ጠበቃው አቶ ዮናታን ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሀሳቡን በነፃነት ገለፀ እንጅ ሽብርተኝነትን የማበረታት ተግባር አለመፈፀሙን፣ ሆኖም የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ህግና ማስረጃን መሰረት ያላደረገ፣ ስህተትና ያልተገባ ነው ብለዋል። በመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በመሻር ይግባኝ ባይን እንዲያሰናብት ጠይቀዋል። ይህ ከታለፈ እንኳን እስካሁን የታሰረው ጊዜ በቂ ተብሎ ከእስር እንዲለቀቅ አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ ዮናታን በበቂ እንዲለቀቅ የቀረበውን ጥያቄ ካለፈውም ፣ ለስር ፍርድ ቤቱ 6 በመረጃ የተረጋገጡ ማቅለያዎች ቀርበው ፣ በእነዚህ ማቅለያዎች መሰረት ስድስት እርከን ዝቅ ብሎ መወሰን ሲገባ ሶስት እርከን ብቻ በመቀነስ ውሳኔ ስለተሰጠ ማቅለያዎቹ ተይዘው የቅጣት ውሳኔው ተሻሽሎ እንዲወሰን የይግባኝ ክርክር አቅርበዋል።
በሌላ በኩል አቃቤ ህግ አቶ መኩርያ አለሙ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፅሁፉ በኦነግ አላማ ሲያነሳሳ እንደነበር እና የተፈረደበትም በዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ፍርዱን ሊቀንስለት አይገባም ብሎ ተከራክሯል። አቶ ዮናታን በበኩሉ አቃቤ ህግ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ ክስ ማቅረቡንና በዚህም እንደተፈረደበት በማስታወስ፣ ሆኖም በቀረበው ክስ ላይ ከኦነግ ጋር አለው ስለተባለው ግንኙነት ማስረጃ እንዳልቀረበ፣ ፍርዱም ትክክል እንዳልሆነ ተከራክሯል።
አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተከሰሰውና የተፈረደበት ከ”ማስተር ፕላን” ጋር በተያያዘ ኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው የህዝብ ንቅናቄ ሰበብ ሲሆን አቶ ኃይለማይያም ደሳለኝ በመንግስት ሚዲያዎች ቀርበው ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የመልካም አስተዳደር ችግር እንጅ የሽብር ባህሪ የለውም ብለው መግለጫ ሰጥተው እንደነበር ጠበቃ ሽብሩ በለጠ አስታውሰዋል። የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ለመበየን ለህዳር 18/2010ዓም ተቀጥሯል።