>
11:03 am - Friday October 22, 2021

መንግስት ያለዓላማ ይግደል እንጂ ህዝቡ የሚሞትለትም ሆነ የሚኖርለት ዓላማ አለው (ባለ ዕምባ ራስ)

ሰሞኑን በየአቅጣጫው ያለውን እሳት ራሳችንን ካልካድን በስተቀር ማን ፣ መቼ ፣ እንዴት እና ለምን እንዳቀጣጠለው ሁላችንም እንደምናውቀው የማይታበይ ሀቅ ነው።

ይህ እሳት በየዘመኑ በተለያዩ ምክንያቶችና በተለያዩ አካላት ተቆስቁሶ ንፁሀንን እየፈጀ ሲዳፈን ከርሞ ዘንድሮ ግን ግልጥልጥ ብሎ መለብለቡን ተያይዞታል።

በመንግስት ላይ የሚደረጉ ተቃውሞዎች ያለጥይት ድምፅና ያለድንጋይ እሩምታ እንዲሆን የህዝቡ ምኞት ቢሆንም የአሸባሪው መንግስታችን እና በደሉ ያንገሸገሻቸው ሀይሎች ፍላጎት ግን ሀገሪቱን ወደጦር አውድማ እያመራት መሆኑን እያየን ነው።

መንግስት ያለዓላማ ይግደል እንጂ ህዝቡ የሚሞትለትም ሆነ የሚኖርለት ዓላማ አለው። ዋናው የህዝቡ ዓላማ በይፋ እና በመግባባት የኢትዮጵያን አንድነት ዳግም ለመመለስ ከዘረኝነት የፀዳን ጎጆ በፍቅር ለማነፅ መሆኑን ማረጋገጡ ላይ ነው።

ብዙዎች የህዝብን ዓመፅ በመጠምዘዝ ለዘረኛ ፖለቲካቸው ፍጆታ፣ ለጥቂት ሆዳሞች ዝርፊያ፣ ለድንቁርና አመላካከታቸው ቂም መበቃቀያ እና ወጣቱን ለስልጣን ጠባቂ ወታደሮች እራት እያደረጓቸው ነው።

የህዝብ እንቢተኝነት(አመፅ) የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት በማያሰጋ፣ አላስፈላጊ የሰውም ሆነ የንብረት ውድመት ሳያስከትል፣ ከተንሸዋረረ የዘረኝነት ዕይታ እና ከመከፋፈል ስሜት የፀዳ እስጠሆነ ድረስ በመላው ሀገሪቱ ዒላማውን ያልሳተ ቢሆን ይህን እርኩስ ስርዓት መንግሎ ለመጣል እንዲሁም በለኮሱት እሳት ስርዓታቸውን ለማንደድ ይቻል ነበር።

ከዚህ ዓላማ ውጪ የሆነ ዘርን እየቆጠረ “እከሌ ብሔር በደለኝ፤ እከሌን ብሔር ነፃ ላውጣ” በማለት የሚደረጉ አመፆች ዋጋቢስና የሰውን ህይወት የሚፈጁ ከመሆናቸውም በላይ ከአምባገነኑ ስረዓት የሚለይበት ምክንያት የለውም።

በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስጠብቅና ዜጎች ተቻችለው ተዋደውና በሀገራቸው ኮርተው የሚኖሩበትን ስርዓት የሚፈጥር አመፅ ቢሆን ወጣቱ ሁሉ ቀልቡን ልቡንም ሆነ ነፍሱን ከመስጠት አይቦዝንም።

በሀገር አንድነት እና በህዝብ እኩልነት የሚያምን ዜጋ ሀገሩ ለችግር በተጋረጠችበት ወቅት ሁሉ ከመጮህ እስከ መሞት ድረስ ራሱን የሚሰጥ ነው።

በተያያዘ…

ዛሬ ላይ የሁሉም ክልሎች ቃል እና ድርጊት የነገ እቅዳቸውን ያሳብቅ ጀምሯል። ስለትግራይ ህዝብ የሚሰማኝን ለመናገር የፈለኩት ወያኔን ስለወለዱት ሳይሆን ኢትዮጵያ የእነሱም እንደሆነች ስለምረዳ ነው።

በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ፣ የስርዓቱ ተጎጂ የሆኑ፣ የወያኔ ድብቅ ሴራ ያልገባቸውና ገብቷቸውም የሚታገሉ እንዲሁም ችግሩ “ላም እሳት ወለደች አትልሰው እሳት፤ አትተወው ልጅ ሆነባት” የሆነባቸው ብዙ የትግራይ ተወላጆች አሉ።
በተቃራኒው ደግሞ “ወርቅ ከሆነ ህዝብ ተፈጥረን፣ ለነፃነታችን ታግለን ለስልጣን የበቃን ህዝቦች ነን” የሚሉ፣ ባካበቱት የተዘረፈ ሀብት ሳቢያ ለደህንነታቸው ሲሉ ከኢትዮጵያዊነት ትግራይነት የበለጠባቸው፣ የድብቁን ሴራ ዓላማ ለማየት የሚቋምጡ ለህዝቡ ህይወትና ለሀገሪቱ ደህንነት የማይጨነቁ ትምክህተኛ እና ግብዝ የትግራይ ልጆችንም አውቃለው።

ይሁን እንጂ በታሪክ ሊያፈራርዱና በትውልድ ሊያጠያይቁ የሚችሉ ግፍና በደሎች በሁሉም አቅጣጫዎች ተፈፅመው ያሳዩትን ዝምታ ሰብረው፣ የስርዓቱ ቁንጮዎች እና የአመፁ አጀንዳ “ዘረኝነት” በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚመለከታቸው አምነው፣ ብዙዎች በስማቸው እንደሚበድሉ፣ እንደሚሰርቁ፣ እንደሚፎክሩ ወዘተ ተረድተው ይህንን በመቃወም፣ ሀገራዊ አንድነታቸውን በመግለፅ እና የደረሱት እልቂቶች ሁሉ የእነሱም ሀዘን መሆኑን ገልፀው ከሰፊው ህዛባቸው ጋር ያለጥርጣሬና ያለጥላቻ በጋራና በፍቅር መኖር እንደሚገባቸው አምናለው።

“ወያኔዎች ኢትዮጵያዊነትን በልተውና ሽጠው የጨረሱ ሁለንተናዊ ድሆች በመሆናቸው ራቁታቸውን ቁመው ለቀሩበት ዕርቃን አካላቸው መጠለያ ለማግኘት ሲሉ የትግራይን ህዝብ ሙጭጭ ብለው እንደያዙት ግልፅ ነው። መጠለያ ጊዜያዊ መኖሪያ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ወለድ ችግሮችንም መከላከያ በመሆኑ አዳኝም ሆነ ታዳኝ ፍጡራን ሁሉ ከጭልፊት ጀምሮ የሰላም ተምሳሌት እስከሆነችው ርግብ ጭምር የራሳቸውን መጠለያ አዘጋጅተው ይጠቀማሉ።

የትግራይንም ህዝብ መደበቂያ ምሽግና መግደያ መሳሪያ አድርገው ወያኔዎች እየተጠቀሙበት ይገኛል። ከህዝቡ ተለይተው ቀርቶ ለአፍታ እንኳ ፊቱን ቢያዞርባቸው ፀሀይዋ ጠቁራ ጨለማ የሚውጣቸውና ሰማይ የሚደፋባቸው መሆኑን ስለሚያውቁ ይህንን ከባድ ጭንቀት እየተከላከሉ ጊዜያዊ እፎይታን በመውሰድ ጭንቀታቸውን በትግራይ ህዝብ ላይ በመጫን ነው።

ለዚህም ማሳያ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር በጋራ መድረክ ተገናኝቶ በጋራ ጉዳይ እንዳይመካከር፣ ለዘመናት በጋራ ያኗኗረውን የአብሮነት እሴት ግምት እንዲያጣ፣ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተገነባውን የወንድማማቾች ፍቅር ንደው በጥላቻ እና በጠላትነት እንዲፈረጁ በማድረጉ ፣ የአንድነት መሰረቱንና የዘመናት ታሪኩን አኮስሰው ወደ መንደርተኝነት በማሳነስ ለእነሱ ብቻ የምትመች ትንሽን ሀገር በምኞት ባህር በማሳየትና ወዘተ. . . ከራሳቸውም ከሰፊው ህዝብም ጋር ያቃቃራቸው እንደመሆኑ ይህንን መረዳትና ያለፍቅር ሰላምን ያለሰላም ሀገርን ያለሀገር ትግራይን እንደማይኖር ተረድተን በጋራ ታላቋን ሀገር ወደ ታላቅነቷ እንመልሳት።

Filed in: Amharic