ይጫረስ ይዟል፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ከምንደርስበት ግብ ይልቅ ለምንሄደው መንገድ መጨነቅ ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት አንድን ስሕተት በስሕተትነቱ ከመኮነን ይልቅ የማን ወገን ይህን አደረገው ለሚለው ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት በሌላኛው ጥግ ያለው የመርከቧ ክፍል ሲቃጠል እኔ እተርፋሁ ብሎ በአንዱ ጥግ ቆሞ መሳቅ ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ዛፉ ከሥር እየተገዘገዘ ቅርንጫፉ ላይ ሆኜ እተርፋለሁ ብሎ ማለም ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ከአእምሮ ይልቅ ለስሜት ቅርብ መሆን ማለት ነው፡፡ ሀገራዊ ዕብደት ማለት ሁሉ የሚጫረስበት፤ ተው የሚል የሚጠፋበት፤ ተው ማለት የሚገባቸውም አብረው የሚያብዱበት ማለት ነው፡፡

ታዋቂው የጎንደር ዘመን ሊቅ፣ የሰባት መጻሕፍት ደራሲ፣ የዐፄ በካፋን ዜና መዋዕል የጻፈው አዛዥ ሲኖዳ ‹ፍጻሜ መንግሥት› የሚል መጻሐፍ አለው፡፡ በዚያ መጽሐፉ ላይ ‹እነዚያ ሰዎች የገዛ ቤታቸውን አቃጥለው (እሉ ሰብእ ይኮሰትሩ ቤቶሙ ወይትዋነዩ በነዲዱ፣ ወዝንቱ ዘመን ይሰመይ ዘመነ አብዳን) በእሳቱ የሚጫወቱበት ዘመን ይመጣል፡፡ ያም ዘመን ዘመነ አብዳን ተብሎ ይጠራል› ይላል፡፡ ያ ዘመን አሁን ይመስላል፡፡ የሀገራችን ሰዎች በነውሩ ይዝናናሉ፣ በግፉ ይኩራራሉ፣ በጥፋቱ ይመካሉ፣ በችግሩ ያቅራራሉ፣ በመከራው ይስቃሉ፡፡ የገዛ ሀገራቸው እያቀጠሉ እሳት ይሞቃሉ፡፡ የተረፈውም የዕብድ ገላጋይ ሆኖ ጎራዴ ያቀብላል፡፡

ሀገር ከዘመነ ዕብደት እንድትወጣ ሰከን ብለው ከስሜታቸው፣ ከጥቅማቸው፣ ከክብራቸው፣ ከጎሳቸውና ከሥልጣናቸው በላይ የሚያስቡ ዜጎች ያስፈልጓታል፡፡ እንግሊዝ የኦጋዴንን መሬት ለኢትዮጵያ እኤአ በ1954 ከመመለሷ በፊት ካሊ በተባለ ቦታ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ የጎሳ መሪዎችን ሰብስበዋቸው ነበር፡፡ በዚያ ሸለቆ ውስጥ የተሰባሰቡ የጎሳ መሪዎች ሦስት አማራጭ እንደቀረበላቸው በወቅቱ ልጆች ሆነው ነገሩን የተከታተሉና ከሽማግሌዎቹ የሰሙ የሀገር ሽማግሌዎች በቦታው ላይ ሲናገሩ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ ከታላቋ ሶማሊያ ጋር ትዋሐዳላችሁ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ትዋሐዳላችሁ ወይስ ራሳችሁን ትችላላችሁ፡፡ እንዲያውም የእንግሊዙ መኮንን አንድ ከሸማ የተሠራ ልብስ አምጥቶ በቁጥቋጦው ላይ ጣለውና መልሶ አነሣው፡፡ ልብሱ በቁጥቋጦው እሾህ ተቀዳዶ ነበር፡፡ ‹ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዋ እንዲህ ነው› አላቸው፡፡ እነዚያ የጎሳ መሪዎች ግን ኢትዮጵያ ድኻ፣መንግሥቷም የማይስማማን መሆኑን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ከእርሷ ተገንጥለን አንወጣም› ማለታቸውን ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል፡፡

አሁን ያ ዘመን አልፎ የዕብደቱ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የሀገሬ መሬት ማለቱ ቀርቶ የጎሳዬ መሬት እንላለን፤ የክልል ድንበሮች አጥሮች ሆነዋል፡፡ ከክልል ክልል ከመሄድ ከኢትዮጵያ ኬንያ መሄድ ቀላል ሆኗል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ መሆኑ ቀርቶ መለያያ ሆኗል፤ የጨቋኝ ተጨቋኝ ታሪክን ተርከን ተርከን ሁሉ ዐርበኛ ሆኗል፡፤ 3000 ዓመት የነጻነት ታሪክ አለን እያልን 3000 የነጻ አውጭ ድርጅቶችን መሥርተናል፡፡

ከጎርፉ ጋር በፍጥነት አብሮ የሚወርድ ዋናተኛ ለራሱም አይበጅ ሌላውንም አያድን፡፡ ወንዙን አቋርጦ ራሱንም ሌላውንም ለመታደግ ሦስት አማራጭ ነው ያለው፡፡ የዋናተኛው ዐቅም ከወንዙ ዐቅም በላይ ከሆነ ያቋርጠዋል፡፡ የወንዙ ዐቅም ከዋናተኛው ዐቅም እኩል ከሆነ እንዳይነቃነቅ አድርጎ ይቸክለዋል፡፡ የወንዙ ዐቅም ከዋናተኛው ዐቅም በላይ ከሆነ ይዞት ይሄዳል፡፡ አሁን ሀገሬ ያለችው ሁለተኛው ላይ ነው፡፡ የወንዙ ዐቅምና የኛ ወንዙን የማቋረጥ ዐቅም እኩል ሆኗል፡፡ ስለዚህም ወይ ችግሩ አይፈታም፤ ወይ እኛ አንፈታም – ተቸክለናል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የወንዙ ኃይል እየጨመረ፣ የኛም ዐቅም እየቀነሰ መጥቶ ይዞን መሄዱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ዕብደት ላይ ስላለን፤ መሐል ወንዙ ላይ እንዳንነቃነቅ ሆነን ቆመን ወንዙን እያቋረጥኩት ነው ብለን እናስባለን፣ እንደሰኩራለንም፡፡
መሐል ወንዝ ላይ ማቋረጥ አቅቶት የቆመ ሰው አማራጩ ሦስት ነው፡፡ ወይ ዋናውን ትቶ በሌላ መንገድ (ቢችል በእግሩ መሬት ረግጦ ለመውጣት) ይሞክራል፤ ወይ ኡኡ ብሎ የሌሎችን ርዳታ ይጠይቃል፤ አለያ ደግሞ ወደ ፈጣሪው ይማጸናል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃንም ያሏቸው አማራጮች እነዚህ ናቸው፡፡ ያለበለዚያ ግን ሀገራዊ ዕብደቱ እየጨመረ ሄዶ ወንዙ ሁላችንንም ጠራርጎ ይወስደናል፡፡ የማንፈልግበት ቦታም ያደርሰናል፡፡

Filed in: Amharic