>
9:30 am - Sunday January 29, 2023

ማነዉ ዘረኛ? (ሞሃ ሞሰን)

ኦሮሞ ወይስ እኛ

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ የማዉቀዉንና የኖርኩበትን እዉነት በመጻፍ ሐገሬ ላይ እያንዣበበ ባለዉ አደገኛ ሁኔታ የተነሳ እንደዜጋ ሐላፊነቴን ለመወጣት ነዉ::

በርዕሱ ላይ እኛ ስል ለመግባባት ያህል ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዉጪ ያለነዉን ማለቴ ነዉ፤ … በተረፈ እኔ ስለብሄር ጣጣ እያወራዉ አይደለም፤ እኔም አላዉቀዉም፤… እናትና አባቴም ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰብ የተገኙ አይደሉም፤ ነገር ግን ብሔርን መምረጥ ግዴታ ቢሆንብኝ የኖርኩበትን፣ ያደግኩበትን፣ በደንብ የማዉቀዉን፣ ማንነቴ የተሰራበትን፣ … ኦሮሞነት ወድጄዉ ከመምረጥ ዉጪ ሌላ ማንነት የሌለኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ የኦሮሞን ጉዳይ ጉዳዬ የማይል ኢትዮጵያዊ እሱ ገና ሐገሩን ጠንቅቆ አላወቃትም፤ … ብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዉያን ሌላ ማንነታችንን ሳናዉቅ የምንኖርበት፣ የተዋለድንበት፣ ላንለያይ በጋብቻና ሌሎች ጉዳዮች የተሳሰርንበት፣… ብቻ መሆኑ አይደለም፤ የሷ ሰላም መሆን እንደ ሐገር ለመቀጠልም ግዴታ ስለሚያስፈልግ ነዉ፡፡

ሰላማቸዉ ከሰላማችን፣ ሀዘናቸዉ ከሀዘናችን፣ ደስታቸዉ ከደስታችን፣ እድገታቸዉ ከእድገታችን፣ … ማንም አስረጂ ሳያስፈልገዉ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ሐቅ ነዉ፡፡ ለዚህም ምንም አይነት የምሁርም ሆነ ሌላ የፖለቲከኛ ትንታኔ አልሻም፤ እኔ በተግባር ስላየሁት፣ ስለኖርኩበት፣ አሁንም ብዙ ሚሊየኖች በኦሮሞ አቃፊነት ባህልና ስርዓት ታቅፈዉ የሚኖሩበት ነባራዊ እዉነት ነዉ፡፡ ይህን በራሱ ህያዉ ሆኖ የቆመን ሀቅ ግን ብዙዎቻችን የተረዳነዉ አይመስለኝም፤ ጉዳዩ ሰፊ ዉይይትና ትንታኔ የሚሻ ቢሆንም፣ እኔ ግን ከወቅታዊዉ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሶስት አንኳር ማሳያዎችን ልምዘዝ፡፡

የመጀመሪያዉ ፊደል ቀመስ ነን የምንባል ሰዎችን ይመለከታል፤… እነደ ሐገር ለመቀጠላችን ዋናና ወሳኝ በምንለዉ ቀጠና ዉስጥ እስከአሁን ሲፈጠር ለነበረዉ ትርምስና ችግር በቂ፣ ተከታታይ እና አጥጋቢ ትንታኔዎችንም ሆነ ተሳትፎዎችን ማየት አልቻልኩም፤ ለምንድነዉ የመፍትሄ ሐሳቦች በበቂ ሁኔታ የማይሰነዘሩት?… ይህ ጥያቄ እኔን በሁለተኛነት ወደማነሳዉ ማሳያ ነጥብ ይመራኛል፤ ወደ ጥርጣሬ፡፡

በኦሮሞ ህዝብና ጥያቄዎቹ ላይ ያለን የጥርጣሬ አመለካከት ሁለተኛዉ ነጥቤ ነዉ፤… ሁልጊዜም በኦሮሞ ተወላጆች የሚነሳን ጥያቄ ከማጤን ይልቅ በጥርጣሬ የምንመለከት ሰዎች ትንሽ አይደለንም፤ … ለምንድነዉ ከጎናቸዉ ለመቆም ስጋት የሚገባን? ለምንድነዉ ጉዳያቸዉ የማይገደን? ለምንድነዉ ስኬቶቻቸዉን እንኳን በጥርጣሬ የምናየዉ? መልካም ስራቸዉንና መልካም ሰዎቻቸዉን በቋንቋቸዉ የተነሳ ብቻ ለምን ማድነቅ ይሳነናል? ለምንድነዉ በርካታ ሚሊየኖችን አቅፈዉ በሰላም ማኖራዉ የማይታየን? ለምንድነዉ መብታቸዉን ሲጠይቁ ለፍረጃ የምንቸኩለዉ? ለምንድነዉ ለኢትዮጵያ መቆም ያኖሩትን ግዙፍ አሻራ የምንዘነጋዉ? ለምንድነዉ ኦሮሞን ድል ከሐገር መበታተን ጋር የምናያይዘዉ?… እንዲህ ከሆነ ታዲያ ለምንድነዉ ስለ ኦሮሞነታቸዉ ሲያነሱ የምንኮንናቸዉ?… ፌዴራል ላይ ጥሩ ሲሰሩ የዘመርንላቸዉ ሰዎች ክልል ሄደዉ ለክልል መስራት ያለባቸዉን በመስራታቸዉ ብቻ ለምን በጥርጣሬ አይን ይታያሉ?… ጥያቄዉ ብዙ ነዉ፤ እንደኔ የዚህ መሰሉ ችግር አንዱ መነሻ ኢትዮጵያን ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመጣ የከተሜ ፖለቲከኛነት ይመስለኛል፡፡…

