>
4:34 pm - Tuesday October 16, 7060

ጎበዝ ... ጥቂት ሂሳብ እንስራ! (ዘውድአለም ታደሰ)

1ኛ የኦሮሚያ ህዝብ ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ባደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለዘመናት ሁሉን ህዝብ በፍቅር ሲያስተናግድ የኖረው የሶማሊያ ህዝብ የኦሮሞ ተወላጆችን ገደለ ተባለ።
በሚገርም ሁኔታ ግን አንድ ቀንደኛ የኤህአዴግ አባልና ደጋፊ እንዲሁም የሶማሌ ባለስልጣናት የቅርብ ዘመድ የሆነች ሴት ቆስለው ወደወደቁ ሁለት ተፈናቃዮች እጇን ቀስራ እየሳቀች የተነሳችው ፎቶ ፌስቡክ ላይ ታየ።
ከተፈናቃዮች መሀከል አንዳንዶቹም “የገደለን የሶማሌ ክልል ፖሊስና ልዩ ሀይል እንጂ ህዝቡ አይደለም። እንደውም ህዝቡ ታድጎናል” ሲሉ ተደመጡ።
(መቼም ከመንግስትም ሆነ ከግል ሚድያ ይልቅ ራሱ ተፈናቃዩን ልናምን ይገባል)

እና ይሄ ግፍ በሶማሊያ ምድር ላይ ለምን እንዲፈፀም ተፈለገ?

2ኛ የሶማሌ ህዝብ የኦሮሚያን ህዝብ ገደለ ፣ አፈናቀለ ፣ ብንል እንኳ የሶማሌ ልዩ ሀይል እንዴት ጣልቃ አልገባም? የሶማሌ ህዝብስ ካልጠፋ ግዜ አሁን ድንገት ተነስቶ አብረውት ለዘመናት የኖሩትን የኦሮሚያ ተወላጆች ያለምንም ምክኒያት ለምን ይገድላል?

3ኛ ኦሮሚያ ውስጥ ከሁለት ቀን በፊት ከፍተኛ አመፅ ተቀስቅሶ በተለይ የአማራ ተወላጆች ንብረት ወድሟል። በሚገርም ሁኔታ ግን ሰልፉን የጠራው አካል አልታወቀም። ይባስ ብሎ የሌላ ብሔር ተወላጆች ሰልፉ ላይ ንብረት ሲያወድሙ ተያዙ ተብሎ ፎቷቸውን ሁሉ አየን። ሰዎቹ የደቡብ ክልል የፖሊስ ሃይል አባላት ናቸውም ተብሏል።

እነዚህን ሰዎች ማን ላካቸው። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የአማራ ንብረት ሁን ተብሎ በመውደም በሁለቱ ብሔሮች መሀከል ጠብ እንዲነሳ የሚፈልገው አካል ማን ነው?

4ኛ ዛሬ ENN ቲቪ ላይ ብዙ ሰው የሚጠብቀው የጊዮርጊስና የቡና ጨዋታ ተላለፈ። በጨዋታው መሀል ግን ባልተለመደ ሁኔታ ሰበር ዜና ተብሎ በኢሊ አባቦራ ከተማ አማሮች በብሔራቸው ምክኒያት ብቻ እየተገደሉና ንብረታቸው እየወደመባቸው ነው የሚል አስደንጋጭ ዜና ተላለፈ።

ENN ቴሌቭዥን ይህን ህዝብ የሚያጫርስ መረጃ በግልፅ ለህዝብ ያስተላለፈበት ሰአትና በስፍራው ሪፖርተር እንኳ ሳይልክ እዛ አካባቢ ነን የሚሉ ሁለት ሰዎችን ብቻ አናግሮ መሆኑ ጥርጣሬን ያጭራል። አላማው በዚያ አካባቢ ያሉ ሰዎችን መታደግ ከሆነስ የሌላ ብሔር ተወላጆችና አማሮችን ከማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ያልሆኑ (መጤዎችን) ብቻ ማለት አይበቃውም ነበር ወይ? እንዲህ አይነት ሚድያ እንዲህ አይነት መረጃን ያለጥንቃቄ ለህዝቡ ማስተላለፍ ውጤቱ አደገኛ መሆኑ ጠፍቶት ነው? ወይስ ከመረጃው ጀርባ አንድ በሁለቱ ብሔሮች መሀከል የርስበርስ ግጭት እንዲነሳ የሚፈልግ ስውር አካል አለ?

5ኛ ቀኑን ሙሉ በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞዎች በጭካኔ ተገደለች ተብላ በሚዘገንን ሁኔታ መጥረቢያ አንገቷ ላይ የተሰካ ወጣት ፎቶ ፌስቡክ ላይ ሲሽከረከር ነበር። ብዙ የትግራይ ልጆችም በሁኔታው ማዘናቸውን ሲገልፁ ነበር።

ወደማታ ግን ነገሩ ሌላ ሆኖ ተገኘ። ይሄ ዘግናኝ ፎቶ ራማይ ከተሰኘ የትግሪኛ ፊልም ላይ ስክሪን ሹት የተደረገ ነበር።
ታዲያ ኦሮሚያ ክልል የትግራይዋ ወጣት በጭካኔ ተገደለች በማለት ሁን ብሎ ከፊልም ላይ ፎቶዋን ቆርጦ ሀሰተኛ መረጃ በመልቀቅ በትግራይ ተወላጆች መሀል መደናገጥ እንዲፈጠርና ኦሮሞ እንደአውሬ እንዲታይ ታትሮ እየሰራ ያለው አካል ማን ነው? ምን አይነት ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት?

ለኔ የነዚህ ሁሉ መልስ ወደአንድ አካል ይጠቁመኛል! እናንተም አእምሯችሁን ተጠቅማችሁ መልሱ ላይ ለመድረስ ሞክሩ!!

ኢትዮጵያ ለዘልአለም ትኑር!

Filed in: Amharic