>
3:38 pm - Thursday May 19, 2022

ሀብታሙ ስለ ህወሓት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ፤ አሉላ ስለ ትግራይ ህዝብ ብሎ ነው የሚሰማው (ግርማ ሰይፉ ማሩ)

እኔና አሉላ ሰለሞን በግንባር በመገናኘታችን መንስዔ የተለያዩ አስተያየቶችን ተቀብያለሁ፡፡ ተጠቃሎ ሲታይ በሃሳብ መለያየት፣ጠላትነት ያለመሆኑን እና የዚህ ዓይነት የሰው ለሰው ግንኙነት በቀጣይ ለሚደረጉ የሃሳብ ልውውጦች እንደሚረዱ ብዙ ሰው እንደሚያምን ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ይህ በግሌ ዘወትር የማምንበት በመሆኑ ብዙ ሰዎች የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች መሆናቸውን በማወቄ ደስ ብሎኛል፡፡ አልፎ አልፎ ግን በሁለታችን ግንኙነት ወቅት ምን እንደተነጋገርን ብዙ ሰው የማወቅ ጉጉት ማሳደሩን ተረድቻለሁ፡፡ በዚሁ መነሻ አጭረ ነገር ማለት ፈለኩኝ፡፡

ከአሉላ ጋር ሰንገናኝ በርዕዮተ ዓለም አንድነት ፈጥረን አሸናፊ የሆነ ወደ አንዱ ጎራ ለመቀላቀል አልነበረም፡፡ ግንኙነቱን የጠየኩት እኔ ነበርኩ እንዲህ ብዬ “እንገናኝ መሰማማት የለብንም ነገር ግን፣ ነገር ልናበርድ እድል አለን፡፡ ከከፈለክ ያለህበት ልምጣ … ወይም እኔ ቤት ይሁን፡..” በሚል፡፡ በዚሁ መሰረት ያለበት ቦታ ድረስ ሄጄ ተገናኘን፡፡ እኔ ከምጠብቀው በላይ ረጅምና ደልዳላ ሲሆንብኝ፤ እርሱ ደግሞ ከሚጠብቀው በታች አጥሬበት ሁለታችንም ሰለእያንዳንዳችን ያለን ግምት ልክ እንዳልነበር በቀልድ ጀምረን አሉላ እንዳለውም ወደገደለው ነው የገባ ነው፡፡

አሉላ በዋነኝነት “ጽንፈኛ” የሚላቸው ዲያስፖራቸው፣በሚያድረጉልን ድጋፍ የተነሳ ጫና እንደሚያደርጉብን፣ በዚህ የተነሳም ባለፈው አሜሪካ የመጣው ጊዜም ከዶ/ር መረራ ጋር አብረን ለመስራት ባለመቻላችን መድረክ ውስጥም ችግር እንደነበረ፡፡ በመግቢያነት ያነሳው ነጥብ ነበር፡፡ አሉላ እንደሚያስበው እኔ የዲያስፖራ ጫና የሌለብኝ መሆኑን አንድም ቀን አሜሪካን ሀገር ሰመጣ በፓርቲ ወይም በዲያስፖራ ሰፖንሰር ተደርጌ እንዳልመጣው፣ ይልቁንም በራሴ ወጭ መጥቼም ቢሆን ግን ሁሌም የፓርቲ ተግባር አከናውኜ እንደምመለስ በዝርዝር አስረድቼዋለሁ፡፡ ለተቃዋሚዎች ከዲያስፖራ ብር ይጎርፍላቸዋል የሚለው የተሳሳተ ተረክ በህወሓት/ኢህአዴግ ካድሬዎች ብቻ ሳይሆን በፓርቲ ውስጥም ሆነ ፓርቲው አብሮ ከሚሰራቸው ድርጅቶች ጋር የልዮነት ምንጭ እንደሆነ አስረግጬ ለመንገር ሞክሪያለሁ፡፡ ይህን ማመን ያለማመን የአሉላ ፋንታ ቢሆንም እውነቱ ይህ ነበር፡፡

ከአሉላ ሰለሞን ጋር የቆየንባቸውን ጊዜ ግማሹን ማለት ይቻላል የወሰደው የሀብታሙ አያሌው ንግግሮችና መፅሃፉ ሲሆኑ አሉላ ሀብታሙ ለመረዳት ቁጭ ብለው ማውረት የግድ የሚላቸው ይመስለኛል፡፡ አሉላ ሰለሞን ሀብታሙ አያሌውና ፕ/ሮ መስፍን ወልደማሪያም ለአንድ ቀን በአሜሪካን አገር ከመገናኘታቸው ውጭ ምንም ትውውቅ እንደሌላቸው የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ፕ/ሮ መስፍን የሚፅፉትን የሚያነበንብ አድርጎ ነው የሚገምተው፡፡ ሀብታሙ ሰለ ህወሓት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ አሉላ ሰለ ትግራይ ህዝብ ብሎ ነው የሚሰማው፡፡ በግንባር ውይይታችንም ቢሆን የተረዳሁት ይህንን ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ህወሓት ሰንል አባላቶቹን ብቻ ነው ስንል አይደለም ይሉናል፡፡ ከዚህ በፊት በእስር ቤት እነ ሀጎስ ብዬ የፃፍኩቱን ምዬ ተገዝቼ አስረድቼዋለሁ፡፡ ይህን ለማጣራት ቃሊቲ መሄድ በቂ ሆኖ ሳላ ጭቅጭቅ እንደማያስፈልግ ጭምር፡፡