ጎበዝ ጉዳት እየደረሰ ያለዉ በህዝቡ ቢሆን እኮ ማንም ከልካይ የለም፤ ማንም በምንም አይነት ጥበቃ ሳያግዳቸዉ በብዙ ሚሊየኖች ላይ በየቀኑ ብዙና አስከፊ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ነበር፤ በድፍን ኦሮሚያ ገጠርም ሆነ ከተማ ኦሮሞ ብቻዉን አይኖርም፤ …
ለምንስ ነዉ የበዪ ተመልካች በመሆናቸዉ ልንቆረቆርላቸዉ ሲገባ የጨከንባቸዉ?… አንድ ነገር መርሳት የለብንም፤ በኢኮኖሚ አቅሙ የፈረጠመ የማፊያ ቡድን በአዲሱ የኦህዴድ አመራር አስደንጋጭ እርምጃ እንደተወሰደበት ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ይህም በማስረጃ ጭምር ተደግፎ ያየነዉ እዉነት ነዉ፤ ስለዚህ እያንዳንዱን እንቅስቃሴም ከዚህ የማፊያዎች ድርጊት ጋር አያይዞ ማየትም ያስፈልጋል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የአጋርነታችንን ጉዳይ ነዉ የማነሳዉ፤ … ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮምኛ ተናጋዎች ግልጽና የተቀናጀ ዘመቻ እንደተካሄደባቸዉ ከፍንጭ በላይ የሆኑ ማሳያዎች አደባባይ መዋል ከጀመሩ ሰነበተ፤ እጅግ አሳዛኝና አሰቃቂ ከሆነዉ ሞት በተጨማሪ አስደንጋጭ መፈናቀል ተስተዋለ፤ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሰዉ በገዛ ሐገሩ ላይ ተፈናቃይ ተባለ፤ ሀብትና ንብረቱን አጥቶ በየመጠለያዉ ወደቀ፤ በተቃራኒዉ ግን በጥርጣሬ የምናየዉ ህዝብ ከተደረገበት በጣም የላቀዉን ማድረግ እየቻለ ሳያደርገዉ ቀረ፤… ይህ ሁሉ ሰዉ አዝኖና ተፈናቅሎ፣ ከቋንቋዉ ተናጋሪ ዉጪ ያለን ሰዎች እንዴት ጉዳያቸዉን ቀዳሚ ጉዳያችን አላደረግነዉም? … እንዴት ነዉ ታዲያ ጉዳያቸዉ ጉዳያችን መሆኑን ሳንቀበል፣ በተግባር ሳናሳይ፣ አጋር ሳንሆናቸዉ፣ አቅፈዉ እየሳሙን እኛ ሳናምናቸዉ፣… አትሂዱብን፣ የማንነት ጥያቄ አታንሱብን፣ …ማለት የሚቻለዉ? ይህ ብቻዉን አይበቃም፡፡…

ጉዳዩ ከዚህ በብዙ እጥፍ የሰፉ ትንታኔዎችንና ዉይይቶችን ይፈልጋል፤ የኦሮሞ ጉዳይ ለሐገሪቱ መቀጠልም ሆነ መቆርቆዝና መዉደቅ ወሳኝ መሆኑን ለአፍታ እንኳን ልንዘነጋዉ የማይገባ እዉነት ነዉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ሁሉ ከግንዛቤ ሳናስገባ ወደሌላዉ የምንጠቁመዉ ጣት አንድ ብቻ ሲሆን የተቀሩት አራቱ ግን ወደኛ የሚጠቁሙ መሆናቸዉን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም አንድ አንኳርና ላነሳኋቸዉ ነጥቦች ጥሩ ማሳያ ምሳሌ ላቅርብ፤ በኦሮሞ ህዝብም ሆነ በሌላኛዉ ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘዉ የአኖሌን ሀዉልት ያቆመዉ የነሙክታር አስተዳደር ነዉ ወይስ ኦሮሞነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር አስተሳስሮ ያቀቀነዉ የነለማ አስተዳደር?…ይህ መልስ የሚያስፈልገዉ ጥያቄ ሆኖ አይደለም፤ ይልቅስ ጉዳዩ ከኦህዴድ በላይ በቅጡ ስላልተረዳነዉ የኦሮሞ ህዝብ ብዙ ነገር ስለሚነግረን እንጂ፡፡

Filed in: Amharic