>

የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 87ኛ ዓመት የንግስና መታሰቢያ (አምደ ጽዮን ሚኒሊክ)

ከ1909 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም በአልጋ ወራሽነት፣ በንጉስነትና በንጉሰ ነገሥትነት ኢትዮጵያን የመሩት ተፈሪ መኮንን ወልደሚካኤል (ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) ንጉሰ ነገሥት የሆኑት ከዛሬ 87 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም) ነበር፡፡

መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል በመኳንንቱና ኢትዮጵያን ለመቀራመት አሰፍስፈው ይጠብቁ በነበሩ ቄሳራውያን ኃይሎች ሴራ ከአልጋ ወራሽነታቸው ከተሻሩ በኋላ፣ የዳግማዊ አጤ ምኒልክ ልጅ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት የራስ መኮንን ወልደሚካኤል ልጅ ተፈሪ መኮንን ደግሞ አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ፡፡

ዘውዲቱ ንግሥት ተፈሪ ደግሞ አልጋ ወራሽ ከሆኑ በኋላ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከነበሩት የሥልጣን ሽኩቻ ሴራዎች እንደ አንዱ ተደርጎ የሚቆጠር ፍትጊያ አዲስ አበባ ውስጥ ታይቷል፡፡

የአልጋ ወራሹ ደጋፊና ታማኝ የነበሩ መሐል ሰፋሪዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ተፈሪ መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም ንጉስ የሚባል ማዕረግ አገኙ፡፡ (በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ንጉሥ ወይም ንግሥት በዙፋኑ ላይ እያለ ሌላ ንጉሥ/ንግሥት የሚሾምበት አሰራር ያልተለመደ ነበር)

የዘውዲቱ የቀድሞ ባለቤት ከነበሩት ከራስ ጉግሳ ወሌ ጋር የተደረገው የአንችም ጦርነት በተፈሪና ወዳጆቻቸው ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ንጉሰ ነገሥት መሆን እድላቸው እየሰፋ መጣ፡፡

ንግሥት ዘውዲቱ ከጦርነቱ ፍፃሜ ጥቂት ቀናት በኋላ ሲያርፉ ተፈሪ መኮንን ንጉሰ ነገሥት ከመሆን የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ ተረጋገጠ፡፡

ንጉሰ ነገሥት ለመሆን ረጅም፣ አስገራሚና አሳዛኝ የሴራ መንገድ ያለፉት ተፈሪ መኮንን በዓለ ንግሥናቸው ለጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም ቀጠሮ ተያዘለትና ሽር ጉዱ ተጀመረ፡፡

ንግስናው ከመከናወኑ በፊት ንጉሱና ንግስቲቱ የሚጓዙበት ሠረገላ ከጀርመን አገር መጣ፡፡ ልብሶቹ ሁሉ በወርቅና በሐር የተሸቆጠቆጡ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ ደሳሳ ቤቶች ፈረሱ፤ መንገዱ አስፋልት ሆነ፤ የከተማ ፖሊሶች ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ ዩኒፎርም ለበሱ፡፡ ቤተ-መንግስቱና አካባቢው በኤሌክትሪክ ብርሃን አሸበረቀ፡፡

በዓለ ንግሱ 15 ቀናት ሲቀሩት በበዓሉ ላይ ለመታደም ከአሜሪካና ከአውሮፓ የመጡ የመንግሥታት ተወካዮች በአዲስ አበባ ተገኙ፡፡ ብዛታቸው ለቁጥር የሚታክት ጋዜጠኞችም አዲስ አበባ ገብተው ስለነበር በዓለ ንግሱ በመላው ዓለም ትኩረት እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡

ጥቅምት 23/1923 ዓ.ም በመናገሻ ገነተ-ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) ተፈሪ መኮንን፣ ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ቅብዓ መንግስቱን ተቀብተው ዘውዳቸውን ጫኑ፡፡

ባለቤታቸው ወይዘሮ መነን አስፋውም የእቴጌነቱ ዘውድ ተደፋላቸው፡፡ ልጃቸው አሥፋወሰን ደግሞ ለአልጋ ወራሽነት የሚገባው ስርዓት ተፈፅሞለት የወርቅ አክሊል ደፋ፡፡ ስርዓቱ ተፈፅሞ ወደ ቤተመንግስት ተመልሰው ዙፋናቸው ላይ ሲቀመጡ 101 ጊዜ መድፍ እንዲተኮስ ተደረገ፡፡

ከዚያም ድል ያለ ግብዣ ተደረገ፡፡ አዲስ አበባም በንጉሰ ነገሥቱና በእቴጌይቱ ፎቶ፣ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንዲሁም በመብራት አሸብርቃ ቆየች፡፡ ተፈሪ መኮንንም በንግሥና ስማቸው ‹‹ኃይለሥላሴ›› ተብለው መጠራት ጀመሩ፡፡

ደመወዝ ለማስጨመር በተሰባሰቡ ወታደሮች ከዙፋናቸው እስከሚወርዱ ድረስ ም ለ44 ዓመታት ኢትዮጵያን በንጉሰ ነገሥትነት አስተዳድረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ህልፈት እስከ በዓለ ንግሥናው ድረስ የነበሩት ሰባት ወራት በኢትዮጵያ ታሪክ/ምድር ታይቶ የማይታወቅ የበዓል ማሸብረቂያ ዝግጅት የተካሄደባቸው ወራት ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ምድር ታይቶ የማይታወቅ ደማቅ የንግሥና በዓል ስለነበር ብዙዎችን አስደንቋል፡፡

Filed in: Amharic