>

መተከል ጎጃም ነበር፤ አማራ ግን «አገርህ አይደለም» ተብሎ እንደ ፋሲካ ዶሮ ይታረድበታል! (አቻምየለህ ታምሩ)

ወያኔ ከጎጃምና ከወለጋ ወስዶ በፈጠረው «ቤንሻንጉል ጉሙዝ» በተባለው ክልል ውስጥ ከጎጃም የተወሰደው መተከል አውራጃ አዲስ የተፈጠረው ክልል ሰፊው ዞን ነው። በዚህ የወያኔ ክልል ውስጥ ዛሬም ድረስ አብዛኛው ባላገር አማራና ኦሮሞ ነው። እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. ወያኔ ባካሄደው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ ቤንሻንጉል ክልል የሚባለው ክልል ውስጥ 784,345 ኗሪዎች ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ 170,132 የሚሆነው አማራ ሲሆን 106,275 የሚሆነው ደግሞ ኦሮሞ ነው።

ክፍሌ ወዳጆ የሚባለው የወያኔ አገልጋይ በጻፈው ሕገ አራዊት ግን የክልሉ ሕገ መንግሥት በተባለው ሰነድ ውስጥ ጠቅላላ ድንጋጌዎች በቀረቡበት ምዕራፍ አንቀጽ 2 ስር ስለክልሉ ባለቤቶች እንዲህ ይላል፤

«በክልሉ [በቤንሻንጉል ክልል ለማለት ነው] ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም፤ የክልሉ ባለቤት ብሄር፣ ብሄረሰቦች ግን በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው።

ልብ በሉ! የክልሉ ባለቤቶች የተባሉት ብሄርና ብሄረሰቦች ለምሳሌ ጉምዝ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. ወያኔ ባካሄደው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ብዛቱ 163, 781፤ ሺናሻ 60,687፤ ማኦ 15,384 ሲሆን ኮሞ ደግሞ 7, 773 ነው። ከነዚህ የክልሉ ባለቤቶች ከተባሉት ብሄር፣ ብሄረሰቦች ቁጥር የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ትናንትና ጎጃምና ወለጋ የተወለዱ አማራና ኦሮሞዎች ግን ዛሬ ከጎጃምና ወለጋ ተወስዶ በተፈጠረው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ እትብታቸው በተቀበረበት ምድር ባለቤቶች አይደሉም።

ባጭሩ ትናንትና ወለጋ የተወለዱ ኦሮሞዎችና ጎጃም የተወለዱ አማሮች እትብታቸው የተቀበረበት መሬት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደሚል ስለተቀየረ መኖሪያ ፈቃድ ያላቸው «ኗሪዎች» እንጂ የተወለዱበት ምድር ባለቤቶች አይደሉም ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ እነዚህ ትናንትና ወለጋና ጎጃም የተወለዱ ኦሮሞና አማራዎች ዛሬ በፋሽስት ወያኔ ዘመን በተዘረጋው የከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ አብረዋቸው የኖሩት ጎረቤቶቻቸው የክልሉ ባለቤት ሲሆኑ እነሱ ግን አማራና ኦሮሞ በመሆናቸው የተነሳ አገር አልባ ሆነዋል ማለት ነው። This is a classic textbook example of apartheid Ethiopia. It looks like apartheid, it walks like apartheid, it behaves like apartheid; it’s apartheid!

ትናትና ጎጃም ክፍለ ሃገር መተከል አውራጃ የነበረው የዛሬው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጎጃም ውስጥ ከነበሩ አውራጃዎች አንዱ እንደነበር ከፍ ብዬ ጠቅሻለሁ። ወያኔ በነውረኛው ክፍለ ወዳጆ አዝማችነት የጎጃሙን መተከል አውራጃ ለሁለት ክልሎች ሰነጠቀው። አንዱን ስንጣቂ «አዊ ዞን» የሚባል ፈጠረና ወደ «አማራ ክልል» ሲካተተው የተቀረውን ስንጣቂ ደግሞ «መተከል ዞን» ብሎ «ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል» ብሎ በፈጠረው ክልል ውስጥ አካትቶ ተከዜን ተሻግሮ በጎንደርና ሱዳን እየተዋሰነ ከተዘረጋው የትግራይ ክልል ጋር አጎራበተው። ይህ ሁሉ ሆኖ ዛሬም ድረስ «መተከል ዞን» ውስጥ በብዛት የሚኖረው አማራ ነው። አማራ እንዳይኖርበት «የሌላ ክልል» ብለው በፈጠሩት ግዛት ውስጥ ይህ መሆኑ ያበሳጫቸው ወያኔዎች እንደ ሰንበሌጥ አጎንብሶ የሚነሳውን፤ እንደ በቆሎ ዘር ጠውልጎ የሚያለመልምውን፤እንደ ወይራ ዛፍ ደርቆ የሚያቆጠቁጠውን ስር ነቅለው ሊጨርሱ ያልፈጸሙት የጭፍጨፋ አይነት የለም።

ከርስቱ ከመተከል አውራጃ ባለቤት አይደለም ተብሎ አማራ እየተጨፈጨፈ «ወደ አገርህ ሂድ» ተብሎ የሚሳደደው የጋምቤላ ክልል መሬት ተወደድብን ላሉ የትግራይ ባለሃብቶች ሰፋፊ መሬቶችን ለመስጠት ሲባል ነው። ክልሉን እንዲያስተዳደር የተሰየመው ምስለኔው አሻድሊ ሀሰን «አማራዎችን ከአገራችሁ አስወጡ» ተብሎ ትዕዛዝ ተላልፎለታል። ማፈናቀሉ ግን በአንድ ዙር እንዳይካሄድ በጥብቅ እንደታዘዘ ባለፈው ሰሞን ጽፈን ነበር።

እቅዳቸው ተራ በተራ በማፈናቀል ያን ለም መሬት ለትግራይ ባለሃብቶች ጨርሶ ለመስጠት ነው። ትናንትም ሆነ ዛሬ እየሆነ ያለው ይህ ነው። ትናንት የተጨፈጨፉትን አማሮች ቦታ ለማረስ ተጨማሪ የትግራይ ባለሀብቶች ከሰሞኑ ከአውሮፓና ከአሜሪካ እየተጠሩ ከልማት ባንክ ያሻቸውን ገንዘብ በመዛቅ ትራክተር ከኤፌርት ገዝተው መተከል እንደሚገቡ ይጠበቃል። በአማራ መቃብር ትግራይን ይገነቧል ማለት ይህ ነው።

ጎጃም-መተከል! አማራው እየተጨፈጨፈ የትግራይ ባለሀብቶች ሰፋፊ የእርሻ መሬት የሚሰጥበት ምድር!

እንዲህ ዳምኖ ዳምኖ የዘነበ እንደሆን፣
እንዴት ያሉ በሮች ይጠመዱ ይሆን?
እንዲህ ጭሶ ጭሶ የነደደ እንደሆን፣
የአመዱ መጣያ ስፍራዉ ወዴት ይሆን?
ንገሯት ጎጆዬን አቃጥላታለሁ፣
ሲያጨሱ እየጬሰች ያለኝ እመስላለሁ፤
ያንተ ልጅ ሲበላ የኔ ልጅ አልቅሶ፣
ያንተ ቤት ሲታደስ የኔ ጎጆ ፈርሶ፣
ለኔም መሄጃዬ ላንተም መጥፊያህ ደርሶ።
….

በግፍ የወደቁ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር!

Filed in: Amharic