>

‹‹ሀገሬ…›› (ህይወት እምሻው)

በከባድ ንፋስና ዝናብ ሰአት ትልልቅ ዛፎችን አይታችሁ ታውቃላችሁ?
የቅጠሎቹን ሳያቋርጡ መርገፍገፍ፣ የቅርንጫፎቹን መንቀጥቀጥ ስታዩ ‹‹ይሄ ዛፍ ካሁን ካሁን ወደቀ፣ ካሁን ካሁን ተገነደሰ ››ብላችሁ ሰግታችሁ ይሆናል፡፡

ቅርንጫፎቹ ቅንጥስ እያሉ ቢወድቁም፣
ቅጠሎቹ ባንድነት ቢረግፉም፣ ግንዱን ብትመለከቱ ግን አይነቃነቅም፡፡
ምክንያቱም ስር የሰደደ ነው፡፡
ምክንያቱም መሬትን ቆንጥጦ የያዘ ነው፡፡
ምክንያቱም ጠንካራ ነው፡፡
ምክንያቱም ግንድ ነው፡፡
….እና እኔ ሀገሬ ግንዱን ትመስለኛለች፡፡
ቅርንጫፎቹ መንግስታቷን፡፡
ቅጠሎቹ ደግሞ ማለዳ እንደ አዲስ በቅለው ማምሻውን እንደ አሮጌ የሚረግፉ ባለስልጣናትዋን፡፡
እና…
ሀገሬ ምን ጋኖች አልቀውባት በምንቸቶች ብትሞላ፣
ምን ለአንዱ በስንዝር ለሌላው በሄክታር ብትታደል፣
ዘወትር በእመቤት ወግ ባትኖር
በጭጋጋማ ቀናት ብትሸፈንም፣
በውርጭ ብትንዘፈዘፍም፣
በብርቱ ንፋስ ብትናወጥም፣
በዶፍ ዝናብ ብትደበደብም፣
ግንድ ናት እና ንቅንቅ አትልም፡፡
አውሎ ንፋስ በተነሳ ቁጥር፣
ከባድ ዝናብ በጣለ ቁጥር፣
ትልቅ ዛፍ ሁሉ ቢወድቅ ኖሮ ዛፍ አይኖርም ነበር፡፡
ነውጥ በተነሳ ጊዜ ሁሉ፣
ፈተና በበዛ ሰአት ሁሉ፣
ሀገር የምትወድቅ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ግን ቅርንጫፍ ስላልሆነች በቀላሉ አትቀነጠስም፡፡
ቅጠል ሳላልሆነች እንደዋዛ አትረግፍም፡፡
ይልቁንስ ፤ ለዘልአለም ስር እንደሰደደች ትኖራለች፡

Filed in: Amharic