>
3:46 pm - Thursday May 19, 2022

ህወሀት ምስጥ የጨረሰው ኩይሳ ሆኗል (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ነው። ነግቶ በመሸ ቁጥር አዲስ ነገር ይሰማል። አዲስ ቀን አዲስ ክስተት ይዞ ብቅ እያለ ነው። ባለፉት ሁለት ወራት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽ ላይ የተፈጠሩት ክስተቶች ባለፉት 25 ዓመታት ከሆኑት አንጻር ፈጣንና አይቀሬ ለውጥ በቅርበት እንዳደፈጠ የሚጠቁሙ ናቸው። ለውጡ ምን እንደሆነ አሁን ላይ መተንበይ ሊያስቸግር ይችላል። ጽልመትና ተስፋው ከፊት ተደቅነዋል። ጨለማው በእጅጉን የጠቆረውን ያህል በጭላንጭል የሚታይ ብርሃንም አለ። ጽልመቱ እንዳያሸንፍ፡ ለውጡ የመጥፎ እንዳይሆን ከጸሎት ባሻገር ትንፋሽ ወስዶ፡ ቁጭ ብሎ መመካከር ያስፈልጋል።

ህወሀት በአጭሩ ደክሞታል። ሲፈጠር ጀምሮ ያጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ሳያገኝ ወደ መቃብሩ ጉዞ የጀመረ ይመስላል። በውስጣዊ የሃይል መሳሳብ ጉልበቱ ዝሎ፡ አቅሞ ተሟጦ፡ ሞተሩን እንደነከሰ አውቶሞቢል መንተፋተፍ ከጀመረ ሰንብቷል። ህወሀት ከእርጅናው ጋር ተዳምሮ የገባበት ውጥንቅጥ የቋመጣትን 100 ዓመት የመግዛት ህልሙ እንዲጨናገፍበት አድርጎታል። የህልሙን ሲሶ እንደኖረ በታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሊሰናበት 11ኛው ሰዓትን ተጠግቷል።

በእርግጥ የስብሃትና የሳሞራ ቡድኖች በር ዘግተው በህንፍሽፍሽ ሲሞዣለቁ ከከረሙ በኋላ በስብሃት ቡድን አሸናፊነት ግብግቡ ማብቃቱም ይነገራል። ሆኖም ህወሀት የትኛውም አንጃ ነጥሮ ቢወጣ ደካማ ህወሀት መሆኑ አይቀርም። ከእንግዲህ ሳሞራም ያሸንፍ ስብሃት ህወህትን የሚታደግ አንጃ አይኖርም። ህወሀት ጥይቱን ጨርሷል። ተልፈስፍሷል። ምስጥ የጨረሰው ኩይሳ ሆኗል። መለስ ዜናዊ በቁሙ ህወሀት ሲፈርስ ሳያይ ሞት ስለቀደመው እድለኛ ነው። እንደ ጋዳፊ በጥፊ እየተመታ፡ በውርደት ከመሞት አምልጧልና።

እንደሰማነው ህወሀት የሽግግር መንግስትን እንደሁለተኛ አማራጭ ይዟል። በአጥንቱም ቢሆን ረግጦ መግዛት የማይችል ከሆነ መከላከያውና ደህንነቱ ከእጁ ሳይወጡ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ፍላጎት እንዳለው የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል። ይህ ካልሆነም ኢትዮጵያውያን መሃል በየቦታው የቀበረውን ፈንጂ እንዲፈነዳ በማድረግ ወደ መቀሌ ገብቶ የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት በፕላን C ይዞታል። ለዚህም አጀንዳውን ቀስቅሶ በአንዳንድ ቦታዎች ተጋሩዎች ውይይት ማድረግ ጀምረዋል። ሰሞኑን የአዲስ አበባ ተጋሩዎች በትግራይ መገንጠል ዙሪያ አጀንዳውን እንደመከሩበት ተሰምቷል። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ሆነና ህወሀት ከማይቀረው ሞቱ ለማምለጥ የትኛውንም ሙከራ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም። ኢትዮጵያ ጠፍታ ህወሀት የሚተርፍ ከሆነ ያደርገዋል። ውዷን ሀገራችንን ከማጥፋቱ በፊት እንዲጠፋ ማድረጉ የዚህ ትውልድ ትልቁ የቤት ስራ ሆኗል።

የትግራይ ህዝብ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ከሰሞኑ የሚሰሙት ነገሮች ለትግራይ ህዝብ የማንቂያ ደውል ሊሆኑ ይገባል። የሆኑትና ሊሆኑ እያንዣበቡ ያሉት አደጋዎች ያስፈራሉ። ለኢትዮጵያችን የማይገቧት ናቸው። የትግራይ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት በስሙ ከነገደው፡ በስሙ ከዘረፈው፡ በስሙ ከገደለውና በመጨረሻም ብቻውን ወደ መቃብሩ እየገሰገሰ ካለው ህወሀት ጋር ፍቺ የሚፈጽምበት ጊዜ ቢዘገይም አሁንም ይጠበቃል። በግልጽ ለመናገር የትግራይ ህዝብ ከህወሀት ጋር የሚፈጽመው ፍቺ ለኢትዮጵያ ፈውስ ይሆናል።

እናም የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ሊቆም ይገባል። ትላንት አልፏል። ዛሬ ግን በትግራይ ህዝብ እጅ ነው። ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆነ ግልጽ መልዕክት እያሰማ ነው። ይህ ጸረ ህዝብ የሆነው ስርዓት ስልጣን ላይ የቆየበት ዘመን ለትግራይ ህዝብ መጥፎ ዘመን ላይሆን ይችላል። ለኢትዮጵያውያን ግን የመከራ፡ የፍዳና የስቃይ ዘመን መሆኑን የትግራይ ወገኖቻችን ሊረዱትና ህወሀትን በቃ! ሊሉት ይጠበቅባቸዋል። ዛሬ ሳይሆን አሁኑኑ!!!!

Filed in: Amharic