ከዚህ ውጭ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተጠናከሩት ሰርዓቱ አፋኝ ከመሆኑ ይልቅ የፓርቲዎቹ ድክመት ተደርጎ እንዲወሰድ አሉላ ይፈልጋል፡፡ መንግሰት በመድበለ ፓርቲ ላይ ያለው አቋም አገሪቱ እንዳትበታተን ካለው ፍላጎት መሆኑንም ይገልፃል፡፡ ይህ ሃሳብ በመንግስት ሚዲያ ከምንሰማው የሚለይ አይደለም፡፡ በዚህ መስመር የነበረን ረጅም ውይይት ጉንጭ አልፋ ነበር፡፡ ነገሩ ለመስማማት ስለ አልነበር አልመስማማታችን አይገርምም፡፡ አሉላ ባለፈው ፅሁፉ እንዳለው በተቃዋሚ ጎራ ያለውን ድክመት ግን በግሌ ትክክል መሆኑን ገልጬለታለሁ፡፡ መፍትሔው በእጃችን እንደሆነም፡፡

በህወሓት ዙሪያ ያቀረብኩለት ግልፅ ጥያቄ “ህወሓት ከሌሎቹ የግንባር ድርጅቶች በተነፃፃሪ ወጣት የሚባሉ ማፍራት አልቻለም፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ የምትጠቅስልኝ እገሌ የሚባል ህወሓት ውስጥ (ከጌታቸው ረዳና ዛይድ በስተቀር) አለ ወይ? የሚል ነበር፡፡” ሊመልስልኝ ባለመቻሉ ምክንያት “ህወሓት እንደ ከዚህ ቀደሙ በግንባሩ ውስጥ ጠንክሮ የመሪነት ሚና ሊጫወት አልቻለም፡፡ ለምን ገብታችሁ አታግዙትም? በፌስ ቡክ ሳይሆን በትክክል ለምን ወጣቶች ገብታችሁ አትሳተፉም? አሁን ህወሓት ከመለስ ሞት በፊት የነበረው ነው ወይ? ብዬውም ነበር፡፡” በቀጥታ ባይሆንም የሰጠኝ መልስ፤ ችግሩ ሁሉም ህወሓት ኢትዮጵያን የመምራት ሃላፊነት ያለበት ሰለሚመሰለው ነው፡፡ ህወሓት ጥንካሬው መለካት ያለበት ክልሉን በማስተዳደሩ አቅም ላይ መሆን አለበት፤ ሌላው የሁሉም አባል ድርጅቶችና አጋሮች አላፊነት ነው ብሎኛል፡፡ ከዚህ በላይ ዝርዝር መልስ ሰለማልፈልግ ወደ ሌላ ርዕስ ነው የተሸጋገነው፡፡

ማህበረ ቅዱሳን፣የቅንጅት ጉዳይ፣ የፓርቲ መሪዎች ንግግር፣የአክሱም አውልታና ወላይታ፣ ባንዲራ ጨርቅ ነው፣ ኢትዮጵያዊነትና ዘውጌነት፣ ወዘተ ለሁሉም ግን መልሶቹ መለስ እንዳለው ሲሆን በመጨረሻም “ህዝብ” የሚባል ምሽግ አለበት፡፡ እኔ የመጣሁት ህዝብ ወክዬ ሰለ አልሆነ ሰለሚያሰበው ግለሰብ ተጠያቂነት መሆኑን ገልጨለት፣ በግል የማንም ፀር እንዳልሆንኩ አስረድቼዋለሁ፡፡ ህዝብ የጋራ ጭንቅላት እንደሌለው መናገር መቼም ክፋት አይደለም፡፡ በግሌ እምነቴ ተጠያቂነት የሚወስድ ግለሰብ ጉዳይ ነው፡፡ ሲደመር ነው ህዝብ፡፡

በእውነቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ያላነሳነው ያልጣልነው ነገር የለም፡፡ የተሰማማንበት ነገር ቢኖር ላለመስማማት መስማማት እንደሚቻል ነው፡፡ እኔና አሉላ የአንድ ፓርቲ አባል ልንሆን አንችልም፣ አሉላ ሰለሞን አሜሪካንም ቢሆን የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የልማታዊ መንግሰት ተከታይ ነው፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ሆኜ የሊብራል ዴሞክራሲ አቀንቃኝ ነኝ፡፡ አንድ የሚያደርገን ብዙ ነገሮች እንዳሉ ተረዳድተናል፡፡ በመሰዳደብና መጠላላት ምንም ለአገራችን እንደማንጨምር ለመረዳዳት ችለናል፡፡ የሰለሞንን ልጅን በማግኘቴ ምንም አልተከፋሁም፣ ባለገኘሁት የሚል ቁጭት አላደረብኝም ይልቁንም በተደጋጋሚ ተገናኝተን በተደራጀ እና አጀንዳ ባለው ሁኔታ ብንነጋገር ለዚህች አገር አንድ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችል ይሆናል የሚል ተሰፋ ጭሮብኛል፡፡
ተስፈኛው ግርማ ሠይፉ ማሩ፡፡

Filed in: Amharic